የሸዋ ጥያቄ – ተስፋዬ መኮንን

በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች ፊታውራሪነት የተዘጋጀውና የፀደቀው የሽግግር ቻርተርም ሆነ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተቀዳሚ ዓላማ፣ በ1960ዎቹ ሲቀነቀን የነበረውን ታሪካዊ መሠረት የሌለው የብሔር ብሔረሰብ ትርክት መሠረት በማድረግ፣ ጨቋኝ ተብሎ የተፈረጀውን አማራ ማሳነስ ነው፡፡ የሕወሓትና ኦነግ መሪዎችና ሌሎች የኢትዮጵያን የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ በቅጡ ያልመረመሩ ኀይሎች እንደያወሩለት የዚህ ሕገ መንግሥት ዋና ዓላማ የሕዝቦችን እኩልነት ማረጋገጥና ዲሞክራሲያዊ አንድነትን አይደለም፤ አማራውን በሕዝብ ቁጥር (ዲሞግራፊ) እና በግዛት (ጆግራፊ) ማሳነስ ነው፡፡

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የታየው እውነታ እንዳረጋገጠው ይህ በመሠረተ-ቢስ ትርክት ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ ነገዶች መካከል እጅግ አደገኛ መጠራጠርና ግጭት ፈጥሯል፤ ሕዝብ በነጻነት መክሮና ዘክሮ ያፀደቀው ሕገ መንግሥት እስከሌለ ድረስ አሁን በተያዘው መንገድ ከቀጠልን አገራችን ወደከፋ መከራና የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባ የምትችልበት ዕድልም በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሦስት ዐሥርት ለሚጠጉ ዓመታት እንዳነው ከዚህ ሕገ መንግሥት ያተረፍነው የኢትዮጵያዊያንን መፈናቀልና መሳደድ ነው፤ የምንታዘበው የማያባራ ግጭት ነው፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ እስካለ ድረስ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ይቀጥላል፡፡ በመሬት ይገባኛል ምክንያት እየተከሰተ ያለው የዜጎች ስደትና ሞት አይቆምም፤ እንዲያውም በግልጽ እንደሚታየው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ በውሸት ትርክትና በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን ግጭት ፈልፋይ አወቃቀር ከሥረ መሠረቱ መቀየር ነው፡፡ ከዚያ መለስ ያለው እርምጃ ሁሉ ጊዜያዊ ማስታገሻ ካልሆነ በስተቀር ሀገርና ሕዝብ በዘላቂነት የሚጠቀሙበት መፍትሔ አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው መቶ በመቶ በኢሕአዴግና አጋሮቹ የተያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ የማንነትና አስተዳደራዊ ኮሚሽንን በአዋጅ አቋቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ በየአካባቢው በማንነትና ወሰን ጉዳዮች የሚነሱ ጥያቄዎችን እያጠና የመፍትሔ ምክረ-ሐሳብ የሚያቀርባና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመሆን የሚያስፈፅም ነው ተብሏል፡፡ በእኔ አስተያየት በተሳሳተ ትርክት በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች በዚህ ኮሚሽን አማካይነት ሊፈቱ ባይችሉም፣ ዘላቂ መፍትሔዎችን በመጠቆም ረገድ የራሱ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ፣ ይህ ኮሚሽን ሕዝበ-ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውንና ሕዝበ-ውሳኔ ሳያስፈልግ መታጠፍ ያለባቸውን አካባቢዎች በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪዎች የወልቃይት ጠገዴን መሬት ነባሩን ሕዝብ በመመንጠርና የራሳቸውን ታጋይና የቀን ሠራተኞች እንዳሰፈሩበት በግልጽ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባ ሐቅ አለ፤ ወልቃይት ጠገዴ ላይ ከየትኛውም የአገራችን አካባቢ በከፋ መልኩ በመንግሥት የተቀነባበረ ዘር መንጠራ ተካሂዷል፡፡ ነባሩ ሕዝብ ተመንጥሯል፡፡ ለዚህ አስከፊ ወንጀል ኀላፊነት የሚወስዱት ደግሞ ከሕወሓት የለቀቁትም ይሁኑ አሁንም ድርጅቱን የሚመሩት ግፈኛ የድርጅቱ መሪዎች፣ እንዲሁም የእነሱን ጉዳይ ሲያስፈፅሙ የነበሩት እንደ አዲሱ ለገሰና በረከት ስምኦን ያሉ የብአዴን መሪዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ ኮሚሽን ወልቃይት ጠገዴ ላይ የተከሰተውን ዘግናኝ ወንጀል በሚገባ መርምሮ ይህን ወንጀል የፈፀሙና ያስፈፀሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባዋል፡፡ በአገራችን በየትኛውም አካባቢ፣ በየትኛውም ሕዝብ ላይ ግፍ ሊፈፀም አይገባም የሚል እምነት ያለው የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፣ ምሁር፣ የሃይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌ ሁሉ ወልቃይት ጠገዴ ላይ በሕወሓት መሪዎች ፊታውራሪነት የተፈፀመውን ኢሰብአዊ ድርጊትና የሕዝብ ምንጠራ በማያሻማ ቃል ማውገዝ ይጠበቅበታል፡፡

በሌላ በኩል ከወንጀለኞች በቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር/አማራ ታሪካዊ ግዛት መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቀውና ሐቁም እሱ ስለሆነ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ነባር ማንነቱ እንዲመለስ ያስፈልጋል፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ሳይመለስ በትግራይና በአማራ ሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ይፈጠራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ወደ ቀልባቸው ከተመለሱ ይህን ሐቅ የሕወሓት መሪዎችም ሊስቱት አይችሉም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አማራውን በመሬትም በሕዝብ ቁጥርም ለማሳነስ በተቀየሰው በሕገ መንግሥት በተደገፈ እርምጃ ምክንያት የተወሰዱት ራያና መተከልም ወደ ነባር ይዞታቸው መመለስ ይገባቸዋል፡፡ ራያና መተከል ላይ ሕዝበ-ውሳኔ ብሎ ነገር ቀልድ ነው፡፡ ስለ ሕዝበ ውሳኔ መወራት ያለበት አናሳውን መብት ለማስከበር ሲባል ብዙሃኑ በርስቱ በአስከፊ ጭቆና ውስጥ እንዲገባ ስለተደረገበት ኬሚሴ ነው፡፡ የነገዶችን በቋንቋቸው የመጠቀም መበት አስከብራለሁ የሚለው ሕወሓትና ኦነግ ሥርዓት ለአማሮች ሲሆን አይሠራም፡፡ ኬሚሴ ላይ ያለውን እጅግ አሳዛኝና በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለው ሁኔታ መመልከት በቂ ነው፡፡ ስለሆነም የተቋቋመው ኮሚሽን ኬሚሴ ላይ ሕዝበ-ውሳኔ የሚደረግበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

ሸዋ እና ኢትዮጵያ
****
ባዕዳን የኢትዮጵያ ጠላቶችም፣ የኢትዮጵያ የትንሽነት ኀይሎችም ሸዋን በሚመለከት የሚጋሩት ነገር አለ፡፡ ሁሉም ሸዋን በከፍተኛ ጥርጣሬና ጥላቻ ነው የሚያዩት፡፡ ሁሉም ሰንድ አዘጋጅተው ዘምተውበታል፡፡ ስለ “አንኮበርና አንጎለላ ሥነ-ልቦና” ብዙ ጽፈዋል፤ ሸዋ ስለሚዳከምበት ሁኔታ የተቀናጀ ዘመቻ አድርገዋል፡፡ አሁንም አልቆመም፡፡
የዚህ ሁሉ ውርጅብኝ ምክንያቱ በሚገባ ይታወቃል፤ ሸዋ የመካከለኛውና የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እምበርት ስለሆነች ነው፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አርክቴክቶች የዚህ አካባቢ መሪዎች ስለሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ምክንያቱ ይህ ብቻ አይደለም፤ ከዚህም በእጅጉ ይሰፋል፡፡ ሸዋ አማራው፣ የጉራጌው፣ የኦሮሞው፣ የሃድያው፣ የከምባታው፣ የየሙና የሌላውም ነገድ ውሕድና ኅብር ስለሆነች ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ማሳነስና ማዳከም የሚፈልግ ማንኛውም ኀይል ሸዋን ማሳነስና ማዳከም ይፈልጋል፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሰነድ አዘጋጅተው ከተማሪ እስከ ፕሮፌሰር፣ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበር አባላት ስለ ሸዋ እኩይነት አሰልጥነዋል፡፡ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው የዚህ ሁሉ የጥፋት ተግባር ዋና ዓላመው ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ምልክት የሆነችውን ሸዋን ማሳነስና ማዳከም አስፈላጊ ነው የሚል ስትራቴጅ ስላላቸው ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ኦሮሚያን እንመሠርታለን የሚለው ኦነግና የእሱን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ኀይሎችም ሸዋን ለማሳነስና ለማዳከም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ የእነሱን አካሄድ ለየት የሚያደርገው የማሳነስና የማዳከሙ ሥራ መልኩን ቀይሮና የሸዋን ኅብር አጥፍቶ ኦሮሞ በማድረግ የሚገለጽ መሆኑ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም የሚጨነቅ ከሆነ፣ የሸዋን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ ሊያጤነውና መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሸዋ ውስጥ የማይኖር ነገድ ስለሌለ፣ በዚህና ለአገረ መንግሥት ግንባታ ባደረገችው ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ ምክንያት፣ ሸዋ የኢትዮጵያ ቀንዲል ስለሆነች፣ በልዩ ሁኔታ ታይታ የራሷ አስተዳደራዊ ግዛት እንዲኖራት ማድረግ ይገባል፡፡