የኦሮሞ ብሔርተኝነት ተፈታታኝ ተግዳሮቶች:- ሃይማኖታዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መጣረስ (ዩሱፍ ያሲን)

ሃይማኖታዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መጣረስ

ዩሱፍ ያሲን፣

ኢትዮጵያዊነት፣ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት በሚል በ2009 በታተመው መፅሐፋቸውን “የኦሮሞ ብሔርተኝነት ተፈታታኝ ተግዳሮቶች” በሚል ርእስ ስር ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል አንዱ የሃይማኖታዊ ማንነትና የብሔር ማንነት መጣረስ ነው። ኦሮሞ በአገሪቷ ደረጃ አብላጫ ቁጥር ያለው ስብስብ ብቻ ሳይሆን አብላጫ ሙስሊሞችን ያቀፈ ብሔረሰብ ነው፡፡ ትክክለኛው ቁጥር ቢዋዥቅም ኦሮሞ ከፍተኛ የእስልምና አማኞችን በውስጡ ያካተተ ማኅበረሰባዊ አሀድ መሆኑ ከቶ አያጠያይቅም፡፡ ከጠቅላላ ሙስሊም ውስጥ በያዙት አብላጫና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም የወደፊት አቅጣጫ የሚወስኑት የኦሮሞ ሙስሊሞች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ያለ እነሱ ምርኩዝነት ሊያድግና ሊስፋፋ ስለማቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

… በአገራችን የማንነት ፖሊተካ የብሔረሰብ ማንነት ከሃይማኖታዊ ማንነትና ወገንተኛነት ብሔረሰባዊ ወገንተኛነት እየተፎካከረው መሆኑን ልብ ማለታችን አይቀርም፡፡ ከሙስሊም ሕበረተሰብ ለዲናቸው (ለሃይማኖታቸው) ቅድሚያ የሚሰጡ እየተበራከቱ፣ ባንፃሩ ደግሞ የብሔረሰባቸው ማንነት የሚበልጥባቸው እያነሱ ናቸው ወደማለቱ መደምደሚያ ባንደርስም የሃይማኖቱ ማንነት የበለጠ ግምትና ትርጉም እየተሰጠው የመጣበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ልብ እንላለን፡፡… ‹አላህ ለሙስሊም ወንድምህ ምን ሠራህ ብሎ ይጠይቀኝ ይሆናል እንጂ ለኦሮሞው ምን ሠራህ ብሎ አይጠይቀኝም› እንዳለው አማኝ አክቲቪስት ዓይነቱ ግለሰብ የትኛውን ማንነቱን እንደሚያስቀድም አነጋጋሪም፣ አጠያያቂም አይደለም፤ ግልጽ ነው ማለቱ ይቀላል፡፡ እስልምና እንደ አንድ ሁሉን ጠቅልል የእምነት ዘይቤ በመሠረቱ ለማንኛውም ብሔርተኛ ዝንባሌ ራሱ ተግዳሮት ሆኖ ይቀርባል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛነትም እንዲሁ መጋፈጥ ያለበት ተፎካካሪ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የብሔረሰብ ማንነት ተቆናጦ የነበረውን ቦታ አሁን ደግሞ ሃይማኖታዊ ማንነት እየተቆጣጠረ መምጣቱን ልብ ማለት የግድ ተመራማሪ መሆን አያሻም እላለሁ፡፡ ይህ ደግሞ በተራው በኦሮሞ ብሔርተኝነት ላይ የራሱን ተፅእኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡

የግድ ነው ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ከላይ የተመለከትነው የቀድሞ የኦነግ ደጋፊ አክቲቪስት ዓይነቶቹ ብቻ አይደለም ለሙስሊማዊ ግደታቸው ቅድሚያ የሚሰጡት፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እስላማዊ መነቃቃትንና አዲሱን የሕዝበ ሙስሊሙ ማንነት ያለ ኦሮሞ ሙስሊም ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማሰቡ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛነት ከሃይማኖታዊ ሙስሊማዊ ማንነት ጋር ውድድር ውስጥ ገብቷል ማለትም ያስደፍራል፡፡ ከኦሮሞ ብሔረሰብ በምሥራቅና በምዕራብ የሚኖረው አብላጫው ክፍል በእምነቱ ሙስሊም ነው ብለናል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኛነት ከወቅታዊው የሙስሊም መነቃቃት ጋር ያለው ተያያዥነት፣ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንንም የግድ ከግምት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለብሔርተኞቹ አሉታዊ ጎን አያጣም፡፡ ቅድሚያ ለሃይማኖቱ ወይም ለዲኑ የሚሰጥ ከሆነ ግለሰቡ አገራዊ ወይም ብሔረሰባዊ ማንነቱ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ጫና ይኖራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ማንነት ላይ የበላይነት እየተቆናጠጠ መምጣቱን መካድ የማይቻል እውነታ ነው፡፡ እስልምና የአማኞቹን ወንድማማችነት ስለሚሰብክና ስለሚያስቀድም ሁለቱ ማለትም እምነትና ብሔርተኝነት አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት ይጣረሳሉ፤ ይወዳደራሉ ዲኔን (ሃይማኖቴን) አስቀድማለሁ፤ ብሔሬን አስቀድማለሁ በሚሉት መካከል በሚጧጧፈው ግብግብ ውስጥ እንበለው፡፡ እነዚህን አስታርቆ መጓዙ ፖለቲካዊ ብልህነትን ይጠይቃል፡፡ ከሁሉ አቀፍ ኦሮሞ ብሔርተኝነት ይልቅ የኡማው ወይም የሕዝበ ሙስሊሙን መብቶች ለማስከበሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ምእመን ደግሞ ለነጻ ኦሮሚያ መሥራቾች ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ መሰናክልም ነው፡፡ ከወቅታዊ የዓለማችን ችግሮች አንዱ ሆኖ የሚያተየውን የኢራቅን ኩርዶችን ብሔርተኛ ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰደው፡፡

ኩርዶቹ በእምነት እረገድ ልክ እንደ ኢራቅ ዓረብ ሙስሊብ ብቻ ሳይሆኑ ባመዛኙ ሱኒም ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ከዓረቦቹ አለያይ ስንጥቅ አድርገው የሚመለከቱት የኩርድ ቋንቋ ስብስብነታቸውን እንጂ ዛሬ ኢራቅ የተዘፈቀችበት የሱኒ-ሺዓ እርኩቻ አይመለከተንም ባዮች ናቸው፡፡ እዚያ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡም አይታዩም፡፡ በኢራቅ የሱኒ ሺዓ እርኩቻ ሃይማኖታዊ መገለጫዎች የኩርድ ብሔርተኛ እንቅስቃሴን አይመለከትም ማለት ነው፡፡ የኮርድ ብሔርተኞች አሰላለፍ አያሻማም ማለት ነው፤ በሌላ አባባል፡፡ በአገራችን የኦሮሞ ብሔርተኛ ኃይሎች ኦሮሞ በቋንቋ ስብስብነቱ ብቻ እንዲሰለፍ ሙከራ ሲያደርጉ ቢታዩም ቅሉ ይህንን አሰላለፍ መስመር ማስጠበቅ ስለመቻላቸው ርግጠኖች አይደለንም፡፡ የኢራቅ ኩርዶች የቋንቋ ስብስብነት ማንነት ቁልጭ ብሎ እንደሚገለጸው ይህ በአገራችን ኦሮሞ ብሔርተኛ አሰላለፍ ረገድ ግልጽ ሆኖ አይታይም፡፡ ፖለቲካንና ሃይማኖትን (ፖሊቲሳይዝ) እስልምና እና ብሔርተኝነት መካከል በበርካታ ቦታዎች የተከሰተ አለመጣጣም ነው እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡… ዛሬ ዛሬ፣ በአገራችን የሙስሊም ወገን ጥያቄና ቅሬታ ከጠቅላላው የኦሮሞ ቅሬታና የመብት ጥያቄዎች ጋር እየተመሰሰሉ የመጡበት ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ ይህን ደግሞ ለአገሪቱ አንድነት አሉታዊምም አዎንታዊምም ሊያሳርፍ የሚችል የእምነት ስብጥር አድርገን ነው የምንመለከተው፡፡

በቁጥር ደረጃ አመዛኙ የኦሮሞ ሕዝብ በሃይማኖቱ ሙስሊም ነው ብለናል፡፡ ከኦሮሞ የሙስሊም ድርሻ እስከ 65% ድረስ ነው አንዳንዶቹ፡፡ 47% ነው ይላል የማዕከላዊ እስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት አሐዝ፡፡ የእስላማዊ ሃይማኖት ማንነት መገለጫዎች የበላይነት እየተቆናጠጡ ከመጡ የኦሮሞን ብሔርተኛ እንቅስቃሴ የሚደግፍ አካሃድ ሊሆን አይችልም የሚል ግምት አለ፡፡ በሌላ በኩል ሙስሊማዊ ወገንተኛነት ወደ ሙስሊም ጠቅለል መንገሥት ምሥረታ ጥያቄና ትግል ያመራል የሚል ግምት የለም፡፡ ይህም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሕዝበ ሙስሊሙን አስገንጥዬ አዲስ አገር እመሠርታለሁ ባይ የሃይማኖት ፖለቲከኛ መኖሩ በእጅጉ አጣራጣሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች በአንድ መንግሥት ሥር ለመጠቅለል የሚታገል አደረጃጀት ይኖራል ብሎ ማሰብ መቼም አዳጋች ነው፤ ከኢትዮጵያ መገንጠልን እንደ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያነገበ ሙስሊማዊ ፖለቲካ ኃይል ይኖራል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ አገራዊነት የሕዝበ ሙስሊሙን መብት ለማጎናጸፍ መሞከር እንጂ፡፡ ይህን ማለት ግን ኡማው ወይም ሕዝበ ሙስሊሙን አንድ አድርጌ በአላህ ሕግ ደንብ አስተዳድራለሁ የሚል ምኞትም ሆነ ትልም በልቡ ያደረ ወገን ሊኖር አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ሊኖር ይችላል፡፡ የአብዛኛው ሕዝበ ሙስሊም ድጋፍ አሰባስቦ ዓላማውን እግቡ ማድረስ ይሳካለታል ወይ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው አጠራጣሪው፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው በአላህ ፊት የሚጠየቀው ለሕዝበ ሙስሊሙ ወገንህ ምን ዋልክለት ተብሎ እንጂ ለተወለደበት ስብስብ ወይም ብሔረሰብ ምን አደረግክለት በመባል እንዳልሆነ እስካላመነ ድረስ ቅድሚያ ታማኝነቱ ለየትኛው ማንነት መገለጫ እንደሚሆን አጠያያቂ አለመሆኑ ሥዕሉን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡ በሌላ በኩል በኢሕአዴግ መር ሥርዓት በብሔረሰብ እንጂ በሃይማኖት መደራጀት የተፈቀደ አይደለም፤ በሌላ አባባል ክልክል ነው፡፡ በሙስሊሙ ዙሪያ የምንመለከታቸው ሃይማኖታዊ መነቀቃቶች ባመዛኙ በትውልድ ወይም በብሔረሰብ ማንነት ኦሮሞ የሆነውን ሙስሊም ወገን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ እስላም ወይም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ለይቶ የማይመለከት እስላም ለማንኛውም የቋንቋ (ብሔረሰብ) ማንነት የስጋት ምንጭ መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ሐጂ ነጅብ መሐመድ ‹ኢስላም ከጎሣኛነት ጋር ሊጣመር አይችልም› በማለት በቅርቡ በሚኒሶታ የተናገሩት አቧራ አስረጅ ምሳሌ ነው፡፡ ይህ በተለይ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ላይ የደቀነው አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለአክራሪው ሙስሊም አማኝ፣ ወደ ገዳ ሥርዓት እመለሳለሁ ባይ ብሔርተኛ ኦሮሞ ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን በመሠረቱ የ‹ባዕድ አምልኮ› አቀንቃኝ ከመሆን አይዘልም፡፡ የኦሮሙማ ርዕዮተ ዓለም ከኢትዮጵያዊነት፣ ከሐበሻነት፣ ከአማራነት ብቻ ሳይሆን ከኢስላሙማ ጋርም ደጋግሞ ሲጋጭ መመልከታችን የሁለቱ ማንነት መገለጫዎች መጣረስ የሚያስከትለው አሳሳቢ አይቀሬ ውጤት ነው።

(ዩሱፍ ያሲን፣ ‹ኢትዮጵያዊነት፣ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት ›፣ 2009፣ ገጽ 254-267)


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE