ተማሪዎች ለአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ኃላፊነታቸው መወጣት እንደለባቸው ተገለጸ

ተማሪዎች ለአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ኃላፊነታቸው መወጣት እንደለባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፦ ተማሪዎች የአገሪቱን አንድነት በመጠበቅ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን በኩል ድርብ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም ገለጹ፡፡

ከመላው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጡ ከ600 በላይ ተማሪዎች ትናንት የፌዴሬሽን እና የተወካዮች ምክር ቤቶችን ሲጎበኙ ወይዘሮ ኬርያ እንዳሉት፣ኢትዮጵያ የቋንቋ፣ የእምነት፣ የባህል እና የሌሎችም በርካታ ሕብረ ብሔራዊ ውህድ ናት፡፡ በመሆኑም ተከባብሮ በፍቅር መኖር አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከሕፃንነት ጀምሮ መገንባት አለበት፤ ይህ መሆን ሲችል ብዝሃነት የአንድነት ምንጭ እንጂ ፈጽሞ ሥጋት ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለማንም የማይበጅ ብሎም ለሰላምና ብልጽግና ጠንቅ በመሆኑ ሁሉም ወገን ሊያወግዘው እንደሚገባ አፈ ጉባኤዋ አሳስበው፤ ተማሪዎችም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ተማሪዎዎቹ ሕገ መንግሥቱን በልጅ ነታቸው በተገቢው መንገድ አውቀው ሲያድጉ ተግባራዊ ለማድረግ አይቸግራቸውም፤ አገራዊ ፍቅራቸው ይጨምራል ያሉት ወይዘሮ ኬርያ፣በተመሳሳይም የሕግ ጥሰትን ማስከበር የሚችል ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬን እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በበኩላቸው የተማሪዎቹ ጉብኝት ብሔሮችና ብሔረሰቦችን እርስ በእርስ ከማስተዋወቁ ባሻገር ቋንቋ፣ ባህልና ወግን ለመለዋወጥ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ በዚህ አጋጣሚ ያዩትንና ያገኙትን ተሞክሮ በየአካባቢያቸው ሲመለሱ ለበርካታ ተማሪዎች ከማካፈል በተጨማሪ የሰላምና የአንድነት አምባሳደር መሆን እንደሚገባቸው ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎቹ የቀጣዮቹ ፓርላማ ተረካቢ ትውልድ እንደመሆናቸው መጠን ለዚህ ሕዝባዊ ኃላፊነት ለመብቃት በትምህርታቸው በርትተው እንዲተጉ አስገንዝበዋል፡፡
ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ለማ ድሳሳ በበኩሉ፣በልምድ ልውውጡ ኢትየዮጵያ እውነትም የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አገር መሆኗን በተግባር ማየት መቻሉን ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች የሚያውቀውን የፓርላማ የአሠራር ሥርዓት በተግባር ገለጻ በቦታው ተገኝቶ ማግኘቱ እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡
በጉብኝቱ የቀሰመውን ልምድ በሚኖርበት አካባቢ በሰፊው እንደሚያካፍል የገለጸው ወጣት ለማ፣ ተማሪዎች በአገርህን እወቅ አማካኝነት ከልጅነታቸው ጀምሮ ማየትና አገራቸውን ማወቅ እንደሚገባቸው ተናግሯል፡፡

በአጠቃላይ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጉብኝት ፕሮግራም በተማሪዎቹ ዘንድ መነሳሳትን ከመፍጠሩም በተጨማሪ ከነወላጆቻቸው የጉብኝቱ አካል መሆናቸው ይበልጡን ጉጉታቸውና ፍላጎታቸው እንዲጨምር አድርጓል፡፡

በፌዴሬሽንና በተወካዮች ምክር ቤቶች የጉብኝት መርሐግብር መሰረት ዛሬ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት ‹‹ኑ የሠላም ቡና ጠጡ ›› ፕሮግራም በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE