የኦሜጋ ቲቪ ባለቤት እባክዎ ለመጋቤ ሐዲስ ቡሩክ አድርሱልኝ

የኦሜጋ ቲቪ ባለቤት እባክዎ ለመጋቤ ሐዲስ ቡሩክ አድርሱልኝ

ከቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

“በአዲስ አበባ የሚኖሩትን የትግራይን ካህናት ለሚያስሩና ለሚገድሉ በትግራይ ሕዝብ ላይም ጀኖሳይድ ለሚፈጽሙ ኃይል ሰጭ ካህናት” በሚል ርእስ እኔን ወቅሰው በOmaga tv ለተመልካች ያቀረቡትን የተመለከቱ ሰዎች ነግረውኝ አየሁት፡፡ ሕሊናዬን እንድፈትሸውና እንድቃኘው ስላደረገኝ በጣም አመሰግነወታለሁ፡፡ ከዳሕጸ ሕሊና ነጻ በመሆኔም እግዚአብሔርን አመሰገንኩት፡፡ ከዳሕጸልሳን ነጻ ለመሆኔ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ዳህጸሕሊና ታስቦና ታቅዶ ከግል ጥቅምና ክብር ተያይዞ ከሕሊና በሸፍጥ በተንኮል መንጭቶ ባንደበት የሚገለጽ ንግግር ነው፡፡ በሕሊና ላይ የሚጥለው ጠባሳ በቀላሉ የሚፈወስ አይደለም፡፡ የሚያስከተለውም ፍዳ ከባድ ነው፡፡  ዳሕጸ ልሳን ግን ከሸፍጥ ከተንኮልና ከበቀል ነጻ ከሆነ ሕሊና የሚመነጭ፤ ካለመጠንቀቅ ከመቸኮልና ካለማስተዋል ካንደበት የሚፈልቅ መታረም የሚችል በይቅርታ የሚታለፍ የንግግር ስሕተት ነው፡፡

ከዳሕጸ ህሊና ነጻ መሆን የሚቻለው ቅዱስ ጳውሎስ “በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ እጥራለሁ” (የሐዋ 24፡16)  እንዳለው ከግል ጥቅም ወይም ከአድላዊነት ሕሊናን ነጻ ለማድረግ በመጣር ነው፡፡ በተለይ እኛ ካህናቱ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል መርሆ ፈሩን የለቀቀ ፍቅርና ጠብ ከማንም ጋራ ሊኖረን አይገባም፡፡ ፈሩን ከለቀቀ ግንኙነት ራሳችንን ከጠበቅን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “ለሞት የሚያበቃ በደል ከተገኘብኝ አልሞትም አልልም” (የሐዋ 25፡11)” ለማለት ድፍረት ይኖረናል፡፡

አንድ ሰው ባልበደለው በደል፤ በተንኮል ወይም በጥላቻ ቢከሰስም እንኳ  ፍርድ የሰፈነበት ዘመን ከሆነ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ  “ለሞት የሚያበቃኝ ከሆነ ለቄሳር ይግባኝ እላለሁ” ማለት ይቻላል፡፡ አሁን እንዳለንበት ይግባኝ  ሰሚ የጠፋበት ዘመን ሲሆን ወደ እግዚአብሔርና ሕዝብ ይግባኝ ይባላል፡፡ ወደ እግዚአብሔርና ሕዝብ ይግባኝ ማለቱ የበለጠ ይሻላል፡፡

በንግግሬ “በአዲስ አበባ ያሉ የትግራይ ንጹሐን ካህናት ይታሰሩ በትግራይ ሕዝብም ላይ ጀኖሳይድ ይፈጸምባቸው” ብየ ከሆነ የኔንም ሰምተው እንዲፈርዱ እኔን ከሰው ላቀረቡላቸው አድማጭወችዎ ይግባኝ ብያለሁና በነካ አንደበተዎና መገናኝ ይህችን ያድርሱልኝ፡፡ የተከሰስኩብት ከቄስ ነዋይ ጋራ ያቀረብኩት ንግግሬ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንቀጾች ላይ መሰርቼ ነው፡፡

“በኢትዮጵያ ምድር ባሉት ኢትዮጵያውያን ላይ የታወጀው ግድያ በአራት ማንነቶቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ እጅግ የከፋው ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን  አራቱንም ማንነቶች አካቶ በመያዝ በተገኘው ወገን ላይ ነው”

1ኛ፦በኢትዮጵያዊነት

2ኛ፦በአማራነት

3ኛ፦ባመረኛ ተናጋሪነት

4ኛ፦በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት

ኢትዮጵያውያን ከ 1 እስከ 4 በተዘረዘሩት ማንነቶቻቸው እየታደኑ ተገለዋል” ብየ የተናገርኩት ከሚጠበቅብኝ እርከን በታች እንዳዋረደኝ መስክረውብኛል፡፡ ከበቂ ባላይ በሆኑ ዋቢወች ላይ መስርቼ የተናገርኩት እርሰዎ እንዳሉት  ከነበርኩበት እኔነቴ ዝቅ ያደረኝ ከሆነ “ወዮለት ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር”(ማቴ 26፡24) ተብሎ ወዮታ ከታውጀበት ከይሁዳ ውድቀት እጅግ የከፋ ዋይታ ላይ ወድቄለሁ ማለት ነው፡፡

በዋቢ የተደገፈውን ስለተናገርኩ ወቀሳና ክስ ከደረሰብኝ በዋቤወቼ ላይ የሚደርሰው ክስ በኔ ላይ ከሚደርሰው እጅግ በጣም የከፋ ይሆናል፡፡ በዋቢወቼ ላይ የሚድርሰው እጅግ የከፋ ከሆነ ደግሞ ከላይ በተገለጹት በአራት ማንነቶቻቸው ላይ ግድያ በፈጸሙት ሰወችና ታራሚ እያሉ ባስፈጸሙት ካህናት ላይ የሚደርስባቸው ፍርድ ምንኛ እጅግ  የከፋ ይሆን? ከአማራው ውጭ በሆነው  ወገን ላይ ስለደረሰው እልቂት አልተናገርክም ብለውም ወቅሰውኛል፡፡ ከተዘረዘሩት ማንነቶች ካራቱ ባንዱ ንክኪ ያለው ሁሉ ተገደለ ስል፤ ስለተገደለው ሁሉ መናገሬ እንጅ  አማራ ብቻ ተገደለ ማለቴ አልነበርም፡፡

ለአጽንኦተ ርትዕ  እደግመዋለሁ፡፡ “በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ የሚኖረው አማራ ባይሆንም ቋኑቋውን በመናገሩ ተገድሏል፡፡ አማራ ባይሆንም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በመሆኑ ተገድሏል፡፡ አማራ ባይሆንም በኢትዮጵያዊነቱ ተገድሏል፡፡ ግድያው እጅግ የከፋበትና የጸናበት  አራቱን ማንነቶችን ይዞ በተገኘው ክፍል ላይ ስለ ሆነ ከሕሊናየ ፈልቆ  ባንደበቴ የፈሰሰውን በመደጋገም አጠነክረዋለሁ፡፡

በአራቱ ማንነቶች ላይ ወያኔዎች ያወጁት ግድያ  የትግራይን ሕዝብ ቀጥታ ባያካትትም “እስመ ቦ ጻድቃን ዘይበጽሕ ላዕሆሙ ግብረ ረሲዓን”(መክ 8፡14)  ለኃጥአን የወረደ ለጻድቃን ይተርፋል ማለት ነው፤ አራቱን ማንነቶች አካቶ በያዘው ባማራው ላይ የታቀደው ግድያ፡ የትግራይ ህዝብም በኢትዮጵያውነቱና በኦርቶድክስነቱ   ከመሰበርና ከመታረድ እንዳላመለጠ ደጋግሜ ገልጫለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ያልተገደለ አለ ከተባለ ከተዘረዘሩት ከአራቱ ማንነቶች ንክኪ የሌለው ብቻ እንደሆነ ተናግሬአለሁ፡፡

ኢትዮጵያውያን በአራት ማንነቶቻቸው ለመታረዳቸው  “አትረዱኝ ወላሂ ከዛሬ ጀምሮ አማራ አይደለሁም” እያለች የታረደችው ልጃችን በምድር ላይ ሳለች መስክራለች፡፡ የዚህች ልጅ ነፍስ “እስከ መቼ አትፈርድም እስከ መቼስ  ደማችንን በምድር የሚኖሮትን ትውልደአራዊት አትበቀልም”  እያሉ ገዳዮቻቸውን ከሚከሱት ነፍሳት ጋራ ተቀላቅላ እየከሰሰች ነው፡፡  (ራእይ 6፡10 )

መጋቤ ሐዲስ ቡሩክ ዳሕጸሕሊና ላይ ካልወደቁ በቀር ኢትዮጵያውያን  በ 4ቱ ማንነቶቻቸው ብቻ እየተዘመተባቸው መጨፍጨፋቸውን ሳያውቁት የቀሩ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት ባገር ውስጥ ስላልነበርኩ በቦታው አልነበርክም በዐይንህ አላየህም፤ ብለው ከሆነ በአካል ስላልነበርኩ ባይኔም ስላላየሁ ወቀሳውና ክሱ በከፊል ልክ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ግን ስሕተተኛ አያደርገኝም፡፡

ማንም ሰው ከግል ጥቅምና ክብር ርቆ በአድለዎ ሳይሰናከል በማነኛውም ነገር ላይ ከንጹሕ ሕሊና የሚሰጠው አስተያየት ፍጹም ባይሆንም ጨርሶ ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ትልቁ ዳኛ በጥቅም ያልተበከለ ንጹሕ ሕሊና ነው፡፡ እውነተኛ ዳኛ የሚፈርደው በቀረበለት መረጃ እንጅ በሚፈርድበት ጉዳይ ላይ ሁሉ በአካል ተገኝቶ አይደለም፡፡ ከላይ እንዳልኩት ዳኛየ ከሳሼ ሕሊናየ ነው፡፡

ገዳዮችና አስገዳዮች የሰሩትን ደባ ለመግለጽ ባደረኩት ንግግር ሰው ከተገደለበት ለገዳዩም ለተገዳዩም እጅግ አዝናለሁ፡፡ ተጠያቂነት ግን ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ “በሶስት ምስክር ነገር ይጸናል” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር መሠረት አድርጌ ከንጹህ ሕሊናየ ፈልቆ ባንደበቴ ለፈሰሰው ንግግሬ  ከዚህ በታች የዘረዘርኳቸውን ዋቢወቼን ተጠቅሜአለሁ፡፡

1ኛ፦ጀነራል ነጋ ተገኝ ነፍሳቸውን ይማረውና ወያኔወች በወልቃይት አማሮች ላይ  የፈጸሙትን  አልቂት ተመልክተው  1981 ዓ/ም አልቅሰው ሱዳንን ለቀው ለንደን የገቡት ክቡር ጄነራ ነጋ ተገኝ ነግረውኛል፡፡

2ኛ፦በዚያን ወቅት ሱዳንና አሜሪካ ይመላለሱ የነበሩት አሁን ኢትዮጵያ የሚኖሩት ልዑል መገሻ ሥዩም ወያኔወች በወልቃይት አማሮች ላይ የፈጸሙትን ግፍ ዲሲ ሲናገሩ ስምቻቸዋለሁ፡፡

3ኛ፦ የወልቃይት ጸገዴ ተወላጅ የሆኑት አሁንም በመታገል ላይ ያሉት አቶ ቻላቸው አባይ ከጀነራል ነጋ ተልይተው ወደ አሜሪካ መጥተው ስያትል ዋሸንገተን ሲያርፉ ከተቀበሏቸው ሰወች አንዱ ነብርኩ፡፡ ከሁለቱ አዛውንቶች የሰማሁትን አጠናክረው ሲናገሩ ሰምቻቸዋለሁ፡፡

4ኛ፦ ባንድ ወቅት “ እርቅ የሚሉ ሁሉ ይገደሉ” በሌላ ወቅት “አማራንን ኦርቶዶክስን ሰበርነው” ያሉት አቶ ስብሀት ነጋንም ሰምቻለሁ፡፡

5ኛ፦ ወያኔወች “የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑን ትግባር ያከናወኑትም አቶ ስብሀት ነጋን ገ/ኪዳን ደስታ ናቸው፡፡ የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው”  ብለው በመመሪያቸው ያሰፈሩትን፤ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት መመረቂያ በጻፉት ላይ ጠቅሰውት አንብቤዋለሁ፡፡

5ኛ፦ ከላይ እንደተጠቀሰው ወያኔወች ቀደም ብለው የዘረጉትን የጥፋት ዘመቻ ከግቡ ለማድረስ  ኢትዮጵያን ከተቆጣጣሩ በኋል ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል ሕዝቡ እርስ በሩሱ እንዲፋጅ የቀመሩትን መርዝ አንቅጽ 39ን አንቤአለሁ፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ አቅደው ህዝብ የሚለያይበትን ሰው የሚጎዳዳበትን ሕግ ለሚቀርጹ እኩያን “አሌ ሎሙ ለእለ ይጽሕፉ መጽሐፈ እኩየ ወይመይጡ ፍትሐ ነዳይ ወምስኪን ሕዝብየ ወአይቴ የሐደጉ ትርሲቶሙ ከመ ኢይደቁ ውስተ ሀሳር፡፡ ውበዝኒ ኩሉ ኢተመይጠት መአቱ”  (ኢሳይያስ 10 ፡2) ብሎ  የተናገረውን አንቀጽ 39 ን በህግ ወስጥ በሰነቀሩ ሰወች ላይ ጠቅሼ ክፋታቸውንና ተንኮላቸውን ካልመሰከርኩ በቅኔ ቤት ባንድምታው ቤት መቆየቴ ባስኳለውስ መድከሜ ጥቅሙ ምንድነው?

ነገርን ነገር ያመጣዋልና መጋቤ ሐዲስ ቡሩክ እኔን በወቀሱበት መድረክ ባንድ ወቅት ከቡነ ማትያስ ጋር በተያያዘ ምክንያት በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ የሰነዘርኩትን ደግፈው ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ቢደግፉትም በወቅቱ የዲያቆን ዳንኤል ጭፍሮች ከነሱ ይልቅ አብልጣ አጥብታና አልቃ ካሰደገችኝ ከቤተ ክርስቲያኔ እንድልይና እንድገለል ዘምተውብኛል፡፡  የምጽፈው እንዳይነበብ የምናገረው እንዳይሰማ ያላቸውን የማፈን ኃይል ተጠቅመዋል፡፡ ሸፍጣቸውን ባልተረዱ ወዳጅ ዘመዶቼም  እንድጠላ አድርገውኛል፡፡

በዚያ ወቅት የተናገርኩት ለርሰዎ ቢመቼወና ቢደግፉትም በነ ዲያቆን ዳንኤል ሸፍጠኛ መረብ ተጠልፌ እንድጠመድ ያደረገኝ በማይለወጠው አቋሜ ነው፡፡ ወያኔ የዘረጋው የፖለቲካ ሰይፍ በመካከላችን የነበረውን የፍቅር ሰንሰለት በጠሰውና ለያየን እንጅ እንኳን እነ ዲያቆን ዳንኤል ዛሬ የከበቧቸው ያካቢያቸው ሰወች አቡነ ማትያስን ከኔ የበለጠ ያውቋቸዋል ብየ አልገምትም፡፡ አቡነ ማትያስን  በዘር በጎሳ በፖለትካና በጥቅም ከከበቧቸው  በላይ አውቃቸዋለሁ፡፡

ሰወች በዘርጉላቸው ጥልፍልፍ ውስጥ ገብተው አብረዋቸው ከኖሩት በዚያን ጊዜ መምህር መርሐ ጽድቅ ያሁኑ ቄርሎስ አብልጠው ይወዷቸው የነበሩትን አባታቸውን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከማውገዛቸው በፊትና፡ ከዚያም በወያኔወች ፖለቲካ ተጠልፈው ጭንቅላታቸው እንደኳስ መንጠር ሳይጀምር በሰባዊ አመለካከታቸው ገርና የዋህ አባት እንደነበሩ ባልመሰክር ከሕሊናየ ክስ ማምለጥ የማልችል ሸፍጠኛ መሆኔ ነው፡፡

መጋቤ ሐዲስ ቡሩክ ዲያቆን ዳኔልን የጠቀሱበትን ምክንያት ሳይገልጹ ከኔ ጋራ በማያያዝ አቅርበውታል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል እራሱ ተሳስቶ አቡነ ማትያስን ባሳሳታቸው ጉዳይ፡ እንደገና በሌላ ወቅት ራሱን ቀይሮ ሌላ ሰው በመሆን አቡነ ማትያስን ሲከስ እኔ የማውቀውን ያላወቀ ሰው፡ በሱ ሸፋጭ ንግግር በገርነት የተጠለፉትን አቡነ ማትያስን ከመውቀስ ለማትረፍ ዲያቆን ዳንኤልን ወቅሼ ጽፌአለሁ፡፡ ይህን ስጽፍ ከወንድሜ ዳኔል ጋራ መጣላትን ከአቡነ ማትያስ መወደድን በመሻት አይደለም፡፡

ዲያቆኑን የወቀስኩት “ዘየአምራ ለሠናይት ወኢይገብራ ኃጢአት ትከውኖ” () ከሚለው ከራሴ ሕሊናዊ ወቀሳ ክስ ለማምለጥ ብቻ ነው፡፡ ሰው ለመኖር አየር ስለሚተነፍስ ውሀ ስለሚጥጣ መመስገን እንደሌለበት ሁሉ፦ ለራሱ ሕሊና ጤንነት በመጠንቀቅ ለሚያደርገው መመስገን ያለበት አይመስለኝም፡፡

መጋቤ ሐዲስ ቡሩክ ዲያቆን ዳንኤልን ከኔ ጋራ አጫፍረው የገለጹበትን ምክንያት ራሳቸው ባይገልጹትም ባጭሩ ልግለጸው፡፡ አቡነ ማትያስ ወያኔ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር የመላ አሜሪካ ሊቀ ጳጳስ በሆኑ ጊዜ፤ በኔና በአቡነ ማትያስ መካከል የነገረ ማርያም ትርጉም ልዩነት ተፈጠረ፡፡ በኔና በሳቸው መካከል የተፈጥረው የትርጉም ልዩነት ከኔ አልፎ በአቡነ ማትያስና በዚያን ጊዜ በሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ይመራ በነበረው በማህበረ ካህናቱ መካከል ሆነ፡፡

በወቅቱ ለአዲስ አበባው ሲኖዶስ ቀኝ እጅ ሆኖ ይራወጥ የነበሩው  ዲያቆን ዳንንኤልና ሁለት ቢለዋ ይጠቀም የነበረው ቄስ ከፈለኝ  ባልዋሉበት ባልተማሩት ባልደከሙበት ለጥቅም ፍለጋ ራሳቸውን አሰልፈው “የእኛና የሮማ ኮቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በገረ ማርያም በፍጹም ልዩነት የለንም አንድ ነን፡፡ የቀድሞወቹን ጽሑፎች የሚተኩ ሌሎችን መጻሕፍት ጽፈው ያበረከቱ መሆናቸውን መረዳት እጅግ አስፈላጊ ይመስለናል”(ንጋት ገጽ 40_42)   ብለው ጽፎ አቡነ ማትያስን እያሰፈረመ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሚመለከተው ማሰራጨት ጀመረ፡፡

በሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ይመራ የነበረው ማህበረ ካህናት “ይህን አባባል መላው ኦርቶዶክስ አይቀበለውም፡፡ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ጋራ የተጋጨ ነው፡፡  የጥንቱን የኦርቶዶክሱን ጥላችሁ አዲስ ሊቃውንት የጻፏቸውን አዳድዲስ መጻህፍትንና የሚሰብኩትን አዲስ እምነት ተቀበሉ ማለት ነውና አንቀበለውም” ተሳስተዋልና ይታረሙ  46_55  የሚል መልስ በመስጠት ማህበረ ካህናቱንና አቡነ ማትያስን ከውዝግብ ከተታቸው፡፡

አቡነ ማትያስን እያስፈረመለአቡነ ጳውሎስ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለማይመለከተው ሁሉ አሰራጨ፡፡ የአቡነ ማትያስ ፊርማ ቢኖርበትም በዳንኤል ክብረት ስሕተት የታጀለ  ቤተ ክርስቲያንን ከኦርቶዶክሱ ሕብረት የሚያወጣት ስለነበረ በአቡነ ጳውሎስ  ይመራ የነበረው ሲኖዶስ ታዝቦ ጣለው፡፡

የፈጠረው ግጭት ከማህበረ ካህናቱ ጋራ ብቻ ሳይሆን ወደ አኀት አብያተ ክርስቲያናትና ወደ አቡነ ጵዋሎስም ተሻገረ፡፡ ከአኅት አብያተ ክርስቲያናት ሕብረትም እንደወጡ አድርገው አስወቅሷቸው፡፡

አቡነ ማትያስ በነ ዲያቆን ዳንዔል ተጽፎ ቀርቦላቸው የፈረሙበት ወረቀት በአቡነ ጳውሎስና በሲኖዶስ በመጣሉ ተናደው፡ አቡነ ጳውሎስን “ከፋፋይ” በሚል ቃል ከዘለፉባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ የዳንዔል ጠንቅ ነበር፡፡ ዝርዝር ጉዳዩን “እውነትና ንጋት ” በሚል ርእስ ቆሞስ አባ ሠረቀ ወ/ ሳሙኤል  ታህሳስ 2004 አሳትመው ባስመረቁት መጽሐፍ ከገጽ 23 እስከ 55  ላይ የሰፈረውን ይመልከቱ፡፡

ዲያቆን ዳንኤል የራሱን ሸፍጥና ስህተት ጽፎ እያሰፈረመ ባሰራጨው አቡነ ማትያስን ከብዙወች ጋራ ማጋጨቱን ረስቶ ይሁን ደብቆ፡ እንደገና በሌላ ወቅት ራሱን ቀይሮ ራሱን የነገረ ማርያም ጠባቂ አቡነ ማትያስ አፍራሽ አደርጎ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ  “ለመሆኑ የእኛ አባት የቱን ነው እየፈጸሙ ያሉት? ወይስ ከኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ውጭ ሆነናል?” እያለ የጻፈው እጅግ ገረመኝ አስቆጣኝም፡፡

በመቀጠለም እንደ ጠንቌይ ብእር አነሱ እያለ በሳቸው ላይ ያቀረበውን ዘርቅ እንኳን ለሳቸው መገለጫ ሆኖ ሊነገር ቀርቶ ለራሱ እንኳ ሲነገርበት ብሰማ የማልቀበለው በመሆኑ ስሰማው ዘገነነኝ፡ “ታዲያ በዚህ ጉዳይ ከአቡነ ማትያስ ጋራ ወይስ ከዳንዔል ጋር መሰለፍ አለብኝ?ፈጽሞ የለብኝም” ብየ  “ተስልክላኪ ዘንዶ” በሚል ርእስ June 13, 2015 በጻፉኩት ጦማር  በዲያቆን ዳንኤል ላይ የነበረኝን ትዝብት ለታዛቢው ህዝብ ገልጫለሁ፡፡

”ወይፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ “ የሚለውን ያስተማሩኝ  ሊቃውንት፤ ሰውን በየምግባሩና በየስራው ለመግለጽ እንጅ፤ በሌላ ነገር የበደለ ቢሆንም ባልደለበት ነገር፤ በሸረኛ ሲገደል ታደገው እንጅ፤ እሰይ እንኳ ደረሰበት ብለህ ከገዳዩ ጋራ ብትስማማ አንተም ነፍሰ ገዳይ ነህ“ ብለው ያስተማሩኝን እንዴት ልለፈውብያለሁ፡፡

ዲያቆን ዳኔል ያደረገውን ጥልፍልፍ ሸር ተቃውሜ ያቀረብኩትን ሀሳብ መጋቤ ሐዲስ ቡሩክ ከብዙ አመታት በኋል ጠቅሰው ቅር ከተሰኙበት ጋራ በማነጻጸር ያቀረቡብኝን ወቀሳ  ስመለከተው ባንድ ወቅት ባንድ ቦታ የተከሰተውን ታሪክ  አስታወሰኝ፡፡

አንድ ሰው በመንደሮች መሐል ሲያልፍ፤ በመንደሮች መካከል የበቀለ ትልቅ ዋርካ  ቅርንጫፍቹ እጅግ ከብደውት በመንደሮቹ ጣራ ላይ ሊወድቅ አንዣቦ ያያል፡፡ አልፎ ሀጁ ሰው  “ይህ ዛፍ  ሊወድቅ ነው፡፡ ከወደቀ ቤትም በረትም ሰውም እንስሣም አይተርፍምና በጊዜ ከርክሙት” እያለ የማስጠንቀቂያ ድምጹን አሰማ፡፡ ከነዋሪወቹ  ጩኸቱን ሰምቶ ለማስተካከል የሞከረ ሰው አልነበረም፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ዋርካው በነፋስ ተገፍቶ በቤት በበረት ላይ ወድቆ  ሕዝብና ከብት ፈጀ፡፡ ከሞት ያመለጡ ሰወች አልፎ ሐጁ ሰው የነገራቸውን ማስጠንቀቂያ ሳይጠቀሙበት በመቅረታቸው መጸጸት ሲገባቸው ያስጥነቀቃቸውን ሰው “ሟርተኛ” ብለው  ከሰሱት፡፡ መጋቤ ሐዲስ ቡሩክም እኔን በማይገልጸኝ ከመውቀስ ይልቅ  ሟርተኛ ቢሉኝ ይገልጽላቸው ነበር፡፡

መጋቤ ሐዲስ የወቀሰኙ ምንም በደል ሳይሰሩ በአራቱ ማንነቶቻቸው ብቻ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው መከራ በክርስቶስ ላይ ከደረሰው ተደራራቢ መከራ ጋራ እንኳ የሚነጻጸር አይደለም በማለቴ ነው፡፡ ክርስቶስ የደረሰበትን መከራ በተወሀደው መለኮቱ ቻለው፡፡ በአራት ማንነቶቻቸው እየተፈለጉና እየታደኑ የተዘመተባቸው ወገኖቻችን ይህንን አሰቃቂ ድርብርብ መከራ በምን አቅማቸው ይቻሉት? ፡፡ክርስቶስ “በኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ይሠራል፡፡ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” (ዮሐ 14፡12) ያለው፦ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ይህን የመሰለውን ተደራራቢ መከራ ለመግለጽ እንደሆነ ኦርቶዶክሳውያን መምህሮቻችን ነግረውናል፡፡

በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው መከራ  የተደራረበ ነው ያልኩት፤  ከሞት የተረፉት ወገኖቻችን ባሎቻቸው ሚስቶቻቸው ልጆቻቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሰይፍ እየታረዱ በጦር እየተወጉ በድንጋይ በብትር እየተቀጠቀጡ በእሳት እየተቃጠሉ  ሲገደሉ በማየታቸው ነው፡፡ ንብረታቸው ቤታቸው ተቃጥሎ ፈርሶ የቀብር መሬት ተነፍጓቸው ለአራዊት ሲሰጡ አይተዋል፡፡ ይህን ሁሉ አይተው ከሞት ተርፈው በሕይወት ያሉት ወገኖቻችን ክርስቶስ “እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ”” (ምቴ 9፡36) ከተጨነቀላቸውና ካዘነላቸው ሰወች በላይ የሚገባቸውን እዝናትና ብድራት  በመንግሥትም በቤተ ክርስቲያናቸውም የተነፈጉ ናቸው፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ “ከኃጢአተኛ ጋራ ስትታገሉ ደማችሁን እስከማፍሰስ ድረስ  አልተቃወማችሁም” (ዕብ 12፡4)፡ እንዳለው በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያናቸውም እዝናትና ብድራት ለተነፈጉት  በአራት ማንነቶቻቸው ለታረዱት ክርስቲያኖች የሚያርዷቸውን አረመኔወች እስከ ደም ጠብታ የተቃወመላቸው  አንድም ጳጳስ የለም፡፡ ዛሬ በተናጠል እጅግ በጣም ለቀረበን ሰው ጉዳት ብቻ የሚደረገው ጩኸት ከተጠያቂነት አያድነንም፡፡

በንግግሬ ዳሕጸ ልሳን ከተገኘ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡  እዝናትና ብድራት ከተነፈጉት መካከል እንደ መአዛ መሐመድ በአካል ተገኝቼ  መከራውን ባለመሳተፌ ይጸጽተኝ እንደሁ እንጅ እርሰወ ባቀረቡብኝ ወቀሳ ሕሊናየ አልፈረደብኝም፡፡

ስለሚቀጥል እዚህ ላይ ይቆየን፡፡

ቀሲስ አስተርአየ

[email protected]

መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም.