የጉጂ ሕዝብ ተቃውሞ ቀጥሏል፤ መንግስት ውሳኔዬን አልቀለብስም ብሏል

የተመሰረተው ዞን እንደማይቀለበስ፤ ነገር ግን ስያሜውን ሦስቱ ጎሳዎች ተመካክረው መቀየር ይችላሉ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል በማለት ምስራቅ ቦረና በሚል የመሰረተው የክልሉ 21ኛ ዞን ኢፍትሃዊ ነው በማለት የጉጂ ህዝብ መቃወሙን ተከትሎ የዞኑ ተወካዮች ቅሬታቸውን ለፌዴራልና ለክልሉ መንግስታት አቀረቡ፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በዚሁ ቅሬታ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግስት የተመሰረተው ዞን እንደማይቀለበስ፤ ነገር ግን ስያሜውን ሶስቱ ጎሳዎች ተመካክረው መቀየር እንደሚችሉ ተነግሮናል ብለዋል፡፡

ጥያቄያችን ምስራቅ ቦረና በሚል የተሰየመውን ዞን ስሙን ከመቀየርም በላይ ነው ያሉት የጉጂ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎቹ በመንግስት ምላሽ አለመርካታቸውን ገልጸው፤ ውሳኔው የህዝብ በመሆኑ ህዝብ ግን እናወያይበታለን ብለዋል፡፡

Addis Ababa Guji የጉጂ ዞን ተወካዮች ቅሬታቸውን ለፌዴራልና ለክልሉ መንግስታት አቀረቡ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ከአንድ ሳምንት በፊት ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. አደረኩ ባለው 6ኛ የስራ ዘምን 2ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ምስራቅ ቦረና የተባለውን 21ኛ ዞን ከቦረና ሞያሌ፣ ጉቺ እና ዋችሌ ወረዳዎችን፤ ከጉጂ ጉሚ የልደሎ እና ሊበን ወረዳዎች እንዲሁም ነጌሌ ቦረና ከተማን፤ እንዲሁም ከባሌ ዞን መደወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሀረና ቡሉቅ ወረዳዎችን በማካተት መሰረትኩ ብሏል፡፡ በውሳኔው መሰረት ከዚህ በፊት የጉጂ ዞን ዋና ከተማ ሆና ስታገለግል የነበረችው ነገሌ፤ ነጌሌ ቦረና በሚል መጠሪያ የምስራቅ ቦረና ዞን መቀመጫ ትሆናለች፡፡ አዶላ ሬዴ ደግሞ የጉጂ ዞን ዋና ከተማ እንድትሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ይህንኑን ተከትሎም ተቃውሞና አለመረጋጋት በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ባለፉት ሁለት ሳምንታት መስተዋሉም አይዘነጋም፡፡