ብሔርተኝነት፦ የለውጡ መንስዔ ብሎም እንቅፋት (በፍቃዱ ኃይሉ)

ብሔርተኝነት፦ የለውጡ መንስዔ ብሎም እንቅፋት

በፍቃዱ ኃይሉ
ብሔርተኝነት ዓለም ዐቀፍ ትኩሳት ነው። ብሔርተኝነት እና ማኅበራዊ ሚዲያ ሲገናኙ ደግሞ ትኩሳቱን የበለጠ እንዲፋጅ እያደረጉት ነው። በአሜሪካ ለዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ፣ ለእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት እና የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች መግነን የሚወቀሰው ማኅበራዊ ሚዲያ ያቀጣጠለው ብሔርተኝነት ነው። በኢትዮጵያም ካለፉት ዓመታት የቀጠለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተደማምሮበት፥ ዴሞክራሲያዊነትን ለመገንባት በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ብሔርተኝነት ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ ቆሟል።

ብሔርተኝነት እንደ ለውጥ መንስዔ
በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባን በዙሪያዋ ከሚገኙ የገበሬ ይዞታዎች ጋር የሚያስተሳስረው ‘ማስተር ፕላንን’ ተከትሎ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞም ይሁን በአማራ ክልል ‘የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ’ አባላት መታሰርን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ መሠረታቸው ብሔርተኝነት ነበር። ‘ማንነታችን፣ መሬታችን ይቀማል’ ወይም ‘ለኛ’ ይገባናል የሚሉ ጥያቄዎች የተቃውሞዎቹ ትርክቶች ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብሔርተኝነት በአደጉት አገራት ከምናየው የሚለየው፥ የብሔርተኝነት ፉክክሩ አገሪቱ ውስጥ ባሉት ብሔሮች እና የዘውግ ቡድኖች መካከል የሚደረግ በመሆኑ ነው። ስለሆነም በሁለቱም ክልሎች ውስጥ የነበሩት ተቃውሞዎች እና ሕዝባዊ አመፆች መነሻ ነጥቦቻቸው ድንገተኛ ክስተቶች ቢመስሉም የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ግን ሥር የሰደዱ እና በአንድ በኩል ‘ከማንነት ጋር የተያያዘ መገለል እና ጥቃት ደርሶብናል’ የሚሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‘ከአሁን የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ይገባናል’ የሚሉ ነበሩ።
ይህ በእንዲህ እያለ የሕወሓት የበላይነት ነበረበት የሚባለውን ገዢ ፓርቲ – ኢሕአዴግ የሚንጥ መከፋፈል በውስጡ የተከሰተው በሁለቱ ብሔርተኛ ድርጅቶች – የአሁኖቹ ኦዴፓ እና አዴፓ ጥምረት ነው። ጥምረቶቹ የመጡት ሁለቱ ድርጅቶች በክልላቸው የተሰማውን የተቃውሞ ድምፅ በመደገፋቸው ነው። ይህም ለድል አብቅቷቸዋል። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ወዲህ በተለይ የዘውግ ብሔርተኝነት (ethno-nationalism) እንዲቀዛቀዝ የተቻላቸውን ያክል መወትወት ይዘዋል። ነገር ግን የቀናቸው አይመስልም። የፖለቲካ ለውጡ ከተከሰተ ወዲህ የተከሰቱት ግጭቶች በሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ዘውግን መሠረት ያደረጉ (ብሔርተኛ) ናቸው።

የለውጡ መንስዔ፣ የለውጡ ተግዳሮት
በኢትዮጵያ ያለው የብሔርተኝነት ፉክክር፣ ባለፉት ዐሥርታት የነበረውን አፈና ለማስቆም ጥሩ መሣሪያ ሆኖ ቢያገለግልም፥ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋጋር የሚደረገውን ጥረት በግንባር ቀደምነት ይገዳደረዋል ብሎ መገመት አይቸግርም። አሁንም ምልክቶች እየታዩ ነው።
የፖለቲካ ለውጡ በይፋ ከታወጀ ወዲህ የለውጡ ባለቤትነትን ጨምሮ የለውጡ ተጠቃሚነት ጉዳይ የንትርክ እና የግጭት መንስዔ ሆኖ ታይቷል። የብሔርተኝነት ጥያቄ ለራስ ቡድን ከመወገንም በላይ ከሌላ ብሔር አንፃር የራስን ጉዳይ ማነፃፀርን ስለሚጨምር ፉክክሩ ግጭት ለመጫር ቅርብ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ፌዴራላዊ መዋቅርም ይሁን የብዙዎቹ ፖለቲካ ድርጅቶች አመሠራረት በዚሁ በብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን በእሳቱ ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ ሆኗል።
ከፖለቲካ ለውጡ በፊት ብሔርተኛ ድርጅቶች እርስበርስ ትብብር አሳይተው ነበር። የየክልሎቹ ገዢ ፓርቲዎች እና ተቃዋሚዎቻቸው አጋርነት ጀምረው ነበር። ሆኖም ለውጡ ከመጣ በኋላ ግን አጋርነታቸው ወደ ፉክክር ተመልሷል። የአንድ ክልል ብሔርተኞች ፉክክር ደግሞ እኔ የበለጠ ብሔርተኛ ነኝ የሚል በመሆኑ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለውን የጥላቻ እና ፀብ ጡዘት የበለጠ አጋንኖታል። በዚህ አካሔዱ ከቀጠለ (ይቀጥላል ብዬ እገምታለሁ) ብሔርተኝነቱ ያመጣውን ለውጥ እና ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ዕድል ራሱ ብሔርተኝነት መልሶ ይቀለብሰዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE