ከታዘለበት አንቀልባ አልወርድ ያለው የሶማሊ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶህዴፓ) ! (RAJO)

ከታዘለበት አንቀልባ አልወርድ ያለው የሶማሊ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶህዴፓ) ! (RAJO)


ቀድሞውኑ እራሱን ችሎ ህልውና ያልነበረውና ዛሬ ላይ ግዜ ከድቷቸው መቐለ ላይ የመሸጉት የህወሃት አጁዛዎች የራሳቸውን የፓለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስፈጸም እንዲችሉ ቀርፀው ባዘጋጁለት የፖለቲካ ፕሮግራም በህወሃት አንቀልባ ታዝሎ የይስሙላ መሪ ፓርቲ ሆኖ ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት የሶማሊ ክልልን በህወሃት የጦር ጄኔራሎች ሞግዚትነት ስር እንዲውል የሶማሊ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶህዴፓ) የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይሁንና የክልሉ ህዝብ በከፈለው መስዋእትነት ቀንደኛ የህወሃት ሎሌ የነበረውን አብዲ ዒሌና ግብረ አበሮቹ ከክልል መስተዳድሩ ስልጣን እንዲወገዱና የሶማሊ ህዝብም ከሞግዚት አስተዳደር ተላቆ የለውጡ ተቋዳሽ እንዲሆን የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ጅማሮዎች እየታዩ ቢሆንም ነገር ግን ከዚህ ቀደም የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ የነበሩና በክልሉ ተንሰራፍቶ ለነበረው የሙስናና ብልሹ አስተዳደር ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ቡድኖች ፓርቲው በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እራሳቸውን በአዲስ መልክ አደራጅተው ወደ ስልጣን ለመምጣት እንዲችሉ እያደረጉ ያሉት ሰፊ እንቅስቃሴ በክልሉ የተጀመረውን የለውጥ ጅማሮ ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡

በዚህ ረገድ የሶማሊ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶህዴፓ) ምንም እንኳን የአንድ ፓርቲ ጥንካሬ መለኪያ ፓርቲው በሚመራው ህዝብ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አላማ ላይ ተመስርቶ ከተቀረጸው የፖለቲካ ፕሮግራሙ በተጨማሪ የፓርቲው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ የሚመራበት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና መመሪያ ተግባራዊነት ቢሆንም ነገር ግን ሶህዴፓን ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት በከፍተኛ አመራርነት ሲመሩ የነበሩት ኃላፊዎች የፓርቲው አባላት በሚያነሷቸው ትችት እና ጥቆማ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አካሄድና በፓርቲው ደንብ እና በመመሪያ ላይ በተደነገገው መሠረት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ሁሉም የየራሱን የግል ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ እርስ በእርሳቸው ከመሻኮት የዘለለ ለክልሉ ህዝብ የፈየዱት አንዳች ፋይዳ አልነበረም፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ በፓርቲው ዘንድ የአሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነት አለመኖር አንዱና ዋነኛው ችግር ሲሆን በገንዘብ አሰባሰብ እና አወጣጥ፣ በውሳኔ አሰጣጥ፣ የስልጣን ተዋረድ እና የመሳሰሉት ግልፅ ያለመሆናቸው በተለይ ደግሞ አብዛኛው የፓርቲ ሥራዎች በተወሰኑ የጥቅም ቁርኝት ባለቸው ሰዎች ጥብቅ ትስስር መከናወናቸው የአሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነትን ከማሳጣቱ በተጨማሪ የፓርቲው አባላት በሚታዩት ችግሮች ላይ የተቀናጀ የጋራ ትግል እንዳያደርጉ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፓርቲው የሚከናወነውን የስራ ድልድል እና ሃላፊነትን በተመለከተ በፓርቲው የሃላፊነት ቦታ ላይ ለመሰየም ብቁ የሚያደርጉ መስፈርቶች እና በፓርቲው ከተሰየሙበት የሥራ ሃላፊነት ለመነሳት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን አስመልክቶ በፓርቲው ደንብ እና መመሪያ የተቀመጠ ቢሆንም ምንም አይነት የትምህርት ብቃትና ችሎታ የሌላቸው፤ በሙስና የተዘፈቁ እንዲሁም ለፓርቲው ያደረጉት አስተዋጽኦ እንዴት እና በምን መልኩ እንደሆነ ሳይታወቅ ወይም ፓርቲን መሠረት ያላደረገ የግለሰቦችን ፍላጎት የሚያረካ ሹመት እና ሽረት ሲካሄድ ይስተዋላል፡፡

ስለዚህ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የሶማሊ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶህዴፓ) የሚገኝበትን አቋምና እንዲሁም እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ሲታይ በሶማሊ ክልል የተጀመረውን በጎና ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጅማሮዎች ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ስለሆነ በክልሉ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ቀጣይነት እንዲኖረው ፓርቲው በአዲስ የለውጥ ሃይል መደራጀት ይኖርበታል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE