በሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

በሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ።
ቀን፡- ሰኔ ፲፯ ፳፻፲፬ June 24 2022
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
“እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም” መ መክብብ ፬፤ ፩
ቀዳሚት ታሪካዊት የሆነች ሀገራችን ኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተከባብሮና ተዋዶ የኖረባት በጋራ ጠላት ሲመጣም በጋራ ተከላክሎ ሀገርን ከነ ድንበሩ ያስከበረ ሕዝብ የኖረባት ሀገር ናት። ከዓለም መንግሥታት በታሪክ፤ በእውቀት፤ በጥበብ ቀዳሚ ከነበሩት መካከልም ተጠቃሽ ነበረች። ይሁን እንጂ የሀገራችን የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ በየጊዜው ቢቀያየር የእውቀት፤ የእድገት ለውጥ ሳይታይ በተቃራኒው ጦርነት፤ ረሃብ፤ ችጋር የሚፈራረቅባት ከሆነች አርባና ሃምሳ ዓመታት በላይ እየተቆጠሩ ነው።
ይልቁንም በሀገራችን በጎሳ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ሥፍራውን ከያዘ ጀምሮ በአንድነት የኖረውን ማኅበረሰብ በጎሳ በቋንቋ በመከፋፈል ለከፋ ጉዳት መጣሉ የታወቀ ነው። በተለይም ከዛሬ አራት አመት ወዲህ የሕወሃት መንግሥት ከቦታው ሲወገድ “ለውጥ ይመጣል ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ ተስፋ ተነሥቶ እንደ ነበር የትናንት ትውስታችን ነው። ነገር ግን ተስፋው ቀርቶ መከራው እጥፍ ሆኖ መታየት የጀመረው በማግሥቱ ነበር። ይህው ጥላቻና የሥልጣን ሽኩቻ ወደ ጦርነት አምርቶ በመቶ ሺህዎች ኢትዮጵያውያን ያለቁበት፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለመፈናቀል ለስደት ለረሃብ ለችግር የተጋለጡበት ጦርነት ዛሬም ድረስ እልባት አላገኘም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ያለፉት አራት ዓመታት ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ መልኩ የሰው ልጅ በማንነቱ እየተመረጠ ከመገደል ያቆመበት አንድም ቀን የለም። በተለይም በኦሮሚያ፤ በቤኒሻንጉል በጋምቤላ ክልል አማራ በመሆናቸው በሚል፤ ተወልደው ባደጉበት በሀገራቸው እንደ ሌላ ሀገር ዜጋ ታይተው ከዋሉበት እንዳያድሩ ካደሩበት እንዳይውሉ ሕጻን፤ አረጋዊ፤ ሴት ሳይሉ የሰው ልጅ እንደ አራዊት ተጨክኖባቸው በጥይት እየተደበደቡ፤ በገጀራ እየተቀሉ በጩቤ የተወጎ በመግደል ላይ ናቸው።
ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በኦሮሚያ ከልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰ የዘር ማጥፋት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው በኦነግ ታጣቂዎች ያለማንም ከልካይ ይልቁንም በመንግስት ቀጥታ ትእዛዝና እገዛ በግፍ በጥይት ተደብድበው፤ በስለት ተቆራርጠው በእሳት ታቃጥለው አልቀዋል።
በአሁኑ ወቅት አቤት ተብሎ የሞጮህበት መንግሥት ብሎም የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት የሚጠብቅ አካል _ አለ ለማለት አያስደፍርም። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር በአርአያው የፈጠረው የሰው ልጅ በየዱሩ እየወደቀ ሲሆን ሀገራችን የንጹሐን ዜጎቿ ደም እንደ ጅረት በየቀኑ እየፈሰሰ ርኩሰት ምድሪቱን እስከ አንገቷ ሞልቷታል።
የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ግፍና ሰቆቃ ከማውገዝ ከመቃወም ያቆመበት ጊዜ የለም። አሁንም ወደ እግዚአብሔር ከመጮህ በላይ ትልቅ ነገር ባለመኖሩ የአቤልን፤ የዘካርያስን ደም የተቆጣጠረ አምላክ ለንጹሐን እንዲደርስላቸው ጸሎታችን ነው። በዚህ የዘር ማጥፋት ሕይወታቸውን ላጡት ሁሉ እግዚአብሔር የሰማዕታትን ዋጋ እንዲሰጣቸው ነፍሳቸውንም በቅዱሳት እቅፍ ያሳርፍልን እያልን ለወዳጅ ዘመድ፤ በሩቅና በቅርብ የሐዘኑ ተካፋይ ለሆናችሁት ኢትዮጵያውያን ሁሉ መጽናናቱን ይስጥልን።
ከሞት የተረፉ ወገኖቻችን እረኛ እንደ ሌለው መንጋ በየዱርና ገደሉ እያታደኑ ሲሆን የሃይማኖት ተቋማት በጉዳቱ ቦታ ድረስ በመገኘት ችግሩን በማየት ለሕያዋን እንዲደርሱላቸው፤ የሞቱትንም በክብር እንዲያርፉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አቅሙና ችሎታው ያለው አካላት በመረባረብ ማትረፍ እንዲችሉ፤ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰላም በጋራ ለመኖር ይህንን የደም መፍስሰ በቃ የሚልበት ጊዜው አሁን መሆኑንም ማስገንዘብ እንወዳለን። ሆኖም ግን አሁንም ይሁን ላለፈው የንጸሐን ዜጎች ጥቃት መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል። እግዚአብሔር በምሕረት እስኪጎበኘን ግፋኞችንናን ግፍን መቃወም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሲሆን ለተጎጂዎች በሚደረገው በጎነትና ርዳታ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ እናሳስባለን።
ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር
የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት ጽ/ቤት
ሰሜን አሜሪካ
May be an image of text