የአዲሱ ጉራጌ ፓርቲ አስተባባሪዎች በፖሊስ ታፈኑ

የምስረታ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያካሄደው ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ጎጎት የሚል ስያሜ ያለው አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ” የምርጫ አስፈፃሚዎች እና አስተባባሪዎች ከያዙት ሰነድ ጋር ዛሬ በፖሊስ ታፍነው ተወሰዱ ሲል የፓርቲው ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ አስታወቀ ። የኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ጀሚል ሳኒ ሰዎቹ የተያዙት ስብሰባው ከተካሄደበት ሆቴል አድረው ሲወጡ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

«ምርጫው እስከ ለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ነው የሄደው።ከ9 ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸርው መሄድ ስለማይችሉ እዛው በጉባኤተኛ የተመረጡ የምርጫ አስፈጻሚዎችና የእለቱን ጉባኤ ሲያስተባብሩ የነበሩ ቆጠራ ላይ የነበሩ ወደ አምስት ሰዎች የምርጫ አስፈጻሚ ሶስት አጠቃላይ የምርጫ አስፈጻሚ 8 አካባቢ አጠቃላይ 10 ልጆች ነበሩ።እዚያው ዋቢሸበሌ አድረው ሲወጡ ከያዙት የጉባኤው ሰነድ ጋር ጭምር አንድ ላይ በፖሊስታፍነው ተወስደዋል።»

ድርጅቱ ከሦስት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ማግኘቱን ያስታወቁት አቶ ጀሚል ሳኒ ትናንት እሁድ እስከ ሌሊት ባካሄዱት ስብሰባ የኦዲት እና የቁጥጥር አባላትን ጨምሮ 29 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና 7 ተጠባባቂዎች ተመርጠው ዝርዝሩ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተልኳል፤ ውጤቱም በአጭር ጊዜ ይታወቃል ብለዋል።ውጤቱ ከታወቀ በኋላ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚዎች ተለይተው ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

አቶ ጀሚል ፓርቲው የተመሠረተው “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጉራጌ ሕዝብ ላይ ሕገ – መንግሥታዊ ያሉት ጥያቄ ስለተጠየቀ ብቻ አቃፊ ድርጅት ባለመኖሩ መንግሥት ጠያቂዎችን “መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች” በሚል እየፈረጀ እና እያሰረ መሆኑ፣ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ለዚህ የማህበረሰቡ ጥያቄ አጽንዖት ሰጥተው ከመግለጫ ባለፈ መንግሥትን መሞገት ባለመቻላቸው ያንን ክፍተት ለመሙላት ነው ብለዋል።

ጉራጌ ክልል መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ ያነሱ ሰዎች ለእሥር እና እንግልት መዳረጋቸውን የተናገሩት አቶ ጀሚል መሥራች ጉባኤውን ያደረገው ይህ ፓርቲ እንዲህ ያለው ችግር እንዲፈታና የሕዝብ ጥያቄዌች መልስ እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል።