በ9 ወር ግማሽ ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተናገረ

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በ9 ወር የስራ ጊዜው ግማሽ ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ተናገረ፡፡

ገቢው ከእቅድ በላይ ነው የተባለ ሲሆን 75 በመቶ የኢትዮጵያ ድርሻ ይሆናል ተብሏል፡፡

ቀሪውን 25 በመቶ ደግሞ በውሉ መሰረት የጅቡቲ ድርሻ እንደሚሆን ሰምተናል፡፡
የኢትዮ ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ ለሸገር እንደተናገሩት አብዛኛው ገቢ የተሰበሰበው የጭነት አገልግሎት በመስጠት ነው፡፡

በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ከጅቡቲ ሞጆ ድረስ በየቀኑ 53 ፉርጎዎችን የሚጎትት 1 ባቡር ብቻ ይገባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ግን ከጅቡቲ ጭነት የሚያመላልሰውን ባቡር ሁለት በማድረግ በቀን 106 ኮንቴይነር ወደ ሞጆ በማመላለስም ገቢውን ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ሐዲድ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ የብድር ገንዘብ የተገነባ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በሌላም በኩል አገልግሎቱን ለ6 አመት የማስተዳደር ስራ በኮንትራት ለወሰደው የቻይና ኩባንያ በአመት ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

እንዲህ ያሉ ወጪዎች እያሉበት ከገቢው አንፃር አገልግሎቱ ብድሩን ለመክፈል ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል ያልናቸው ኢንጂነር ጥላሁን የጭነት አገልግሎቱን በሰፊው መስጠት ከተቻለ ከ5 አመት የበለጠ ጊዜ ላይወስድበት ይችላል ብለዋል፡፡

ይሁንና በቂ ጭነት የማይገኝበት ጊዜ ስለመኖሩ ጠቁመው ከወደብ መኪኖቹንና ሌሎችንም የግለሰብ ነጋዴዎች ጭነቶችን ለማመላለስ የሚያስችሉ ፉርጎዎች ቢኖሩንም ግለሰቦች ከባቡሩ ይልቅ በጭነት መኪኖች ማመላለስን በመምረጣቸው እስካሁን ይሄንን ስራ አልጀመርንም ብለዋል፡፡

በቅርቡ ግን የጭነት አገልግሎቱን ከመንግስት ገቢና ወጭ ንግድ እቃዎች ባሻገር ለግለሰብ ነጋዴዎችም ጭምር ለመስጠት እቅድ ይዘን እየሰራን ነው ሲሉ ኢንጂነር ጥላሁን ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ያገኘው የ5 መቶ ሚሊየን ብር ገቢ ከእቅዱ በላይ ቢሆንም በሌላ በኩል በሚደርሱ ተደጋጋሚ አደጋዎች ምክንያት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉ ይታወቃል፡፡

Sheger fm


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE