በደቡብ ክልል በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ከሃያ ሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

DW  : ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በወረዳው አንገላ ቀበሌ ውስጥ ሰላሳ ሁለት ሰዎች ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ተፈናቃዮቹ መንግሥት በነደፈው የግብርና ሠፈራ ፕሮግራም አማካኝነት ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት ከከንባታ ጠንባሮ ዞን ወደ ከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በመሰፈር በግብርና ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡

በደቡብ ክልል የከፋ ዞን በሚገኘው ዴቻ ወረዳ በመፈናቀል ወደ ከንባታ ጠንባሮ ዞን የገቡት ነዋሪዎች ቁጥራቸው ከሃያ ከሁለት ሺህ በላይ እንደሚገመት ይነገራል ፡፡ ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ አንገላ ቀበሌ የሰፈሩት የደቡብ ክልል መንግሥት በነደፈው የግብርና ሠፈራ ፕሮግራም አማካኝነት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በእነኝህ ዓመታት አልፎ አልፎ በታጠቁ ቡድኖች ሲያጋጥማቸው ከነበረው የከብት ዘረፋ በስተቀር የግብርና ሥራቸውን በሰላም ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም፣ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ባልተለመደ መልኩ በታጠቁ ቡድኖች የሚፈጸሙ የግድያና የዘረፋ ተግባራት እየተባባሱ በመምጣቸው አካባቢውን ጥለው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ተፈናቅለው በከንባታ ዞን ደንቦያ ወረዳ እንደሚገኙ የሚናገሩት ዴቢሳ አዳሮ በጥቃቱ ከተፈናቀሉት በተጨማሪ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ባል ሚስትና ህጻናትን ጨምሮ በተለያዩ ሰዎች ላይ አሰቃቂ የግድያ ተግባር መፈጸሙን ነው ለዲ ደብሊው የገለጹት፡፡

በከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ከመጡ በኋላ በግብርና ሥራ ባደረጉት ጥረት በሞዴል አርሶአደርነት እስከመሸለም ደርሼ ነበር የሚሉት ሌላው ተፈናቃይ አርሶ አደር ማርቆስ ጫኪሶ በበኩላቸው ከዘራፊዎች ጥቃት ለማምለጥ አስከዛሬ የፈሩትን ቋሚና ተንቀሳቃሽ ሀብት ጥለው ከአካባቢው መሸሻቸውን ገልጸዋል፡፡
የከንባታ ጠንባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ታከለ ነጮ በወረዳው በተፈጸመው ጥቃት እስከአሁን ሰላሳ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ ከሃያ ሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን በስልክ ለDW  ተናግረዋል፡፡

Äthiopien - Vertriebene Kembata Völker in Keffa Zone (DW/S. Wegayehu) በተለይም በጥቃቱ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ህጻናትን ጨምሮ የተለያዩ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ተፈናቃዮች በዞኑ መስተዳድር በኩል የህክምናና ተያያዥ ድጋፎች በመደረግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡  አሁን የሚታየውን መፈናቀል ለማስቆምና በቀጣይ መደረግ ያለበትን ሁኔታ ለመገምገም ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ቡድንም ወደ አካባቢው መንቀሳቀሱን አመልክተዋል፡፡
በደቡብ ክልል የሰፈራ ፕሮግራም በተካሄደባቸው የቤንች ማጂና የከፋ ዞኖች በሠፋሪ አርሶአደሮች ላይ የመፈናቀል አደጋ ሲያጋጥም የአሁኑ መጀመሪያው አይደለም፡፡
ከዛሬ ስምንት ዓመታት በፊትም ከአማራ ክልል በመምጣት ጉራ ፈርዳ በተባለ አካባቢ ሰፍረው በነበሩ ነዋሪዎች ላይ ተመሳሳይ የመፈናቀል ጥቃት መፈጸሙ አይዘነጋም ፡፡

► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE