የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት ባለፉት ቀናት በከፈተቱ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሽራሮን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችን መያዛቸውን ገለጹ።
ዋና አዛዡ ማክሰኞ መስከረም 03/2015 ዓ.ም. ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ እየተካሄደ ነው ስላሉት ጦርነት በሰጡት መግለጫ “ከኤርትራ አቅጣጫ የመጣው የሁለቱ አገራት ሠራዊት ሽራሮን ተቆጣጥሯል” ብለዋል።
ከኤርትራ ድንበር 50 ኪሎ ሜትሮች በላይ የማትረቀው ሽራሮ ከተማ ወደ ሽረ እንዳስላሴ፣ ባድመ እና ሁመራ አቅጣጫ ለመጓዝ አዋሳኝ ከተማ ነች።
የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥት ጥምር ጦሩ ሽራሮን ጨምሮ አንዳንድ የትግራይ አካባቢዎችን ይዘዋል ስለመባላቸው ያሉት ነገር የለም።
“አደመይቲ፣ ሀልነብሪ እና አደርቃይን ተቆጣጥረዋል” ያሉት ታደሰ ወረደ፤ “ማይ ፀብሪን ለመያዝ ማጥቃት ቀጥሏል። ማይ ፀብሪ ላይ ቆሞ ነው ያለው” ሲሉ እየተካሄደ ስላለ ውጊያ ተናግረዋል።
ታደሰ ወረደ የሰጡት መግለጫ የትግራይ አመራሮች የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነትን በንግግር ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ ጦርነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመላከተ ሆኗል።
የትግራይ አመራሮች በኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ መስከረም 01/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ አዲሱ ዓመት የተኩስ ደምጽ የማይሰማበት እንዲሆን፤ ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህን የህወሓት የተኩስ አቁም እና የንግግር ጥሪን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት-ኢጋድ፣ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና ጀርመን እንደሚደግፉት በመግለጽ የሰላም ንግግሩ በአፋጣኝ እንዲጀመር ጥሪ አቅርበው ነበር።
ጦርነቱን “በየትኛውን ጊዜ እና ቦታ” በንግግር ለመፍታት ዝግጁ ነኝ ሲል የነበረው የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ አስተዳዳሪዎች የድርድር ጥሪን ተከትሎ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የትግራይ ኃይሎች መሪ ጀነራል ታደሰ፤ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት ምሥራቅ ዕዝ ወደ ኤርትራ ተሻግሮ ከኤርትራ ሠራዊት ጋር በመሆን በሁለት አቅጣጫ “ትልቅ ኃይል” አሰልፏል ያሉ ሲሆን፤ “አንዱ በሽራሮ አቅጣጫ የሚያጠቃ ነው። ሌላኛው ደግሞ ባድመን መነሻ አድርጎ ጥቃት ከፍቷል ብለዋል።