ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፤

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ትግል በአማራ ሕዝብ ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመቀልበስ ለዚህ መሰረት የሆነውን የሀሰት ትርክትንና የኢትዮጵያን የፖለቲካ አውድ ዝንፈትን በማስተካከል እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለዚህም ከምስረታ ጀምሮ ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የአመራር ድክመቶችና የትግል መስመር ጥሰቶች ታይተዋል፡፡ በዚህም በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የሚገኙ አመራሮችና አባላት ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በተሟላ ሁኔታ ኃላፊነቱን ያለመወጣት፣ ተከታታይ መደበኛ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ወቅታቸውን ጠብቀው አለመካሔድ፣ ድርጅታዊ እቅድ በወቅቱ ተዘጋጅቶና በሚመለከተው አካል ፀድቆ ወደታችኛው መዋቅር ያለመውረድ፣ ያለድርጅታዊ ውሳኔ ድርጅት ዘለል ግንኙነቶችና ትብብሮችን ማከናወን፣ በየደረጃው ባለው የአስፈፃሚ አካል መካከል ተዋረዳዊ ግንኙነት መቋረጥ፣ የዲሲፕሊን ችግሮች እና የመሳሰሉት የህገ ደንብና የመርህ ጥሰቶችን እንዲሁም የአፈፃፀም ጉድለቶችን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከመጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔ ጀምሮ ከቀን ወደ ቀን ድርጅትን የሚያፈርሱና ትግልን የሚበትኑ አካሄዶች እየጎሉ መምጣታቸው እየታየ ነው፡፡

ለዚህም
1) በመጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ሲካሄድ የነበረው ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጠራ በመሆኑ የሪፎርምም ሆነ ሌሎች ቦርዱ ከሰጣቸው አጀንዳዎች ውጭ መታየት እንደማይችሉ በሰብሳቢዎች (የድርጅት ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበር) እንዲሁም የድርጅቱ የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ በመግለፅና ጉባዔተኛው በማፈን ከባድ የዲሲፕሊን ጥሰት መፈፀምና ድርጅቱን ከባድ አደጋ ላይ መጣል፤
2) መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔውን ሰብሳቢዎች ረግጠው በመውጣትና በመበተን ድርጅቱን የማፍረስ አደገኛ እርምጃ መውሰዳቸው፤
3) የድርጅቱ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ከድርጅታዊ ጉባዔ በፊትም ሆነ በኋላ ጉባዔው ውሳኔዎችን ከማሳረፉ አስቀድሞ በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው የተዛቡ እና ከድርጅት ውሳኔ ውጭ የሆኑ አንጃ ፈጣሪ መልእክቶችን ማስተላለፋቸው፤
4) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጠቅላላ ጉባኤው ተወካይ ኮሚቴ በኩል በቀረበው አቤቱታ መሰረት ማስረጃዎችን በመመርመር ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/586 ለአብን በተጻፈ ደብዳቤ የተቋረጠው ጉባዔ ተጠርቶ ሪፎርም እንዲደረግ ቢወስንም የድርጅቱን ማህተም ማግኘት የቻለው አካል ያለድርጅቱ ውሳኔ ስልጣኑን ያለአግባብ በመጠቀም ጉባዔው ለ6 ወራት ይራዘም ብሎ የምርጫ ቦርዱን በመጠየቅ ከባድ የዲሲፕሊን ጥሰት መፈፀሙና ድርጅቱን አደጋ ላይ መጣሉ፤
5) በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚያዚያ 21 – 22 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደው የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ያለውጤት ሲበተን ህጋዊ የሆነ “የጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅና የሪፎርም ኮሚቴ” እንደተቋቋመ ተደርጎ እየተወራ ድርጅቱ አደጋ ላይ እንዲወድቅ መደረጉ፤
6) የድርጅቱን ማህተም ማግኘት በቻለው አካል ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር አብን361/2014 በተፃፈ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርዱ የጉባዔ ማራዘሚያ ተገቢነት የሌለውና ህጋዊ ያልሆነ ጥያቄ በማቅረብ ድርጅቱ አደጋ ላይ እንዲወድቅ መደረጉ፤
7) ለምርጫ ቦርዱ በቀረበው የጉባዔ ማራዘሚያ ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/640 ለአብን በጻፈው ደብዳቤ አለመቀበሉንና በበፊቱ ውሳኔ መሰረት ድርጅቱ እስከ ሰኔ 18 ባለው ጊዜ ጉባኤውን እንዲያካሂድ ቢገልፅም የሚመለከታቸው አካላት ለጉባዔ ባለመዘጋጀትና ዝም ብለው በማየት ድርጅቱ አደጋ ላይ እንዲወድቅ መደረጉ፤
8) ድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ኦዲትና ምርመራ ኮሜሽን ጉባኤውን ለመጥራት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ካለማድረጋቸውና ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች በመነሳት የአብን ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤው የተቋረጠው ጉባዔ እንደገና ተጠርቶ ሪፎርም ተሰርቶና የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ተፈፃሚ ሆኖ ጉባዔው እንዲጠናቀቅና ድርጅቱ ካጋጠመው አደጋ እንዲወጣ በፊርማ የተረጋገጠ ውክልና ሰጥቶ የጉባዔ ዝግጅት ስራዎችን በአብን የጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ አማካኝነት እያከናወነ ቢገኝም የተለያዩ አካላት ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው ተግዳሮት እየፈጠሩ ድርጅቱ ለበለጠ አደጋ እንዲጋለጥ መደረጉ፤
ዋና ዋናዎቹ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ስለሆነም አንዳንድ አመራሮቹ ንቅናቄያችን መሰል አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ ተገቢውን የክንውን፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ አለመስራታችሁ ሳያንስ፤ ከድርጅታችን መነሻ የትግል ግቦችና ከጠቅላላ ጉባያተኛው በተቃርኖ አንጃ በመፍጠር ንቅናቄው እንዲፈርስ እየተንቀሳቀሳችሁ የምትገኙ ከፍተኛ አመራሮችም ከእልህና እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል አቋም ተፋታችሁ፤ ለትናንት የጋራ ትግላችን፣ በህልውና አደጋ ላይ ላለው ሕዝባችንና ለራሳችሁም የዛሬ በጎ ተሳትፎና የነገ ታሪክ ጭምር ስትሉ ድርጅታዊ ጉባኤው በስኬት እንዲካሄድ መተባበርና በጉባዔው ውስጥ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባችኋል። ጠቅላላ ጉባዔው እንደድርጅታችን የበላይ የሥልጣን አካል ለሚወስናቸው ውሳኔዎችም ተገዥ እንድትሆኑ በጥብቅ እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቀርቶ አብን ላይ ለሚከሰት የባሰ አደጋ ግን የታሪክና የትውልድ እዳው በእናንተ ላይ እንደሚወድቅም በአጽንዖት ማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የምትገኙ አባላትና አመራሮች እንዲሁም የአማራና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚገዳችሁ በጎ ኃይሎች ሁሉ፤ አብን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠለት ቀነ ገደብ ጉባዔው እንዳይካሄድ እንቅፋት እየፈጠሩ በሚገኙ ውስን የንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች ላይ በምትችሉት ሁሉ ወንድማዊ ምክር በመለገስ ከእውነቱ ጎን እንዲቆሙ በማድረግና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በመስጠት በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የአብንና የአማራ የትግል እንቅስቃሴ ጠንክሮ እንዲቀጥል በጎ አሻራችሁን ታስቀምጡ ዘንድ እንጠይቃለን።

የጠቅላላ ጉባዔው አባላት፣ ሌሎች የድርጅታችን አመራሮችና አባላት እንዲሁም በአገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ ደጋፊዎች በሙሉ የአብን የጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴው የተቋረጠው 3ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ እንደገና ተጠርቶ እንዲጠናቀቅ በምርጫ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ከማድረግ እንዲሁም ለድርጅቱ ጽ/ቤት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከመጠየቅ ባለፈ ለቦርዱ የደንብ ማሻሻያ ረቂቅን የማቅረብ፣ ወኪሎቹን ልኮ እንዲታዘብ ጥሪ የማድረግ፣ የጉባኤ ቀንና ቦታ የማሳወቅ እና ሌሎች የዝግጅት ተግባራትም መከናዎናቸውን ተገንዝባችሁ ለጉባዔው ስኬት የበኩላችሁን አስተዋፅኦ በማበርከት ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን ትወጡ ዘንድ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

የአብን ጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ ኮሚቴ