‹‹ሰማኒያ ፓርቲ የተፈጠረው ኢህአዴግ ደካሞችን ስለሚያበረታታ ነው፡፡››ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት

‹‹ሰማኒያ ፓርቲ የተፈጠረው ኢህአዴግ ደካሞችን ስለሚያበረታታ ነው፡፡››ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ከምርጫ 97 ጀምረው በኢትዩጲያ ፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡የሰማያዊ ፓርቲ መስራች እና ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነሩ፤በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢትዮጲያ ሃገር አቀፍ ንቅናቄ(ኢሃን) ሊቀመንበር ናቸው፡፡ከኢንጅነር ይልቃል ጋር ስለ ኢትዮጲያ ፖለቲካ ወቅታዊ ሁኔታ ቆይታ አድርገናል፡፡መልካም ንባብ፡፡
ፖለቲካ እና ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንዴት ተገናኙ?
ተወልጀ ያደግሁት ጐጃም ውስጥ ደብረ ወርቅ ከምትባል ትንሽ ቦታ ነው፡፡ በዚሁ አካባቢ ኢህአዴግ እንደገባ የመሬት ድልደላ፣ መሣሪያ ማስመለስ፣ ማደህየት… የመሳሰሉት በደሎች በህዝቡ ላይ ይፈፀም ነበር፡፡ ይህን የማሰብ አቅም ያለው ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ቁጭት ይፈጥራል፡፡ መገፋት ወደ ፖለቲካ ገፋኝ፡፡ ቀጥታ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ የገባሁት ግን በ1997 ዓ.ም ነው፡፡ የቅንጅት አባል ነበርሁ፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ግን የተወሰነ አነሳስቷል፡፡ ለመሆኑ ፓርቲው ለአሁኑ አንፃራዊ ለውጥ ምን ሚና ተጫውቷል?
ከምርጫ 97 በኋላ ገዥው መንግስት በዴሞክራሲ ማሸነፍ እንደማይችል ስላረጋገጠ፣ አፋኝ ህጐችን ማውጣት ጀመረ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ማሰር እና ማንገላታት ሲጀምር የፖለቲካው ሁኔታ ፀጥ እረጭ አለ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ወጣቶች እንደገና ተደራጀን፡፡ ፖለቲካውን ከቢሮ መግለጫነት ባሻገር በተግባር ህዝብን ማነቃነቅ በሚለው መርሐችን መሠረት ከምርጫ 97 ከስምንት ዓመታት በኋላ ሠላማዊ ሠልፍ አደረግን፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት በዓል እየተከበረ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበረ፣ የኢትዮጵያን መንግስት አገዛዝ ችግር ለመላው ዓለም ለማሳየት የሞከርነው፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ማሳወቅ እንጅ ማስፈቀድ ግዴታ እንዳልሆነም ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ከ50ኛው የአፍሪካ ህብረት ሰብስባ ከሳምንት በኋላም ፖለቲካ እስረኞች፣ ስለጋዜጠኞች መብት፣ ስለተፈናቃዮች ጉዳይ በአደባባይ አንስተናል፡፡ በርካታ አማራዎች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው ስለነበር የመብት ጥሰቱን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አሳይተናል፡፡
መንግስት በሐይማኖት ጣልቃ በመግባት በተለይም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ችግር ስለነበር የሙስሊሙን ማህበረሰብ፣ የታሳሪዎች እና የተፈናቃይ ተወካዮች በአደባባይ ሃሣባቸውን እንዲገልፁ አድርገናል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ መሠለፍ፣ መቃወም፤ መብትን መጠየቅ እየተለመደ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ፍርሃትን ገለነዋል፡፡

የአዳር የተቃወሞ ሰላማዊ ሠልፍም ነበራችሁ፡፡ ይሄስ ምን መፍትሔ አመጣህ?
ህዳር 27 እና 28 በ2007ዓ.ም የተካሄደ ነበር፡፡ ምርጫው በነፃነት እንዲደረግ፣ “ነፃነት ለፍትኃዊ ምርጫ” በሚል ነበር ድምፃችንን ያሰማን፡፡ በዚህ የ24 ሰዓት ሰልፍ ሰማያዊ ፖርቲን ጨምሮ የደቡብ አካባቢ ፖርቲዎችም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ድብደባ እና እስር ተፈጽሞብናል፡፡ ሆኖም በተግባር ዋጋ እየከፈሉ መምራት የፖለቲካ ባህሪ መሆኑን ለማሳየት ጥረናል፡፡ ከመኪና ተገፍቸ ወድቄ ከብዙ ጊዜያት በኋላ ነበር የዳንሁ፡፡ ቀዝቃዛ ቤትም ታስረን ነበር፡፡ ይህ ወጣቶችን የበለጠ ለትግል አነሳሳ፡፡ ህዝባዊ አብዮቱም 2008 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ተጋጋለ፡፡
2005 ዓ.ም አማራዎች ከቢንሻንጉል ሲፈናቀሉ ቦታው ድረስ ሄደው ነበር፡፡ ምን ታዘቡ?
በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ ገጠር ድረስ ሂደን ተመልክተናል፡፡ በየገበሬ ማህበሩ ስማቸው ተለይቶ እየተለጠፈ አማራዎች ተለይተው ይባረሩ ነበር፡፡ መንገድ ላይ ሁሉ የወለዱ እናቶች ነበሩ፡፡ የሚገርምህ ነገር፣ “ለምን ወደ ቤሻንጉል ጉሙዝ ገባችሁ?” ተብለን እኛም ታስረን ነበር፡፡ መረጃችንንም ተነጥቀናል፡፡ የተወሰኑ መረጃዎችን ብቻ ይዘን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አድርሰናል፡፡ ሰው ባቀናው ሀገር በድሮው የጐጃም አንድ ክፍለ የነበረው ያን ያህል መፈናቀል ያም ነበር፡፡ ብአዴን ለተፈናቃዩች እውቅና እንኳን አልሰጠም፡፡ አልተዘገበምም ነበር፡፡
ኢሳት ግን ይዘግብ ነበር፡፡ በኋላም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ህዝብ እንዲያውቀው አድርገን መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው አስገድደናል፡፡
እንደ አማራ እና እንደ ኢትዮጲያ መደራጀት የትኛው ለወቅቱ ፖለቲካ ቅርበት አለው?
በፊት የነበረው የአንድነት ፖለቲካ ችግር ነበረው፡፡ በራሳችን ላይ ህገመንግስት ተቀርጾ ጨቋኝ ተብለን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ልዩ ተቆርቋሪ ሆነናል፡፡ አማራው በሁሉም ሁኔታ ሲገለል፣ በምናብ ብቻ ኢትዮጵያ እያልን፣ የአማራውን ችግር አላየንም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተመስርቷል፡፡ ኢትዮጵያም የምትድነው አማራ ሲደራጅ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ እኛ አውዳሚ በሆነ ሁኔታ አማራ ጠል ፕሮፓጋንዳ በገዥው መንግስት እንዳለ እውቅና ስጥተን ሀገር አቀፍ ፖርቲ መስርተናል፡፡ እኛ በኢትዮጵያዊነት ተደራጅተን ለአማራውም ችግር እውቅና እንሰጣለን፡፡

ተጨማሪውን ሊንኩን በመጫን ያንብቡ! http://amharaweb.com/am/node/648