የአማራ ክልል ምክር ቤት የሀዘን መግለጫ እንዳያወጣ በአፈጉባኤዎቹ ታገደ

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሀዘን መግለጫ እንዳያወጣ በአፈጉባኤዎቹ መታገዱን አስመልክቶ ሙሉቀን ተስፋው የሚከተለውን ጦማር ከትቧል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሀዘን መግለጫ እንዳያወጣ በአፈጉባኤዎቹ እንደታገድ ስንቶቻችን እናውቃለን ? ብዙ ሰው የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ አቶ ታደሰ ጫፎ ብቻ አፈና ያደረገ ይመስለዋል። አይደለም ።
በወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ዋና አፈ ጉባኤነትና አቶ አማረ ሰጤ ምክትል አፈጉባኤነት የአማራን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው ምክር ቤት እስካሁን የሃዘን መግለጫ አላወጣም። አንዳንድ ለሕዝብ የሚቆረቆሩ የምክር ቤት አባላት የሀዘን መግለጫ ለማውጣት፣ ጭፍጨፋውን ለማውገዝ ቢፈልጉም በአፈጉባኤዎቹ በመታፈኑ ምንም ማድረግ አልተቻለም።
እንግዲህ ይህ ምክር ቤት ነው የአማራ ሕዝብ ወኪል!
ጉዳት የደረሰው በሌላ ብሄር ብሔር ቢሆን ኖሮ እነ ወይዘሮ ፋንቱ የአዞ እንባ ለማውረድ ማንም አይቀድማቸውም ነበር። አበልና ጥቅማጥቅም ለማሳደድ ማንም የማይቀድማቸው ሰዎች የሕዝብ ደም እንደጎርፍ ሲፈስ ተጎጂው አማራ ስለሆነ ሰምተው እንዳልሰሙ አልፈውታል። እወክላለሁ ብሎ የሚለው ህዝብ ሲጨፈጨፍ ባላዬ የሚያልፍ ምንአልባት የአማራ ክልል ም/ቤት በዓለም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም።
እንስሳት እንኳ ለወገናቸው ይቆማሉ፤ የሕወሓት ቅሪት የሆኑ ሰዎች የነገሱበት ም/ቤት ግን ”የተሰማንን ሀዘን ገልፀናል” በሚል የሽንገላ ቃላት እንኳ ማስመሰል አልቻለም።