«ከኦነግ ጋር 16 ጊዜ ሽምግልና ቢካሄድም ውጤት አልተገኘም» – ኦዴፓ

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ(ኦዴፓ) ከኦነግ ጋር 16 ግዜ ሽምግልና ቢካሄድም ውጤት አልተገኘም ሲል ፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በቅርቡ የተሻለ ሁኔታ እንደሚመጣና ሰላምም እንደሚሰፍን ተስፋ አለኝ ብሏል፡፡የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል እየተስተዋለ ያለውን የሰላም መደፍረስ ችግር ከምንጩ በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መሥራት እንደሚገባ ገልጿል፡፡

የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታዬ ደንደኣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ዴሞክራሲውም ለጋና ህብረተሰቡም ለረዥም ጊዜ በትግል ላይ  የነበረ እንደመሆኑም በችግር ላይ ችግር እንዳይጫንበት በንግግር ችግሩን መፍታትና በምርጫው ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚቻልበትን ሥራ መሥራት ይገባል በሚል ችግሩን በውይይት ለመፍታትም 16 ጊዜ ሽምግልና መቀመጣቸውን፤ ስድስት ጊዜም ሠራዊቱ ወደ መንግሥት በሚገባበት ሂደት ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡

ኦነግ ግን  በእነርሱ ፍላጎት የሚሄድ ስላልመሰለው በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ባደረገው ጥረት ችግሮቹ መፈጠራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም መንግሥት ሕግ ማስከበር ግዴታው እንደመሆኑ ችግሩን ለህብረተሰቡ የማሳወቅ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በጅማ፣ በሻሸመኔ፣ በአዳማ፣ በአምቦ እንዲሁም በአዲስ አበባ በቤተ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ የህዝብ ውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን፤ በእነዚህ ሰፋፊ የህዝብ መድረኮችም ችግሮችን ለህዝቡ በመገለጹ፣ እየተካሄደ ያለውን መጥፎ ድርጊትና በመንግሥት የሄደበትን ርቀትም ማስረዳት በመቻሉ ህዝቡ ችግሩን በመረዳት የህግ የበላይነት እንዲከበር መጠየቁን ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥትም በህዝቡ ጥያቄና ፍላጎት መሰረት በማድረግ የጀመረውን ችግሩን የመፍታት ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ታዬ እንዳሉት፤ ችግሩ የመጣው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አንጻር አይደለም፡፡ ምክንያቱም በክልሉ በርካታ ፓርቲዎች የመኖራቸውን ያክል ሁሉም ሕግና ስርዓትን አክብረው በሰላም የፖለቲካ ሥራቸውን እየሠሩ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራቸውም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

እንደ አቶ ታዬ ገለጻ፤ ኦነግ በአንድ በኩል ሰላማዊ ውይይትን እከተላለሁ ይላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖችን እየከፈተ የ12 ዓመት ሕፃናትን ሳይቀር እያሰለጠነ፤ ብሎም የተስማማነው አልተደረገልንም በማለት ሕብረተሰቡንም በማደናገር ለዓላማው ማስፈጸሚያ እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የተደረሰው ስምምነት ሁሉም ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን በማክበርና የትጥቅ ትግሉን በመተው በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲወዳደሩ፤ በዚህም ካሸነፉ ስልጣን እንዲይዙ፣ ከተሸነፉም ውጤቱን በጸጋ ተቀብሎ ለሌላ ጊዜ እንዲወዳደሩ ነው፡፡ የዚህን ፓርቲ ሠራዊት በተመለከተም መንግሥት ተቀብሎ እንደ ብቃትና ፍላጎታቸው በፖሊስ ሠራዊቱና በክልሉ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ለማቀፍ፤ በዚህ ውስጥ ለመታቀፍ ብቃቱና ፍላጎቱ የሌላቸውንም ድጋፍ ተደርጎላቸው የራሳቸውን ሕይወት የሚመሩበት ዕድል እንዲፈጠርላቸው ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ከኤርትራ የመጡ 1ሺ300 የሠራዊቱ አባላት ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ደግሞ 700 ያህሉን ወደ ክልል ፖሊስ እንዲሳተፉ ተደርጓል፤ የተቀሩትንም ስልጠና በመስጠትና የድጋፍ በጀት በማዘጋጀት በትውልድ ቦታቸው ሄደው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ከተደረሰው ስምምነት የቀረም፣ የጎደለም ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲው የራሱን የተደበቀ ዓላማ በመያዝና ህዝቡንም በማደናገርና ብዥታ እንዲፈጠርበት የተስማማነው አልተፈጸመም በሚል እየተንቀሳቀሰ ነው ለዚህ ያደረሰው ብለዋል፡፡

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲልም በአካባቢው የተረጋጋ ሁኔታ እንዳልነበረና ከግንባሩ ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ በመሆኑ በቅርቡ የተሻለ ሁኔታ እንደሚመጣና ሰላምም እንደሚሰፍን ያላቸውን  ተስፋ ገልጸዋል፡፡

አቶ ቶሌራ  እንደሚሉት፤ ግንባሩ በሰላም ለመታገል ወደ አገር ቤት ከገባ የሰነበተ ቢሆንም፤ በወለጋ አካባቢ በተለይም በምዕራብ ወለጋ ተከሰቱ የተባሉት የሰላም ችግሮች ግን ኦነግ ወደ አገር ቤት ከመምጣቱ በፊት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል የነበረ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ተባብሶ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ተፈናቅሏል፡፡ በዚህ ምክንያት በአካባቢው የተረጋጋ ሁኔታ አይታይም፡፡

በሌላ በኩል ኦነግ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ በአካባቢው የነበረው የግንባሩ ሠራዊት በአካባቢው ከነበረው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጋር በየጊዜው ግጭቶች ነበሩ፡፡ ይሄንንም ቢሆን ከመንግሥት ጋር በየጊዜው እየተመካከርን ሁኔታዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲሄዱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሚጠበቀውና ህዝቡም በሚፈልገው መጠን ሰላም ለማስፈን አልተቻለም፡፡

እንደ አቶ ቶሌራ ገለጻ፤ ኦነግ እያሰለጠነ ያለው ሠራዊት የለም፤ ግንባሩ አንድን ሰው አባል ለማድረግም ቢያንስ 18 ዓመት የሞላው መሆን የግድ እንደመሆኑም ሕፃናትን ለውትድርና እያሰለጠነ አይደለም፡፡

ከኤርትራ የገቡትን የግንባሩ ወታደሮችን በተመለከተም በአካል ማረጋገጥ ባይችሉም የተወሰኑት በመንግሥት መዋቅር እንዲገቡ፣ የተቀሩትም ተደግፈው የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ መደረጉን በመገናኛ ብዙሃን ሰምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ እልባት ያልተገኘለትና ግጭትም እያስከተለ ያለው በግንባሩ እየተመራ ወለጋ ውስጥ ያለው ሠራዊት ወደመንግሥት የጸጥታ ኃይል ውስጥ እንዴት መግባት አለበት የሚለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አሁንም ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር ውይይቶችን እያደረጉና ግጭቶችንም እየፈቱ ሲሆን፤ የተሻለ ሁኔታ እንደሚመጣና ሰላምም እንደሚሰፍን ተስፋ እንዳለቸው ጠቁመው፣  በአካባቢውም ሰላም እንዲሰፍንና ህብረተሰቡም የተረጋጋ ኑሮውን እንዲኖር መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና እንደተናገሩት፤ በክልሉ እየተስተዋለ ያለው የሰላም ችግር ከመቀነስ ይልቅ እየሰፋ ያለ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ጥቂት ቁማርተኞችን የሚጠቅም ሰፊውን ህዝብ የሚጎዳ እንደመሆኑ የችግሩን ምንጭ ለይቶ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡

እንደ ዶክተር መረራ ገለጻ፤ ፓርቲያቸው ችግሮች በተገቢው መንገድ እንዲፈቱ የሚችለውን ያክል ጥረት አድርጓል፡፡ ህብረተሰቡም ችግሮቹ በሰላም እንዲፈቱለት ይፈልጋል፡፡ ሆኖም የችግሩ ምንጭና ባለቤት እኔነኝ ባይ በመጥፋቱና ሁሉም ከራሱ ላይ ማሸሽ በመኖሩ ችግሩ ከመቃለል ይልቅ እየሰፋ ሄዷል፡፡ በየትኛውም አግባብ ደግሞ ግጭት ተገቢ ነው ተብሎ የሚወሰድበት ምክንያት የለውም፡፡ ምክንያቱም በግጭት እንቅስቃሴ ውስጥ የተወሰነ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልግ ኃይል ይንቀሳቀሳል፡፡ ከግጭት የሚያተርፈውም ወንበዴ እንደመሆኑ ግጭቱ እንዴትና ለምን መጣ የሚለው መታየትና የግጭቶቹ ምንጭ ታውቆ ለመፍትሔው መሠራት አለበት፡፡

ሕዝቡም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ በተለይም ይሄን ችግር የማቃለል ኃላፊነት ያለበት መንግሥት የችግሩን ምንጭ መለየትና ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ በሂደቱም በሆደ ሰፊነት ነገሮችን መመልከትና ግጭቶቹም ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆኑ፣ የዜጎችን ሕይወት እንዳይቀጥፉ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 3/2011


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE