ለጋራ አሸናፊነት እንተባበር እንጅ ለውድቀት አንጠላለፍ

“ለጋራ አሸናፊነት እንተባበር እንጅ ለውድቀት አንጠላለፍ”

(የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ወቅታዊ መልእክት)
ታህሣሥ 27 ቀን 2011 ዓ.ም

አሁን ባለንበት ቅጽበት ሀገራችን በለውጥ ተስፋና በእርስ በርስ የግጭት ስጋት ተወጥራ በመንታ መንገድ ላይ ትገኛለች ለማለት ይቻላል። በሕዝብ የለውጥ ፍላጎትና ትግል ተገፍቶ ከውስጥ በመንግሥታዊ አካሉም ጭምር ተቀባይነት ያገኘውና በተግባር እየተሄደበት ያለው የሁለንተናዊ ለውጥ ጉዞ ለሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ ለክልላችን የተስፋ ብርሃንን አሳይቷል። እርስ በርስ ተጠፋፍተን ሀገር ትበተናለች ወደሚል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባንበት ጊዜ አልፎ ለሀገር ሌላ ዕድል ተሰጥቷታል። ይህን ዕድል ተጠቅመን ተስፋውን ማለምለም የምንችለው ግን ስንደማመጥ፣ ስንግባባ፣ ስንከባበርና ስንተባበር እንጅ አሁንም በሴራና በመጠላለፍ መንገድ ስንጓዝ አይደለም። ልዩነቶቻችንን አክብረን መግባባት እንችላለን። በሁሉም ነገር የግድ መግባባትም መስማማትም አይጠበቅብንም። ነገር ግን ተፈጥሯዊ የሆነውን ልዩነት ማክበርና በልዩነትም መስማማት ግድ ይለናል። ምክንያቱም እስከልዩነታችንም ቢሆን በጋራ ለመኖር ካልተስማማን እንጠፋፋለን እንጅ ልዩነትን ማጥፋት አይቻለንምና። ልዩነት ተፈጥሯዊ ነውና ልናስወግደው ከቶውኑ አይቻለንም። ልናስወግደው ካልቻልን ብቸኛው ምርጫችን አክብረነው መኖር ነው። ልዩነትን ከማክበርም አልፈን ውበትና ጸጋ ልናደርገው የምንችለው በመጀመሪያ ሰከን ብለን መነጋገር፣ መደማመጥና መግባባት ስንችል ነው። የራሳችን ሐሳብ ብቻ ተደማጭና አሸናፊ ይሁን ካልን መቼም አንግባባም።

ምርጫችን ሁለት ነው። ወይ በልዩነትም ውስጥ ተስማምተንና ተከባብረን መቀጠል ወይም ልናስወግደው የማንችልን በሰው ልጆች ዘንድ ተፈጥሯዊ የሆነን ልዩነት ባለማክበርና አንዱን አንዱ ለማጥፋት ባለመ ትግል ተጠላልፈን በጋራ መውደቅ። ከዚህ የተለየ አማራጭ ያለን አይመስልም። ሀገራችን ከሶስት ሺህ ዘመናት በላይ ተጉዛና እስካሁን ቀጥላ ያገኘናት ልዩነት ስላልነበረና ሁሉም አንድ አይነት ሐሳብና ፍላጎት ስለነበረው አይደለም። አባቶቻችን ልዩነትን አቻችለው መጓዝ ስለቻሉበት እንጅ። እኛም ሀገርን እስከሙሉ ነፃነትና ክብሯ ጠብቀው ካስረከቡልን አባቶቻችን በልዩነት ውስጥ ተከባብሮ ብቻ ሳይሆን ተፋቅሮም የመኖር ጥበብን ልንማር ይገባል። አባቶቻችን ምክንያት እየፈለጉ በሆነ ባልሆነው መጣላትና መገዳደል ቢፈልጉ ኖሮ ሀገርን ማቆየት አይቻላቸውም ነበር። ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የየራሳቸው ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነትና ሌላም መገለጫ ያላቸውን ሕዝቦች አቅፋ እዚህ እንድትደርስ ያደረገው የአባቶቻችን ጥበብ ልዩ ነው። እርሱም በልዩነት ውስጥ ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ነው። ይህን አለማወቅ ካለማወቅ ሁሉ ይከፋል። ይህን አለማክበር ክብር ያሳጣል። ይህን አለመተግበር ሕልውናን ይፈታተናል። ሀገር በጥበብ እንጅ በስሜትና በእልህ አትመራም።

በሰከነ መንፈስ ከተነጋገርን፣ በመደማመጥ ከተግባባን፣ በልዩነትም ውስጥ ከተስማማን፣ የተጀመረው የተስፋን ብርሃን ሀገራችንን ሆነ ክልላችንን የሚጠቅም ሆኖ ይቀጥላል። ልዩነትን ማስፋትና መጠላለፍ ላይ ካተኮርን ደግሞ ጭላንጭል ብርሃኑን አጥፍተን የውድቀት ታሪክ እንቀጥላለን። ይህ እንዲሆን ግን በፍጹም መፍቀድ የለብንም። ለውጡ ከሕዝቡ የመጣና በሕዝቡም የሚፈለግ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባውም። ከሕዝብ የመጣን ለውጥ ደግሞ ምንም ዓይነት ኃይል ሊያስቆመው አይችልም። የትኛውም የጥፋት ሙከራ ሕዝባዊ ለውጥን አይረብሽም ማለት ባይቻልም ሊያስቆመው ግን ፈጽሞ አይችልም። ሕዝባዊ መሠረት ያለውን ለውጥ ማስቆም ማለት ሕዝብን ማጥፋት እንደማለት ነው። ሕዝብን ማጥፋትም ሆነ ከጉዞው ማስቆም የሚችል ኃይል አይኖርም። ታሪክም ይህን አይነግረንም።

እንደ አማራ ክልልና ሕዝብ ይህን ጅምርና ተስፋ ሰጭ የለውጥ ጉዞ በጋራ ከማስቀጠል የተሻለ አማራጭ የለም። ምንም ለውጥ የለም ማለትም ጨለምተኝነት ነው የሚሆነው። እርግጥ ነው ለውጡ በሚፈለገው መልኩ አልመጣም። ለውጡን በተሻለ መልኩ ለማስኬድ አማጮች አሉኝ የሚል አካል ካለም ተቀራርቦ መነጋገርና መግባባት ይቻላል እንጅ እንደተለመደው በተጠፋፊነት ስሜት መጓዝ ለሕዝቡ ጠብ የሚል ውጤት አያመጣም። የአማራ ሕዝብ ሌላ የመጠላለፍና የመጠፋፋት ዘመንን አይሻም። ሌላ መከራን የሚሸከምበት ትክሻም የለውም።
ይህ ሕዝብ ልዩነትን የማስተናገድ ችግር የለበትም። ልዩነትን ከማክበርም አልፎ ማፍቀርን በተግባር ያሳየ ሕዝብ ነው። በአማራ ክልል ውስጥ በተንኮል የተጠነሰሰ የጥፋት እጅ ያደራጀው ካልሆነ በቀር በልዩ ማንነቱም ሆነ በልዩ ሐሳቡ “በሕዝቡም” ሆነ በሌላ “የአማራ” ኃይል ተገፋሁ የሚል አካል የለም። ማንም ልዩ/ድርብ ማንነት አለኝ የሚል አካል የሆነውን ሆኖ ይኖር ዘንድ ብቻ ሳይሆን ራሱን በራሱ እንዲያስተደድርም ጭምር ተፈጥሯዊ መብቱን ያከበረና ምን አልባትም ሊጠቀሙበት ከቻሉ ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆን ልዩነትን የማስተናገድ ልምድ ያለው ሕዝብ/ክልል ነው። በአማራ ዘንድ መብት ጠያቂም ሆነ ሰጭ ወይም ከልካይ የለም። ሁሉም ተፈጥሯዊ መብቱ ተከብሮለት ይኖራል እንጅ። ይህን ሐቅ ወደ ጎን ብሎ ማሩን በማምረርና ወተቱን በማጥቆር የሚደረግ ወቀሳም ሆነ ውንጀላ የአማራን መልካም ነገር ለማየት ካለመፈለግ የጥላቻ መንፈስ የመነጨ ነው የሚሆነው።

