የግል ባንኮች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ፕሮጀክቶችን እንዲያዋጡ ተጠየቁ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የግል ባንኮች በጋራ “ገበታ ለሀገር” የተሰኘውን ፕሮጀክት ጨምሮ መንግስት ለያዛቸው ተከታታይ የልማት ፕሮጀክቶች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንዲያዋጡ ጥሪ መቅረቡ ተነግሯል።

የግል ባንኮች ለጉዳዩ የሚያዋጡትን የገንዘብ መጠን እንዲገልጹ በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ አማካኝነት መጠየቃቸው ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለፈው ዓመት ትርፉ 7.2 በመቶ የሚሆነውን [ 1.2 ቢሊዮን ብር ] ለልማት ፕሮጀክቶቹ አበርክቷል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበኩሉ ካለፈው ዓመት የተጣራ ትርፉ 6 በመቶውን ለመስጥት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

የግል ባንኮች በበኩላቸው ለልማት ፕሮጀክቶቹ 5 በመቶ ትርፋቸውን ለማበርከት አቅደዋል። ባለፈው ዓመት 16 የሚጠጉ የግል ባንኮች አንድ ላይ 20.7 ቢሊየን የተጣራ ትርፍ ማስመዝገብ ችለዋል። በዚህ ዓመት ሥራ የጀመሩ ባንኮች አበርክቷቸው ከላይ ከተጠቀሱት አንሰው 0.5 በመቶ እንዲሆንም ተጠይቋል።

አዲሱ የማዕከላዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በቅርቡ በተደረገ ስብሰባ የባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ለመንግስት የልማት አጀንዳ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ምንጮች ገልጸዋል ሲል Addis Fortune አስነብቧል።