በጎንደር ጭልጋ አለመረጋጋት መስፈኑን ፖሊስ ገለፀ

• የግጭቱ ተዋናይ ናቸው የተባሉ 59 ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
• በግጭቱ ታሳታፊ ከነበሩ ግለሰቦችም 29 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና 490 የተለያዩ ጥይችን ፖሊስ መያዙን አስታውቋል፡፡

‹‹በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙት የምሥራቅና ምዕራብ ደንቢያ እንዲሁም ጣቁሳ ወረዳዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት እየተረጋጋ ነው፡፡ በጭልጋ ወረዳ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያለመረጋጋት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡›› ፖሊስ

(አብመድ)

ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙ የጭልጋ፣ የምዕራብ እና ምሥራቅ ደንቢያ እንዲሁም ጣቁሳ ወረዳዎች ግጭት መቀስቀሱን የአማራ ብዙኃን መገኛኛ ድርጅት መዘገቡ ይወሳል፡፡

በነበረው ግጭትም በሰው ሕይወትና አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳዬው በሁከቱ ስምንት የእህል ወፍጮዎች እና 500 ያህል ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር እንየው ዘውዴ እንደነገሩን ሁከቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የፀጥታ ኃይሉ ከሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት ግጭቶቹን ለመቆጣጠር እየተሞከረ ነው፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በምዕራብ እና ምሥራቅ ደንቢያ እንዲሁም በጣቁሳ ወረዳዎች የተሻለ አንጻራዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየታዬ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
አብመድ ያነጋገራቸው በደልጊ፣ ጯሂት እና ቆላ ድባ አካባቢ ነዋሪዎችም ‹‹ምንም እንኳን ከግጭቱ በፊት እንደነበረው ባይሆንም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከሰሞኑ በተሻለ ይታያል፤ አንጻራዊ መረጋጋት አለ›› በማለት አረጋግጠዋል፡፡

ነገር ግን በጭልጋ ወረዳ ትናንት ግጭት ተከስቶ እንደነበረም ሰምተናል፡፡ በአይከል ከተማ፣ በጭልጋ ወረዳ ስር በሚገኙት አንከር አደዛ፣ ናራ አውራ አርዳ፣ ቦሆና፣ ገለድባ፣ ዳንጉራና ሌሎችም ቀበሌዎች አለመረጋጋቶች እንደነበሩ ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡ ትናንት ከምሸቱ 11፡30 ገደማ በአይከል ከተማ ግጭት ተከስቶ እንደነበር እና የሰው ሕይወት ማለፉንም አስረድተዋል፡፡

የግጭቱ ተዋናይ ናቸው የተባሉ 59 ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን፤ በግጭቱ ታሳታፊ ከነበሩ ግለሰቦችም 29 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና 490 የተለያዩ ጥይችን ፖሊስ መያዙንም ኮማንደር እንየው አስታውቀዋል፡፡
የአካባቢውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የፀጥታ አካላት ለማረጋጋት እየሠሩ መሆኑንም ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡

የመረጋጋት እንቅስቃሴ የሚታይባቸው አካባቢ ነዋሪዎች አብሮ የመኖር የቆየ ባሕላዊ እሴታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ጥረት እያደረጉ መሆኑን የገለፁት ኮማንደሩ የፀጥታ ችግር የሚታይባቸው ሌሎች አካባቢዎችም ከግጭት ሰላም የሚሻል መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

የፀጥታ ኃይሉ ሕግ የማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ኮማንደሩ የሰላሙ ባለቤት ሕዝቡ ራሱ በመሆኑ የጀመረውን የተቀናጀ ጥረት እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