ቶሌ መንደር ውስጥ የተፈጸመው የጭካኔ ግድያ እና የነዋሪዎች በጥቃቱ ምክንያት ተገድዶ መፈናቀል ዘግንኖኛል – የተመድ ከፍተኛ ባለስልጣን

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመውን «አሰቃቂ» የጅምላ ግድያ ላይ ባለሥልጣናት ፈጣን፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጠየቀ። «ቶሌ መንደር ውስጥ የተፈጸመው የጭካኔ ግድያ እና የነዋሪዎች በጥቃቱ ምክንያት ተገድዶ መፈናቀል ዘግንኖኛል» ያሉት ሚሼል ባችሌት ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓም ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት የዓይን ምስክርን ባልደረባቸው እንዳነጋገሩ እና ወደ መንደሩ የገቡት ታጣቂዎች በነሲብ ተኩስ ከፍተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደገደሉ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን እንዲሁም ቢያንስ 2000 ሰዎች ከአካባቢው ለመሸሽ መገደዳቸውንም አመልክተዋል። አራት ሰዓት በፈጀው ጥቃትም ታጣቂዎቹ በሰዎች ላይ ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪም በርካታ ቤቶችን ማቃጠላቸውንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊዋ መግለጫ ዘርዝሯል። ከጥቃቱ የተረፉት ወገኖች ለሰዓታት ከደረሰው ጥቃት በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ጎሳ ተወላጆች መገደላቸውን አስከሬን አሁንም በመንገዶች ላይ ወድቀው ሊገኙ እንደሚችሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ የዜና ወኪል ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ጥቃቱ በኦሮሞ ነጻነት ጦር፤ መንግሥት አሸባሪ ባለው ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መፈጸሙን ይናገራሉ።

ሆኖም የታጣቂው ቡድን ቃል አቀባይ በበኩሉ ጥቃቱ በመንግሥት ደጋፊ ሚሊሻዎች ነው የተፈጸመው በሚል በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥሪ ማቅረቡን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ኃላፊ ሚሼል ባችሌትም ዛሬ ባወጡት መግለጫ «ጥቃቱ በአፋጣኝ መጣራቱን እንዲያረጋግጡ፤ ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው እውነት፣ ፍትህ እና ካሣ የማግኘት መብታቸውን እንዲሁም አጥፊዎችን በተጠያቂነት መያዛቸውን እንዲያረጋግጡ» ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በጥቃቱ ወቅት መታገታቸውን እና ያሉበት እንደማይታወቅም አጽንኦት ሰጥተዋል። ለዚህም የመንግሥት ባለሥልጣናት የታገቱት ወገኖች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ አስፈላጊ እና ሕጋዊ ርምጃዎችን እንዲወስዱም አሳስበዋል።