የቴዲ አፍሮ ባለቤት አምለሰት ሙጬ ለ200 ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሰጠች

አርቲስት አምለሰት ለ200 ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሰጠች

አርቲስት አምለሰት ሙጬ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው 200 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሰጠች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ህጻናትና ጉዳይ ቢሮ አዳራሽ በተደረገው ርክክብ ላይ አርቲስት አምለሰት እንዳለችው፣ ሴት ተማሪዎች የነገው ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው ዛሬ በጥቃቅን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሳቢያ ከትምህርታቸው ሊደናቀፉ አይገባም።

ለሴቶች ይህን መሰሉን ድጋፍ ማድረግ የነገውን ማንነታቸውን መገንባት ነው ያለችው አርቲስት አምለሰት፣የቁሳቁሶቹ እገዛ ከዚህ በፊት መደረጉን በማስታወስ ወደፊትም በሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፉን ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች። የዛሬው ጥቂት ድጋፍ ሴቶች ነገ ለእህቶቻቸውና ለልጆቸው በዕውቀታቸው መልሰው የሚከፍሉት በመሆኑ የኃላፊነታቸው ድርሻ የጎላ ነው ብላለች።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አርጋው በበኩላቸው፣ሴት ተማሪዎች በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሳቢያ ለበርካታ ችግሮች እንደሚጋለጡ ገልጸዋል። በተለይም የንጽህና መጠበቂያ ችግር በገጠማቸው ጊዜ በዓመት ለሀምሳ ቀናት ያህል ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ ብለዋል።

ይህ የቁሳቁስ ድጋፍ በብዙኃን ዘንድ ጥቃቅን የሚመስል ቢሆንም ለሴቶች የትምህርት ስኬት ግን ታላቅ ድርሻ አለው ያሉት ኃላፊዋ፣አርቲስት አምለሰት ሙጬን ጨምሮ «የሎ ሙቭመንት» የተባሉ የሴት ተማሪዎች ንቅናቄ አባላት በድጋፉ መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል። ድጋፉ በእነሱ ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ ወደፊት ሌሎች አካላትም አጋር ሆነው ሊተባበሩ እንደሚገባም አደራቸውን አስተላልፈዋል።

በዕለቱ የንጽህና ድጋፍ ከተበረከተላቸው ሴት የዩኒርሲቲ ተማሪዎች መሀል የሦስተኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ተማሪዋ ቦንቱ መርጋ እንዳለችው፣ይህ አይነቱ ድጋፍ ለሴት ተማሪዎች የሚያበረክተው ስነልቦናዊ እገዛ በእጅጉ የላቀ ነው።

በተመሳሳይም በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተማሪ እየሩስ አዱኛ እንደገለጸችው፣ከዚህ ቀደም ለአንድ ዓመት የሚሆን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንደተበረከተላት አስታውሳ፣ድጋፉ ትምህርቷን ያለምንም ችግር ለመቀጠል ስለረዳት ምስጋናዋን አቅርባለች።

አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE