በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም ኢሳያስ ዳኘው፣ ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት ያሬድ ዘሪሁን፣ ተስፋዬ ኡርጌ፣ የኢትዮ ቴሌኮም የሴኪዩውሪቲ ዲቪዥን ኃላፊ  የነበሩት ኮሎኔል ጉደታ ኦላና እና ሌሎች ሦስት ተጠርጣሪዎች ናቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት

ተጠርጣሪዎቹ በዛሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ነው የቀረቡት።

ፍርድ ቤቱ በበለስ አንድ ፕሮጀክት ያለአግባብ ለሁለት የውጭ ድርጅቶች የግንባታ ውል በመስጠት ከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሃብት እንዲባክን በማድረግ የተጠረጠሩት ኮሎኔል አሰፋ ዮሃንስ ላይ ፖሊስ የቀረውን ምርመራ አጠናቆ እንዲያቀርብ 10 ቀን በመስጠት ለታሳስ 5 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የአቃቢ ህግ ክስ በማደናቀፍ እና ተገቢ ያልሆነ ሃብት በማከማቸት ወንጀል የተጠረጠሩት በኮለኔል ጉደታ ኦላና ላይ ፖሊስ ከጀመረው ምርመራ በተጨማሪ ቀሪ ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ከህዳር 20 ጀምሮ በሚቆጠር የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዶ ለታሳስ 4 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከአዲስ የሜቴክ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥሮ ከሁለት የውጭ ድርጅቶች 2 ሺህ 500 ትራክተር በድለላ በመግዛት ከ15 ሚሊየን በላይ ለግላቸው አውለዋል የተባሉት አቶ ረመዳን ሙሳ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፥ ፖሊስ የተጠረጠሩበትን ጉዳይም አስረድቷል፡፡

አቶ ረመዳን ሙሳ ላይ ፖሊስ ሦስት ምስክር የተቀበለ ሲሆን፥ የኦዲት እና ትራክተሮች ቆጠራ ለማድረግ  ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ጠይቋል፡፡

ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ፖሊስ ሰነድ ሰብስቧል በዋስ ቢወጡ የሚፈጥሩት ጉዳት የለም ብለዋል፡፡

ሆኖም ፖሊስ በተከላካይ ጠበቃ የቀረበውን ዋስትና ተቋውሟል።

ፍርድቤቱም የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ለነገ ከሰዓት ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

እንዲሁም ፖሊስ በቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው ምርመራ ጊዜ ውስጥ በባለቤታቸው ወይዘሮ አዳነች ስም አገኘሁ ያለውን ሃብት ዘርዝሯል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE