ስብሃት ነጋ ዶ/ር አብይን ደካማ ነው እያለው ነው #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።
 
“አሁን አገሪቷ እያስተዳደረ ያለው ሀይል ደካማ፣ አገሪቱን ማስተዳደር የማይችል እና ፀረ ዲሞክራሲ ሀይል ነው”
 
ይሄን ያለው የዘረኞች አባት የሆነው ስብሃት ነጋ ነው። ዶ/ር አብይን ጸረ-ዲሞክራሲያዊ ነው ያለውን እዚያው ለርሱ ሰዎች ይንገራቸው። ዶ/ር አብይ የፖለቲካ ምህዳሩን የከፈተ፣ ጋዜጦች እንዲያብቡ ያደረገ፣ የፍርድ ቤትን የምርጫ ቦርድ ላይ ገለልተኛ ሰዎች የመደበ በአገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ ትልቅ አስተዋጾ ያደረገ ነው። አብያችን በዚህ አይታመም። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የኛ መሪ በሆነ እያሉት ነው።
 
ግን ስብሃት ነጋ “ደካማ ነው፣ አገሪቷን ማስተዳደር አልቻለም” ያለው ላይ ግን በተወሰነ ደረጃ ትክክለኛነት አይበታለሁ። እንዴት ነው ዶ/ር አብይ ደካማ አይደለም፣ አገር ማስተዳደር ችሏል ብለን መናገር እንችላለንን ?????
 
የኦሮሞ፣ የትግራይና የቤኒሻንጉል ክልሎች ከቁጥጥር ውጭ ሆነዋል። ሕዝብ ትልቅ በደል እየደረሰበት ነው። ህዝብ እየተፈናቀለ፣ ዜጎች በግፍና በጭካኔ እየተገደሉ ነው ።
 
– በምስራቅ ኦሮሚያ በሃረርጌ፣ በደቡብ ኦሮሚያ በቦረና ፣ በምእራብ ኦሮሚያ በወለጋ፣ በመሀል ኦሮሚያ ቡራዩና ፈንታሌ ..የኦነግ ርዝራዦች፣ የጃዋር አክራሪ ቄሮዎች ከሕግ በላይ ሆነው ፣ በአካባቢው ካሉ የዶ/ር አብይ ፓርቲ የኦህዴድ/ኦዴፓ የቀበሌ፣ የወረዳ አመራሮች ጋር በመተባበር እጅና ኋንት በመሆn ህዝቡን እያሸበሩት ነው። ዶ/ር አብይ እንኳን አገርን በሰላም ሊያስተዳደር፣ የራሱን አባላትን እንኳን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ እነዚህ፣ እንደ አሰላዋ አክራሪ ከንቲባ ዘይነባ ያሉ፣ የኦህዴድ ታችኛውና መካከለኛው አመራሮች የድርጅቱን መሪ ዶ/ር አብይን ሳይሆን የሚሰሙት ጃዋር መሐመድን ነው። በአጭሩ እነ ዶ/ር አብይ ሕግን ማስከበር ካለመቻላቸው የተነሳ ክልሉን አሳልፈው ለአክራሪዎች ሰጥተዋል፡
 
– በትግራይ በሕግ የሚፈለጉ ወንጀለኞች በአደባባይ እየደነፉ ነው። የትግራይ ክልል መንግስትና ሕወሃት በይፋ በፌዴራል መንግስቱ ላይ አመጸዋል። የትግራይን ህዝብ ጨምድደው እንደ ሆስቴጅ በመያዝ ፣ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በዘረፉት ገንዘብ ወሮበሎችን እየገዙ፣ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ረብሻ እንዲፈጠር ሌትና ቀን እየሰሩ ነው። ዶ/ር አብይ ግን አሁንም ወንጀለኞችን መለማመጥ ሆኗል ስራው። ጥቂት የሜቴክ ሌቦች ተይዘዋል። እርሱም ቢሆን በነ ዶ/ር አምባቸው ግፊት ነው።
 
– በቤነሻንጉል ክልል በተደጋጋሚ ነው ዜጎች እየተፈናቀሉ ያሉት። በክልሉ የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን አይበልጡም። ከአንድ ሚሊዮን በታች የሆነን ሕዝብ ሰላምና ማረጋጋት መፍጠር ያልቻለ መንግስት ነው የዶ/ር አብይ መንግስት። የቤኔሻንጉል ክልል፣ ህወሃቶች የትግራይ ሳተላይት ክልል እንዲሆን የሸነሸኑት መኖር ያልነበረበት ክልል ነው። የቤኔሻንጉል ክልል የስራ ቋንቋ አማርኛ እንደመሆኑ፣ ክልሉን ሙሉ ለሙሉ በፌዴራል አስተዳደር ስር፣ ወይንም በጊዚያዊትነት በአማራ ክልል ስር እንዲሆን ማድረግ ይቻል ነበር። ለዚህም የዶ/ር አብይ ዉሳኔ ያስፈልጋል። ዶ/ር አብይ ይሄን አይነት ዉሳኔ መወሰን አልቻለም።
 
– በአማራ ክልልም ሕወሃቶች በገዟቸው አፍራሽ ሃይሎች ችግር ተከስቶ ነበር። ሆኖም ግን እነ ጀነራል አሳምነው ጽጌ decisive የሆነ ህግን የማስከበር እርምጃ በመውሰዳቸው በምእራብ ጎንደር የተፈጠረው ችግር በቀናት ውስጥ ነው የተፈታው። በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ክልል የት ነው ቢባል የአማራ ክልል ነው።
 
– በደቡብ ክልል፣ የክልሉ አካል አንሆንም በሚል ከክልሉ ለመዉጣት ሲዳማዎች፣ ከፊቾዎች፣ ጉራጌዎች፣ ጋሞዎች ፣ ወልያታዎች ..እየጠየቁ ነው። ክልሉ ሊፈራረስ ጫፍ ላይ ነው የደረሰው። በዚሁ ሁሉ ግን አሁንም ዶ/ር አብይ ለክልሉ ራእይ የለውም። እቅዱ ፕላኑ ምን እንደሆነ አናውቅም። የክልሉ አስተዳደሪዎች ሆነ የደሃዴን መሪዎች፣ እነ ወ/ሮ ሙፈሪያት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁ አይመስልም። ያ ብቻ አይደለም በአዋሳ አክራሪ ሲዳማዎች ልክ ቄሮ እንደሚያደርገው ማሽበር ጀመረዋል፤ ት/ቤቶችን ይዘጋሉ። የአዋሳ ሕዝብ በፍርሃት ውስጥ ነው ያለው። ዶ/ር አብይ የደቡብ ክልልናና አዋሳን ዝም ብሎ የሚሆነውን ነገር እንደ ስፔክቴተር ከማየት ውጭ ሲመራ አላየንም።
 
በኔ እይታ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ከመጠን በላይ ትእግስት ያበዛ፣ የመንግስትነት ሃላፊነት መወጣት በጭራሽ ያልቻለ፣ ህግን የማስክበር ግደታዉን ለመወጣት ካለመቻሉ የተነሳም አገሪቷን ወደ መፈራረስ እየወሰዳት እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።
 
እሳት እሳት የሚባለው ሲያቃጣል፣ሲያበስል ፣ ሲያሞቅ ነው። ፓርላማ ህግ አውጭ ነው። ፍርድ ቤቱ ሕግ ተርጓሚ ነው። የሚኒትሰሮች ምክር ቤት ደግሞ ሕግ አስከባሪ ነው። የጠቅላይ ሚኒስተሩ ሁለቱ አብየት ተግባራት፣ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ሰብሳቢነትና የጦር ሃይሎች አዛዥነት ነው። ያ ማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁ ስራ አገር ማስተዳደር ህግና ስርዓትን ማስጠበቅ፣ የአገሪቷን ሕግ የሚጥሱት ለሕግ ማቅረብ ነው። ዶ/ር አብይ እነዚህን ሃላፊነቶች እየተወጣ አይደለም። አገር እያስተዳደረ ነው ለማለት ያስቸግራል።
 
እንግዲህ ስብሃት ነጋ ያለው ትክክል አይደለም ከተባለ ዶ/ር አብይ ደካማ አለመሆኑን አገር ማስተዳደርና ማረጋጋት እንዴሚችል በተግባር ያሳየን።