የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀይል መዋዠቅ የተነሳ የማምረቻ መሳሪያዎቻቸው ከጥቅም ውጪ እየሆኑባቸው ነው

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት መቸገራቸው ተነገረ፡፡

በዚህም የተነሳ የአቅማቸውን ያህል እያመረቱ አይደለም ተብሏል፡፡

በሀይል መዋዠቅ የተነሳ የማምረቻ መሳሪያዎቻቸው ከጥቅም ውጪ እየሆኑባቸው መሆኑን ሰምተናል፡፡

ያለው የሀይል አቅርቦትና የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ተመጣጣኝ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከከፍተኛ ሀይል ተጠቃሚዎች ጋር ውይይት ሲያደርግ ሰምተናል፡፡

ከተለያዩ ፋብሪካዎች የተገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎች በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ለብልሽት የሚዳረጉ የማምረቻ መሳሪያዎች ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡
እስካሁን ድረስም የካሳ አከፋፈል ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ለኪሳራ መዳረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በራሳቸው ወጪ ለማስጠገንም የውጪ ምንዛሪ እጦት እክል እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍም ዳግም ቢፈተሽ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡርም በተደጋጋሚ የሀይል እጥረት እንደሚያጋጥመው ተናግሯል፡፡

በዚህም ምክንያት የትራንስፖርት ሥርዓቱ እየተስተጓጎለ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ ከደንበኞች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሰራለን ብለዋል፡፡

መስሪያ ቤታቸው ለተነሱት የሀይል ችግሮች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማበጀትና ለኢንዱስትሪ የሚመጥን ሀይል ለማቅረብ የሀይል ማመንጫዎችንና ማሰራጫዎችን እያስገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Sheger FM


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE