ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በነማን እንደሚዘወር ለማወቅ ጥናት መጀመሩን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተናገረ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በነማን እንደሚዘወር ለማወቅ ጥናት መጀመሩን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተናገረ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለው ህገ-ወጥ መሳሪያ የሚመጣበትና የሚመረትበት ቦታ የት እንደሆነም ተለይቷል የተባለ ሲሆን ወንጀሉን ለመከላከል በውጭ ጉዳይ ሚ/ር በኩል ከሃገራቱ ጋር ንግግር እንዲደረግ ውጥን ተይዟል ብለዋል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ብርሃኑ ፀጋዬ፡፡

የተጀመረው ጥናት በህገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውሩ በዋናነት ጠንሳሽና ዘዋሪዎችን እንዲሁም የገንዘብ ምንጩ ከየት እንደሆነ በመለየት ህግ ፊት ለማቅረብ እንደሚያስችል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡

ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ ምርመራቸው ተጠናቅቀው ለክስ ዝግጁ የሆኑ መዝገቦችም እንዳሉ ሰምተናል፡፡

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አቀነባባሪና የገንዘብ ምንጮችን ከማጥናት ባሻገር መሳሪያዎቹ የሚመጡበትና የሚመረቱበት ሃገራትም ስለተለዩ በሃገር ደረጃም መነጋገር ያስፈልጋል ይላሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፡፡

መሳሪያዎቹ የሚመጡት ከሱዳን፣ የሚመረቱት ደግሞ ከቱርክ ነው ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ስለ ጉዳዩ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፋፋ ያለው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የሃገርን ሰላም የባሰ ያደፈርሳል ኢኮኖሚንም ያናጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡

Sheger fm