ካሁን በፊት በክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም ጭምር ተደጋግሞ እንደተገለጸው አማራ አንገት ደፍቶ የሚቆዝምበት ዘመን አብቅቷል። የጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክትም በአማራን ሕልውና ላይ የተጋረጠና ሊስተካከል የሚገባው መሆኑ ተሰምሮበታል። የወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄዎችም መልስ እንዲሰጣቸው እየተሰራባቸው ነው። አማራው የትም ሄዶ ቢኖር ከሕግም በላይ ተፈጥሯዊ መብቱ እንጅ በገዛ ሀገሩ መጤ የሚሆንበት፣ የሚፈናቀልበትና የሚገደልበት ዘመን ማብቃት አለበት። ለዚህም ከፌዴራል መንግሥትም ሆነ ከሌሎች ክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራበት ነው። በአማራ ክልል በአዲስ መልኩ የተቋቋመው “የበይነ መንግሥታት” ቢሮም ይህንን ዋና ተግባሩ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል። የክልል ከፌዴራልም ሆነ የክልል ከክልል ግንኙነቶች ከሕዝቦች ዘላቂ አብሮነትና ጥቅም አንፃር ተቃኝተው ይሠራሉ። ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው ይሆናል።

ለአማራ ክልልና ሕዝብ ያገባኛል ብለን የምንንቀሳቀስ አካላት ከምንም በላይ ትኩረታችንን የሕዝባችንን ወቅታዊ ችግር መፍታትና ዘላቂ ጥቅሙን ማስከበር ላይ ማድረግ አለብን። ወቅታዊ ችግሩን ብቻ ከተመለከትን ስሜታዊ ሆነን ዘላቂ ጥቅሙን ልናሳጣው እንዳንችልም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ሁለቱን ለአፍታም ነጣጥለን ማየት የለብንም። ምንም እንኳን አማራ ያሳለፋቸው ዘመናት የሚያስቆጩና ስሜታዊ የሚያደርጉ ቢሆኑም ቀጣይና አዋጭ ባልሆነ መንገድ የሚቆም ግፍም ሆነ የሚመጣ መፍትሔ እንደማይኖር ግንዛቤ ሊወሰድ ያስፈልጋል። የአማራ ስደት፣ መፈናቀልና ያለ ግብሩ የመወቀስ ጉዳይ መቆም አለበት። ቀጣይ ዘላቂ ጥቅሙም መከበር አለበት። ከወንድም ሕዝቦች ጋር ያለው የተዋሓደ አብሮነትና ለሀገር ያለው ሁለንተናዊ አበርክቶ ሳይዘነጋ በአማራነት ክብር በሀገሩ በኢትዮጵያ በነፃነትና በፍትሓዊነት የመኖር መብቱ ሳይሸራረፍ እንዲከበር በጋራ ልንሠራ ይገባል።

በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ በምንም አይነት ልዩነት ውስጥ ብንሆን ለሕዝባችን ስንል ተቻችለንም ቢሆን መተባበርና ኃይል አሰባስበን “ስትራቴጂካሊም” ሆነ “ታክቲካሊ” ተግባብተን በጋራ መታገል እንጅ አንዱ ሌላውን በመጥለፍና ጥሎ በማለፍ ስሌት ለመጓዝ መሞከር ብልህነት አይደለም። መንገዱም የትም አያደርሰንም።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE