በሃይማኖት ስም ማጭበርበር ይቁም

DW
በየትኛዉም ዓለም በችግር ጊዜ አልያም በለዉጥ ወቅት ብዙዉን ጊዜ ሰዎች መንፈሳዊ መፍትሄን ለማግኘት መሻታቸዉ የታወቀ ነዉ። ረሃብ ሲመጣ ፤ ጦርነት ሲከሰት፤ ሰዎች ነገር ሁሉ ከአቅማቸዉ በላይ ሲሆን፤ ከነሱ ከፍ ወዳለዉ ኃይል ማዘንበላቸዉ እሙን ነዉ። ይህን ተከትሎ በተለያዩ ሃይማኖቶች አጭበርባሪዉ በዝቶአል።

«ማንኛዉም ግለሠብ መንፈሳዊ ሕይወቱን ማደስ ይፈልጋል። ለዚህ ዋና ማሳየዉ አድርግልሃለሁ አሰጥሃለሁ ላለዉ ሁሉ ልቡን ይከፍታል። በዚህ ይበዘበዛል ወደ አንድ አቅጣጫ ይሄዳል ወደ አልሆነ አስተሳሰብ ዉስጥ ይገባል። » ኡዝታዝ መሐመድ ፈረጅ ይባላሉ፤ በኢትዮጵያ በሃይማኖቶት ስም ስም እየተበራከተ የመጣዉን ሕገ ወጥ ተግባር አስመልክቶ ከሰጡን አስተያየት የተወሰደ ነዉ።  ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት ዓመታት በተለዩ ሃይማኖቶች  ነብይ ነን፤ አልያም አጥምቀን እንፈዉሳለን፤ ፀሎት ስናደርግ እንፈዉሳለን ፤ በሚል ተግባር ከማኅበረሰቡ ገንዘብን ጨምሮ ልዩ ልዩ ጥቅማ ቅምን በማግኘት መተዳደርያቸዉ ያደረጉ ሠዎች መብዛታቸዉ እየተስተዋለ መምጣቱን የተለያዩ እምነት ተከታዩች፤ ምዕመናን ቢናገሩም፤ ሁኔታዉን ግን በግልፅ አዉጥቶ ሲያወግዝ የሚታየዉ ሠዉ ቁጥር በጣት የሚቆጠር ነዉ። በሌላ በኩል አብዛኞች እነዚህን ሰዎች ማዉገዝ በምዕመኑ ነቀፊታይነሳብናል ሲሉ በመፍራት ሁኔታዉን አይናቸዉን ጨፍነዉ እንደሚያልፉ ይናገራሉ። ለራድዮ ጣብያችን ይህን በተመለከተ ዘጋባ ስሩልን ሲሉ ጥቆማ ያደረሱን ተከታታዮቻችን ጥቂቶች አይደሉም። በመግብያችን ላይ የሰማናቸዉ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ኡዝታዝ መሐመድ ፈረጅ፤ ነብይ ነን የሚሉና ሕዝቡን ወደ አልሆነ አቅጣጫ የሚወስዱ ሰዎች መብዛታቸዉ ዋና ምክንያት ማኅበረሰቡ የእምነቱን መሠረታዊ ነገር አለመከተሉ ነዉ ሲሉ ያስረዳሉ ።

Besenritt Hexe Grafik

« በእስላም እምነትና አስተምሮ የመጨረሻዉ ነብይ፤ነብዩ መሐመድ ናቸዉ። ከሳቸዉ በኋላ ነብይ አይመጣም።  ይህ በእንዲህ እንዳለ አስመሳይ ነብይ ነን  ባዮች ይመጣሉ ፤ አትቀበልዋቸዉ፤ አትመንዋቸዉ ፤ በአምላክ ስምም ይዋሻሉ ፤ አላህ ታየን ፤ ተገለፀልን እያሉ ይመጣሉ ሕዝብን ያወናብዳሉ እንዳትሰምዋቸዉ የሚለዉ፤ የመጨረሻዉ የቁራን መመርያ ነዉ። የመጨረሻዉ በቁራን ላይ ማብራርያ የሚሰጡት ነብይ ፤ ነብዩ መሐመድ መሆናቸዉን ቁራን ያስተምራል። የዚህ ችግር መምጣት ማኅበረሰቡ ማለትም አማኞች የእምነቱን መሰረታዊ መፀሐፍ አለመከተላቸዉን እና አለመያዛቸዉ ነዉ። በአሁኑ ሰዓት ሰዉ ወደ ዓለምአዊነት እና ወደ ቁስ በማድላቱ ነዉ። እምነቱን ይዞ መከራከር ሲገባዉ ነብይ ነኝ ብሎ ለሚያወራዉ ሁሉ እጅ መስጠቱ የሕዝቡ ችግር ነዉ። ይህን ለመከላከል የመጨረሻዉ ነብይ ፤ ነብዩ መሐመድ መሆናቸዉን የእምነቱ አባቶች ቢያስተምሩ ሕዝቡን ከዚህ ችግር ይታደጋሉ።»

በፍራንክፈርት ጀርመን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያ ካህን መሪ ጌታ ብሥራት ካሳሁን በበኩላቸዉ ፈጣሪያችን የተናገረዉ ነገር እዉን እየሆነ ይመስለኛል ብለዋል።

« የሚታየኝ ነገር አለ። ፈጣርያችን ለመጀመርያ ጊዜ የተናገረዉ አንድ ነገር አለ። ብዙ ሃሰታዉያን ክርስቶስን፤ ሃሰተኛ የሚያደርጉ፤ ብዙ ነብያቶች ይነሳሉ፤ የክርስቶስ ተከታዮች ነን፤ የሚሉ ሃሰተኞች ይነሳሉ። መምሕራን ሳይሆኑ መምር ነን የሚሉ ይነሳሉ፤ በዚህ ጊዜ ተጠንቀቁ የሚል ፤መፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰ ነገር አለ። ይህ ቃል ሊፈፀም ግድ ነዉ። ይህ መለኮታዊ ቃል ስለሆነ ጊዜዉ አሁን ያ ይመስለኛል።»

ሌላዉ በወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እንደሆኑ የነገሩን ዶ/ር ያሬድ አሰፋ ናቸዉ።  ዶ/ር ያሬድ አሰፋ በጀርመን ሲኖሩ ከ 25 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። ዶ/ር ያሬድ፤ ወቅቱ ከእምነት ከግብረገብ ሰዉን ከማክበር ይልቅ ገንዘብ የሚወዱ ሠዎች የተነሱበት ባይናቸዉ።

« እኔ የፕሮቴስታንት እምነትን በሚመለከት ነዉ የምናገረዉ። የደርግ መንግሥት ከወደቀና ይህ አዲሱ መንግሥት ከመጣ እና የእምነት ነፃነት አገኘን ከተባለ በኋላ፤ ማምለክ ትችላላችሁ ስለተባለ ሁሉም ነገር ለተወሰነ ጊዜ ጥሩ ከሄደ በኋላ መጨረሻ ላይ ለራሳቸዉ ገንዘብ የሚያካብቱ ሰዎች መነሳታቸዉ፤ ለኛ ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብም ግልጽ ነዉ። በፕሮቴስታንት እምነት ዉስጥ ይህ ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ ችግር ሆንዋል። »

ለዉጥ እና አለመረጋጋት ባለበት ወቅት ይህ አይነት ክስተት መታየቱ የተለመደ ነዉ፤ ያሉን መላዕከ ኤዶም ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ፤ ጥሰቱን የሚፈፅሙት ሰዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ታዋቂነትን የማግኘት ቀላል እድልንም አግኝተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

«በየትኛዉም ዓለም በችግር ጊዜ አልያም በለዉጥ ወቅት ብዙዉን ጊዜ ሰዎች መንፈሳዊ መፍትሄን ለማግኘት መሻታቸዉ የታወቀ ነዉ። ረሃብ ሲመጣ ፤ ጦርነት ሲከሰት፤ ሰዎች ነገር ሁሉ ከአቅማቸዉ በላይ ሲሆን፤ ከነሱ ከፍ ወዳለዉ ኃይል ማዘንበላቸዉ እሙን ነዉ። በአገራችንም ቢያንስ ባለፉት ሦስት የለዉጥ ጊዜያት ፤ በ 66ቱ በ 73 እንዲሁም  አሁንም ያለዉ ለዉጥን ተከትሎ የሃገሪቱ ሁኔታ አልረጋጋ ሲል ብቅ ብቅ የሚሉ ፤ አጋጣሚዉን የሚጠቀሙ በመንፈስ ስም፤ በሃይማኖት ስም፤ የሚመጡ ሰዎች አሉ። ይህ አይነት ክስተት በኛ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላዉም ሃገራት የተለመደ ነዉ። ግን በዚህኛዉ ዘመን በኢትዮጵያ በሁሉም እምነቶች ማለት ይችላል ነገሩ ይታያል።  በእስልምናዉም በክርስትናዉም በወንጌላዉያንም እንዲሁም በሌላዉ፤ ሁኔታዉ የተመቻቸላቸዉ ይመስላል። የዘመኑ ሁኔታኔታም ጥሩ እድል የፈጠራለቸዉ ይመስለኛል። ብዙ ዝና በአንድ ጊዜ እዉቅና እና ስማቸዉን አግዝፈዉ ሲጠቀሙ ይታያል። »

Symbolbild - Bibel

ለቁሳዊ ነገሮች ቀዳሚነትን በሚሰጠዉ ዓለም ገንዘብ ለማግኘትና ለመሰብሰብ ሰብዓዊነት መንገድ እንደሌለዉ እሙን መሆኑን የሚናገረዉ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያና ፀሐፊዉ ወጣት ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ፤ በመጀመርያ ሃይማኖትን የገንዘብ ማግኛ ያደርጋሉ ፤ ቆየት ብሎ ደግሞ ራሱን ሃይማኖቱን ገበያ ያደርጋሉ፤ ሲል ገጠመኙን ያስረዳል።

«መጀመርያ አካባቢ ሃይማኖትን እንደ ገንዘብ ማግኛ የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ። ከዝያ ሲብስ ደግሞ ሃይማኖቱን ራሱ ገበያ አድርገዉ መጠቀም የሚጀምሩ ብልጣብልጥ ሰዎች ይኖራሉ። የህዝቡን አመለካከት የርዕዮተ ዓለም አለመስፋት በመረዳት ሃይማኖት ማዕቀፍ ዉስጥ ለመክተት ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ ቁሳዊና የገንዘብ ፍላጎታቸዉን ለማሟላት የሚጥሩ ሰዎች ይታያሉ። ይህ እኔ በአጠናሁት የስደት መንገድ እንኳ የተወሰኑ ሰዎች ሃይማኖትን ተገን አድርገዉ ሰዎችን ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የመላክ ነገር ሲያካሂዱ ታዝቤያለሁ። የሰዎቹ ዋና ዓላማ ደቡብ አፍሪቃ መግባት ሳይሆን ልጆቹን ወድያ ሲልኩ የሚያገኙት ገንዘብ ነዉ። እዝያ ከሄዱ በኋላ የተለያዩ ነገሮችን በመክፈት ስደተኞች እነሱ ጋር እየሄዱ ስብከት እንዲሰሙ ከሚያገኙት ገንዘብም መዋጮ እንዲያደርጉ እያደረጉ በዚህ መንገድ ገንዘብ ይሰበስባሉ። ይህን የሚያደርጉ በርካታ ሰዎች አሉ። ምናልባት ይህ አይነቱ ሁኔታ የተከሰተዉ ለዉጥ ሂደት ላይ ስላለን ይሆናል ጊዜዉ ምስቅልቅል ጊዜ ነዉ። ይህን ምስቅልቅል እና ክፍተት በመጠቀም በጣም ብዙ ሰዎች ሃይማኖትን ተገን አድርገዉ ቁሳዊና የገንዘብ ፍላጎትን ለማሟላት  በሃይማኖቱ ስም መነገድ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖቱን ራሱ የገበያ ማዕከል እያደረጉት መሆናቸዉን በተወሰነ መልኩ ለመታዘብ ችያለሁ። »

በተለያዩ ሃይማኖቶች ዉስጥ በሐይማኖት ሥም የሚነግዱ ሰዎችን እንዴት ማስቆም ይቻል ይሆን? ኡዝታዝ መሐመድ ፈረጅ፤ « እምነት መጽሐፍ ላይ ያለ መመርያ ነዉ። ከዛ ወጣ ያለ ነገር ሲመጣ ይህ እምነታችን ዉስጥ የለም ብሎ መከራከር ሲገባ፤ ለሚናገር ሰዉ ሁሉ እጅ መስጠቱ ትልቅ ክፍተት እና የሕዝቡ ችግር ነዉ። ይህን ለመቅረፍ በተገኘዉ መድረክ ሁሉ የመጨረሻዉ ነብይ ፤ ነብዩ መሐመድ መሆናቸዉን የእምነት አባቶች በሰፊዉ ቢያስተምሩ ሕዝቡን ከዚህ ችግር ይታደጉታል። በሌላዉም እምነት ቢሆን መጽሐፍ አለዉ። ከመጽሐፉ ወጣ ያለ አስተሳሰብና ተናጋሪ ሲመጣ ይህ ትክክል አይደለም መጽሐፉ ዉስጥ የለም ብሎ መከራከር ቢችል አይጠቃም። ስለዚህ የእምነት አባቶች በዚህ ዙርያ እንዲያስተምሩ አደራ ስል እጠይቃለሁ።  መንግሥትም ለመሰረታዊ እምነቶች እና ትክክለኛ እምነት አስተምሮ ለሚሰጡ ተቋማት ድጋፍ መማድረግ ፤ ምልጃን በመስጠት ሕዝቡን ካላአስፈላጊ አስተሳሰብ እንዲታደግ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይገባል እላለሁ። »

መላዕከ ኤዶም ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ በበኩላቸዉ የሃይማኖት አባቶች ሃገር የሚሰማቸዉ ሽማግሌዎች ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

« ችግሩ በኛ ሃገር ብቻ የሚታይ ሁኔታ አይደለም። በዚህም ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም። ምናልባት መቀነስ ይቻል ይሆናል። ምክንያቱም የሰዉ ልጅ ስለልቦና በችግር ጊዜ መንገድ የሚያሳይ ሰዉ ስለሚፈልግ ለመታለል ዝግጁ ነን። በሃይማኖቱ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዉም የተለመደ ነዉ። ብዙ ሰዉ ለመታለል ቀላል ነዉ ፤ ከተታለለ በኋላ ወይም የተሳሳተ መረጃን ከተቀበለ በኋላ ፤ ያ ነገር ስህተት ነዉ ብሎ ለማስተካከል ብዙ ጊዜን ይወስድበታል። በኛም ሃገር ያለዉ ሁኔታም እንደዝያ ይመስለናል። በተለይ በእምነት ሰበብ ለሚመጣ ሰዉ፤ የሁሉ ሰዉ ልቦና ክፍት ነዉ። ስለዚህ እንደዚህ አይነቱን የማጭበርበር ሁኔታ መቀነስ ይቻል፤ እንደሆነ ነዉ እንጂ ማቆም የሚቻል አይመስለኝም። ለቅነሳዉ ርዳታ ማድረግ የሚቻለዉ፤ አንደኛ በመንግስት ደረጃ ትብብር ይፈልጋል። ሁለተኛ በየቤት እምነቶች ያሉ የተጠሪዎችን ትብብር ይፈልጋል። በሦስተኛ ደረጃ፤ ሕዝቡ የሚሰማቸዉ የሃገር ሽማግሌዎችን ፤ ቅቡልነት ያላቸዉን ሰዎች ትብብርንም ይፈልጋል። እነዚህ አካላት የሚቀናጁ ከሆነ፤ እንደዚህ አይነት የማጭበርበር ጉዳዮችን መቀነስ ይቻል ይሆናል። »

ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ጊዜዉ ያልተረጋጋ ሠዓት ላይ ስላለን ነዉ እንጂ፤ ነገሩ ይቆማል ያሉን መሪ ጌታ ብሥራት ካሳሁን፤ ዉሸት መጀመርያዉ አይታወቅ እንጂ ዉሸት መጋለጡ አይቀሬ ነዉ ብለዋል።

Deutschland Gottesdienst alte Menschen

« ይህን የማጭበርበር ጉዳይ ለመግታት በቤተ-ክርስትያኒቱ ዙርያ ብዙ ነገር ይደረግ ነበር፤ አሁንም እየተደረገ ነዉ። ለምዕመኑ በትምህርት መልክ እየተሰጠ ነዉ። ግን አጠቃላይ ቤተ-ክርስትያኒቱ እንደ አቋም ወስዳ የተንቀሳቀሰችበት ነገር አለ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ይህ የማጭበርበር ጉዳይ እዚህም እዝያም ብልጭ ሲል ይታያል፤ ግን ብዙም ቦታ የተሰጠዉ አይመስለኝም። የኛም ችግርና ስህተት እሱ ላይ ነዉ። ምዕመኑ እንዲጠነቀቅ ማድረግ ይገባል። አንዱ ሲፈቅድ አንዱ ይቃወማል ፤ አንዱ አይደለም ሲል አንዱ ትክክል ነዉ ይላል። እና ይህን መሰል ችግርም አለብን። ከዚህ በኋላ ግን ይህ ይቀጥላል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ነብይ ነን የሚሉት ሃሰተኞች ናቸዉ ። እዉነተኞች አይደሉም ስለዚህም ይቆማል። እንዳልኩት ይህ የግርግር ጊዜ ስለሆነ ግርግሩ እየተረጋጋ ሲመጣ ቆሞ ብሎ ማየት ይችላል። አታላዮችም ሁል ጊዜ ቤተ-እምነትን ተጠግተዉ በማታለል መዝለቅ አይችሉም። ይህ አገርንም የሚጎዳ ጉዳይ ነዉ። ሕዝቡም ሃገራዊ ራዕይ እንዳይኖረዉ ፤ ተስፋ እንዳይኖረዉ ያደርጋል።  በእምነትም ቢሆን ተስፋን የሚያሟጥጥ ነገር ነዉ። ሕዝቡ እየተጎዳ ነዉ ። ይህን መንግሥትም ቢሆን ወደፊት ሲስተካከል ዝም የሚለዉ አይደለም። ዉሸት መቼም መቆምያ አለዉ አንድ ቀን። ዉሸት መነሻዉ ነዉ የማይታወቀዉ እንጂ ፤ መድረሻዉ ይታወቃል፤ እናም ይቆማል።»

በወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የሆኑት ዶ/ር ያሬድ በበኩላቸዉ መንግሥት ጣልቃ ሊገባ ይገባል ባይ ናቸዉ። ወጣቱ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያና ፀሐፊ ወጣት ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ በበኩሉ የኃይማኖት ተቋማትም ሆነ ሚዲያዎች ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ሊሰጡ ይገባል ሲል ያጠቃልላል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE