የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ከልዩነት በላይ ለህዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ የፊዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ፡፡

በአዲስ አበባ ለሚከበረው የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ዝግጅቱ ተጠናቋል፡- የፌደሬሽን ም/ቤት

የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ከልዩነት በላይ ለህዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ የፊዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ፡፡
የፊታችን ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዝግጅት መጠናቀቁንም ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን በዓል ከልዩነት በላይ ለህዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ በምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረስላሴ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ በዘለለ የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚፈጠር ገልፀዋል፡፡
በዚህም አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል እንዲያንፀባርቅ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጎለብት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል ዳይሬክተሩ፡፡
ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ በዓሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
አቶ ገብሩ አክለውም ዘንድሮ በአዲስ አበባ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው የበዓሉ ተሳታፊዎች እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በበዓሉ ዕለትም በክልሎች ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲምፖዚየሞች፣ የተለያዮ ውይይቶችና ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በበዓሉ በሚካሄዱ ውይይቶች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በግጭቶች መንስኤ ዙሪያ ምክክር ተደርጎ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀመጡም እንደሚደረግ አቶ ገብሩ አመላክተዋል፡፡
ኢፌዲሪ ህገመንግስት የፀደቀበት ቀን የሆነው ህዳር 29 ‹‹በብዝሃነት የደቀመ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ይከበራል፡፡
በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ወቅትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የሰላም ጉባኤዎች በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ምክር ቤት አስታውቋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE