አቶ ጃዋር መሐመድ ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ፕሬስ ጋር ያደረገው ሙሉ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል

አቶ ጃዋር ከዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ
«ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና አካል፤ አዲስ አበባም የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት» «ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና አካል፤ አዲስ አበባም የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት»

ዘመን፡- በራያ ማንነት ላይ የተለያዩ ወገኖች እየተወዛገቡ ነው፤ የእርስዎ ምልከታ ምንድን ነው?

አቶ ጃዋር፡- ራያ የኦሮሞ ጎሳ ነው፡፡ የሚኖረው ግን በአማራና በትግራይ ድንበር ላይ ነው፡፡

በአገራችን በቅርብ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ለውጥ ሳቢያ በስደት የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ይታወቁባቸው የነበሩትን ሌሎች ፖለቲካዊ አማራጮች በመተው በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡

በሕዝቡ ውስጥ የነበረው ፖለቲካዊ መነቃቃትም ከፍ ብሎ ሰልፎችና ሌሎች ሕዝባዊ ትዕይንቶች ተበራክተዋል፡፡ ይሁንና ለውጡ ያስከተለው አዎንታዊ እድገቶች የመኖራቸውን ያህል ግጭቶችና አላስፈላጊ አተካራዎችም ተፈጥረዋል፡፡ በበጎ ከማይተያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጀምሮ፣ እየተካሰሱ ለጸብ እስከተፋጠጡት ድረስ ነገሮች ወዴት ሊያመሩ ይሆን? እየሰኘ ብዙዎችን አሳስቧል፡፡
ይህንን ተከትሎ፡-

♦ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ፌደራላዊ አወቃቀሩ መከለስ ይፈልግ ይሆን?

♦ ግጭቶች ለምንና እንዴት ተበራከቱ?

♦ የማንነት ጥያቄዎችና የድንበር ውዝግቦች እንዴት ይፈቱ?

♦ የዋና ከተማ ጉዳይ በአገራችን ዳራ ምን ዓይነት መልስ ያስፈልገዋል?

♦ እንዲሁም ፓርላሜንታዊው ሥርዓት ከፕሬዝዳንታዊው አንጻር ሲታይ ምን የተለየ ነገር ይኖረዋል? የሚሉና ሌሎች ትልልቅ ጥያቄዎችን እያነሣሣ ይገኛል፡፡

ዝግጅት ክፍላችንም እነዚህን ጥያቄዎች በመያዝ ለቀጣዩ የአገራችን ፖለቲካዊ ጉዞ “ምን ይሆን የሚበጀው?” በሚል ታላላቅ የፖለቲካ ተዋንያንን አነጋግሯል፡፡ በዚህ ዕትም የኦሮሚያ ሚድያ ኔት ወርክ ሥራ አስኪያጅና የፖለቲካ አክቲቪስት አቶ ጃዋር መሀመድና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር የዶክተር ብርሀኑ ነጋን ሐሳቦች እናስነብባለን፡፡ ከአቶ ጃዋር መሀመድ እንጀምር፦

ዘመን፡- ከአሀዳዊና ፌደራላዊ መንግሥታዊ አወቃቀር ለኢትዮጵያ የትኛው ይሻላል ይላሉ?
አቶ ጃዋር፡- በአውሮፓ ውስጥ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ዋና አመለካከት ‹አንድ አገር ውስጥ ብዙ የተለያዩ ባህሎችና ማንነቶች ካሉ እንደምንም በመጨፍለቅ አንድ “ዶሚናንት” (አውራ) ባህልና አገራዊ ማንነት መፍጠር ያስፈልጋል› የሚል ነበር፡፡ በዚህ ሒደት ነው ፈረንሳይን የመሳሰሉ አገሮች ብዙ ብሔሮች ቢኖሯቸውም ጨፍልቀው አንድ አገራዊ ማንነት መፍጠር የቻሉት፡፡ ይህ አመለካከት ከአሥራ ዘጠኝ ሀያዎቹ እስከ አርባዎቹ ድረስ ባሉት ዘመናት በተነሡ ተቃራኒ አመለካከቶች ተግዳሮት ገጠመው፡፡

‹አንጨፈለቅም› የሚል እንቅስቃሴም ተጀመረ፡፡ “ሰልፍ ዲተርሚኔሽን” የምንለው ራስን በራስ የማስተዳደር እንቅስቃሴ መጣ፡፡ ይህኛው ደግሞ በተጻራሪው ‹አንድ አገር ውስጥ የተለያዩ ማንነቶች ካሉ በአንድ አገር ውስጥ አብረው ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ብሔር እየተገነጠለ የራሱ አገር ሊኖረው ይገባል› የሚል ነው፡፡

ይህም አመለካከት ብዙ ፍጅት ፈጠረ፡፡ አገሮች እነዲበታተኑም አደረገ፡፡ ሁለተኛም አንድ ብሔር ተገንጥሎ የራሱን አገር ከመሠረተ በኋላ እንደታሰበው ሰላም ሊገኝ ሳይችል ቀረ፡፡ እናም ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም (መልቲ-ናሽናል ፌደራሊዝም) የምንለው የተሻለ አማራጭ እየሆነ መጣ፡፡ ስለዚህ ከንድፈ ሐሳቡ ተነሥተን ስናየው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ሕብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲና ፌዴራሊዝም የሚያዋጣ ይመስለኛል፡፡
አሐዳዊ ሥርዓት ተሞክሯል፡፡ ኢትዮጵያን ሲገነቡ የነበሩት እነ አክሊሉ ሀብተ ወልድ የፈረንሳይ ተማሪዎች ስለሆኑ ማንነቶችን በመጨፍለቅ (በአሲሚሌሽን) አንድ ብሔራዊ ማንነት ለመፍጠር በተለይ ከጣልያን ወረራ በኋላ ብዙ ጥረዋል፡፡ ነገር ግን በአሥራ ዘጠኝ ሰባዎቹ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ የኤርትራ ጥያቄ፣ የኦሮሞ ጥያቄ፣ የትግራይ ጥያቄ የሚለው ወጣ፡፡ በነዚህ ንቅናቄዎች ‹የባሰውን መገነጣጠል አለብን› የሚል ከረር ያለ ጥያቄ ተነሣ፡፡ ያም ብዙ አልሠራም፡፡ በደርግ ጊዜ የራስ ገዝ አስተዳደር ተፈጠረ፤ በመለስ ጊዜ ደግሞ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተመሠረተ፡፡
ያም ሆነ ይህ አሁን ወደ አሃዳዊ ሥርዓት ፈጽሞ መመለስ አይቻልም፡፡ ብሔሮች ደግሞ ተገንጥለው የራሳቸውን አገር ቢመሠርቱ የበለጠ ግጭት ነው የሚፈጥሩት፡፡ ስለዚህ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ዘመን፡- ምን ዓይነት ፌደራሊዚም የተሻለ ነው?

አቶ ጃዋር፡- የማንነት ፌደራሊዝም ነው፡፡ የኤርትራን ጥያቄ ብትወስደው ብዙ ብሔሮችን ያቀፈ ሆኖ ነገር ግን ኤርትራዊ ማንነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የትግራይና የኦሮሞም የራሱ የተለየ መልክ ያለው የማንነት ጥያቄን የያዘ ነው፡፡ የሶማሌ ደግሞ ብዙ ጎሣዎችን የያዘ ነው፡፡ የማንነት ፌደራሊዝም እዚህ አገር ላይ የተፈጠረው በሕዝብ ጥያቄ የተነሣ ነው፡፡ ፌደራሊዝሙ ለጥያቄው የተሰጠ መልስ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄው አሁንም ቀጥሏል፡፡ በተለይ በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔሮች የራሳቸውን ዞን ለመፍጠር፣ እንደ ሲዳማ ያሉት ደግሞ የራሳቸውን ክልል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ስለዚህ የማንነት ፌደራሊዝም ግዴታ ነው፡፡ ፍጹም ባይሆንም እያሻሻልን ልንቀጥልበት ይገባል፡፡
ዘመን፡- ሕገ መንግሥቱ ያጸደቀው ሰንደቅ ዓላማ እየተቃጠለ ሕጋዊ ያልሆኑ ባንዲራዎችና የድርጅት አርማዎች እንደ ሰንደቅ ዓላማ እየተቆጠሩ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ጃዋር፡- በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ሰዎች የፈለጉትን ባንዲራ ይዘው መሔድ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮችም ባንዲራ ማቃጠል መብት ነው፡፡ ያልፈለግነውን ባንዲራ በሥርዓት፣ በሕግ አግባብ መቀየር እንጂ በጉልበት ለመተካት መሞከር ግን ትክክል አይሆንም፡፡ የተለያዩ ወገኖች የሚመርጧቸው ባንዲራዎች እንጂ አጠቃላይ ሕዝብ የተስማማበት ባንዲራ የለንም፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ልናደርግ የምንችለው በሕዝብ አደባባዮችና በመንግሥት ተቋማት ሕገ መንግስታዊው ባንዲራ፣ ሌሎቹ ባንዲራዎችና የፓርቲ አርማዎች በሰልፎች፣ በቡድኖቹ ስብሰባዎችና በግል ሊውለበለቡ ይችላሉ፡፡ ማንኛውንም ባንዲራ ማቃጠል ግን አደጋ አለው፡፡ ምክንያቱም አንዱ የሌላኛውን ሲያቃጥል፣ በምላሹም ያኛውም ያቃጥልና ወደ ከባድ ግጭት ያመራል፡፡

ስለዚህ ማንም የፈለገውን ባንዲራ በግሉ ይጠቀም፤ ነገር ግን ከሕዝብ አደባባዮችና ተቋማት ያርቃቸው፤ የሌላውን ደግሞ አያቃጥል፡፡
የሕግ ጥሰት ተፈጸመ ስንል ግን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ የፌደራል ወይም የክልል ያልሆነ ባንዲራ ይዤ ብሔድ የሕግ ጥሰት አልፈጸምኩም፡፡ ነገር ግን ወደ አንድ የመንግሥት ተቋም ሔጄ ባለ ኮከቡን ባንዲራ ባወርድና በምትኩም የኦነግን ባንዲራ ልሰቅል ብሞክር ይህ የሕግ ጥሰት ነው፡፡
ዘመን፡- በክልሎች መካከል የመሬት ይገባናል ጥያቄዎችና የድንበር ውዝግቦች እንዴት ቢመለሱ ጥሩ ይሆናል ይላሉ?

አቶ ጃዋር፡- አንዱ የፌደራል መንግሥት ተግባር በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማቀናጀት ነው፡፡ የልማት ቅንጅት ሊሆን ይችላል፤ አንዳንዴም የግጭት አፈታት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ለመሥራት የፌደራል ጉዳይ ሚንስቴር የሚባል መስሪያ ቤት ተቋቁሟል፡፡ ስለሆነም ይሀን መሰሉን ነገር በአገር ሽማግሌዎች ከማቀራረብ ጀምሮ በሕግ ማእቀፍ በሰላማዊ መንገድ ሊፈታው ይችላል፡፡ እስካሁን ያለው ችግር ፌደራላዊው ሥርዓት ለተነሣው የብሔር ጥያቄ በመዋቅር ደረጃ መልስ ሰጥቶ ፍትሐዊ ክፍፍል ሳያደርግ መቅረቱ ነው፡፡

የፌደራሉ ሥልጣን በአንድ ቡድን የተያዘ ስለነበር የፌደራል መንግስት ሥልጣን እየፈረጠመ ክልሎች ደግሞ በፌደራል መንግሥቱ በኩል ብቻ እንጂ እርስ በራስ እንዳይገናኙ የከለከለ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ክልሎች የችግር አፈታት ልምድ እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ የፌደራል መንግስትም የማቀራረብ፣ የማወያየት ሥራ አልሠራም፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ግጭቶችን በሕግ አግባብ ሊፈታ ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ የድንበር ጉዳይ ያን ያህል አጨቃጫቂ ሊሆን አይችልም፡፡

ዘመን፡- ግን እኮ በደምብ አጨቃጭቋል፤ እያጨቃቀጨቀም ነው፡፡
አቶ ጃዋር፡- በርግጥ አጨቃጭቋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በድንበር ሰበብ የሚነሡ አንዳንድ ግጭቶች ምክንያታቸው ሌላ ነው፡፡ የኦሮሚያና የሶማሌ ግጭት በጫትና በመሣሪያ ዝውውር ምክንያት የተፈጠረ እንጂ በድንበር ምክንያት የተፈጠረ አይደለም፡፡ እዚያ የነበሩ ጄኔራሎች ጫት እንደፈለጉ ይነግዱ ነበር፤ መሣሪያ እንደልባቸው እያዘዋወሩ ይሸጡ ነበር፡፡

እናም የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ግጭት የህወሓትና የኦህዴድ በውክልና ጦርነት ያካሔዱበት እንጂ የድንበር ግጭት አይደለም፡፡ በርግጥ የድምበር ግጭት ይነሣል፤ ያን ያህል ደም ማፋሰስ ግን አያስከትልም፡፡ ግጭቱ ከፍ እንዲል ያደረገው አዲስ አበባ ላይ የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ ነው፡፡
ዘመን፡- የወልቃይት ጉዳይስ?

አቶ ጃዋር፡- የወልቃይት ጥያቄ ውስብስብ ነው፡፡ ሆኖም ጥያቄውን በአፈ ሙዝ ለመዝጋት መሞከር ትክክል አይደለም፡፡ ማንኛውንም ጥያቄ በጉልበት መፍታት ትክክል አይደለም፡፡ ታሪክን ተገን አድርገን፣ ሕገ መንግሥትን ተገን አድርገን፣ የሕዝብን ፍላጎት ተገን አድርገን መፍታት እንችላለን፡፡ የወልቃይት ጥያቄም የወልቃት ችግር ብቻ አይመስለኝም፡፡

ህወሓት ጎንደር ውስጥ የቅማንትን ጥያቄ ሲቆሰቁስ ብአዴንም የወልቃይትን ጥያቄ እንደቆሰቆሰ ነው የሚታየኝ፡፡ እዚህም ላይ የማዕከላዊው መንግሥት የፖለቲካ ሽኩቻ ነው በሌላ መልኩ ራሱን ሲገልጥ የምናገኘው፡፡ የፌደራል መንግሥት ድርሻ መሆን ያለበት የልኂቃኑ የሥልጣን ሽኩቻ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ድንበር ላይ ሰው እንዳያፋጅ መጠንቀቅ ነው፡፡

ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመ የፌዴዴሽን ምክር ቤት አለ፤ በሱ በመጠቀም የወልቃይትንም ሆነ የሶማሌ ኦሮሚያ የድንበር ችግሮችን እየፈቱ መሔድ ይቻላል፡፡
ዘመን፡- በሌላ ክልል የሚኖሩ ብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው እንዴት ይከበር?
አቶ ጃዋር፡- በአንዳንድ ቦታዎች ኩታ ገጠም በሆነ ሁኔታና አንድ ወረዳ ሊሆን በሚችል መጠን ሕዝቡ ሊገኝ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር መፍቀድ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል ግን ከአንድ ብሔረሰብ የተገኘ ማኅበረሰብ በቁጥር ብዙ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ተበታትኖና ተሰበጣጥሮ የሚኖርበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አማራ ክልል ውስጥ ኩታ ገጠም በሆነ መልኩ ይገኛል፡፡ እንዲህ ሲሆን ችግሮችን በቀላሉ መፍታት ይቻላል፡፡ ችግር የሚመጣው ለምሳሌ አማራው በኦሮሚያ እንዳለው ዓይነት፣ ወይም በቤኒሻንጉል ውስጥ ሃይላንደርስ (ደገኞች) የምንላቸው በሚኖሩበት ዓይነት ተበታትነው ሲኖሩ ወረዳ ልትሰጣቸው አትችልም፤ ቀበሌ ልትሰጣቸው አትችልም፡፡

ምክንያቱም ተበትነው የሚገኙ ስለሆኑ እንደዚያ ማድረግ አይቻልም፡፡
‹የነዚህን ሕዝቦች መብት እንዴት ነው ሊከበር የሚችለው?› የሚለው በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የሚያከራክር ነው፡፡ የእኔ ምክረ ሐሳብ ተበታትኖ የሚኖረው ማሕበረሰብ የሆነ ፎርሙላ አውጥቶ በክልሉ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ውክልና ቢያገኝና እንደ ትምህርት ቤት ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ቢሟሉለት መልስ የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡ ይህን ጥያቄ ኦሮሚያ መልስ ከሰጠች ሀያ ዓመት ሆኗታል፤ በአማርኛ የሚያስተምሩ በሺ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ኦሮሚያ ውስጥ ተሠርተዋል፡፡

የራያን ጥያቄ ከተመለከትከው ግን ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ሕዝቡም ኩታ ገጠም በሆነ መልኩ ተሰባስቦ የሚኖርና የራሱ ማንነት ያለው ስለሆነ የራሱ አስተዳደር እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ የሚያስቸግረው ግን ተሰባጥሮ የሚኖረው ማኅበረሰብ ይመስለኛል፡፡

ዘመን፡- አርሲ ውስጥ በቁጥር በርካታ የሆነ የአማራ ሕዝብ ይኖራል፤ ይህ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ መልስ የሚፈልግ ይመስሎታል?
አቶ ጃዋር፡- አርሲ ውስጥ አማራ የሌለበት ወረዳ ያለ አይመስለኝም፤ ግን ተበታትኖና ተሰባጥሮ እንጂ አንድም ቦታ ‹‹ዶሚናንት›› ሆኖ የሚኖርበት የለም፡፡ ቁጥሩ በርከት ብሎ የሚገኝ ቢሆንም የተበታተነ ነው፡፡

እስካሁን ባለኝ መረጃ ሳይበታተን ኩታ ገጠም ሆኖ የሚኖር ራያ ብቻ ይመስለኛል፡፡

ዘመን፡- በራያ ማንነት ላይ የተለያዩ ወገኖች እየተወዛገቡ ነው፤ የእርስዎ ምልከታ ምንድን ነው?

አቶ ጃዋር፡- ራያ የኦሮሞ ጎሳ ነው፡፡ የሚኖረው ግን በአማራና በትግራይ ድንበር ላይ ነው፡፡ ከኦሮሚያ ጋር ኩታ ገጠም አይደለም፡፡ የአማራ ክልል የጂኦግራፊ ጥያቄ ሊያነሣ ይችላል፤ ኦሮሚያ ደግሞ የብሔር ጥየቄ ሊያነሣ ይችላል፡፡ እኔ ከዚያ ይልቅ የሚሻል የሚመስለኝ ለሕዝቡ ወረዳ መስጠት ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ሁለት ነው፡፡ በራስ ቋንቋ የመማር ጥያቄና የልማት ፍትሐዊነት ጥያቄ ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ የተወሳሰበ አይደለም፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ በቋንቋ መማር፣ ልማት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አይደለም፡፡

ለምሳሌ ከሚሴን ብትወስድ በቋንቋው መጠቀምና ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከተፈቀደለት በቂው ነው፡፡ ‹ወደ ኦሮሚያ እንግባ› አላሉም፡፡ የማይሆነው ትግራይ ክልል የራያን ቋንቋና ባህል በማጥፋት ቲግራናይዜሽን (የማተግረይ) ፕሮጀክት ሲሞከር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር አደጋ አለው፡፡
ዘመን፡- የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ እንዴት እልባት ሊያገኝ ይችላል?
አቶ ጃዋር፡- አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች፡፡ ምድሯ የኦሮሞ ነው፡፡ በውስጧ ደግሞ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ይኖራሉ፡፡ መፍትሔ መሆን ያለበት
የኦሮሚያ ክልል የባለቤትነት መብት እንዲሁም ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መብት ባመዛዘነ ሲሆን ነው፡፡ ከባለቤትነት ጥያቄ ይልቅ ትኩረት

ሊደረግበት ይገባ ነበር የምለው የዘላቂነት ጥያቄ ነው፡፡ ትልቅ ከተማ እንደመሆኗ መጠን ለመስፋፋትም ሆነ ለሌሎች የከተማዋ ጥቅሞች የሚበጀው የከተማዋ ህልውና ከአካባቢው ጋር የተሣሠረና በአካባቢው ላይ ጥገኛ የሆነ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡

እንደ መብት ካየነው የኦሮሚያ ክልልና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መብት ስለሆነ የሁለቱ ወኪሎች በሚያደረጉት ድርድር ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ላይ ያስቀመጠው መሠረት ተደርጎ ሆኖም ጠለቅ ባለ መልኩ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የኦሮሞ ጥያቄ እየሆነ የመጣው ከተማዋ በሰፋች ቁጥር ነዋሪውን እየጠረገችው መሆኑ ነው፡፡

ገበሬውን ወደ ኢንዱስትሪ እየከተተው አይደለም፡፡ ከተማው በሚውጠው የገበሬ መሬት ምትክ ገበሬውን በኢንዱስትሪ አላቀፈውም፡፡ እዚያ የነበረው ገበሬ ማንነቱንና ከአያቶቹ የወረሰውን መሬቱን እያጣ ብቻ ሳይሆን ዘር ማንዘሩ እየጠፋ የሔደበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ዘመን፡- ገበሬው ተጠረገ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ጃዋር፡- በየዓመቱ ከተማዋ ስታድግ የገበሬው መሬት ወደ ከተማው እየገባ ገበሬው ደግሞ እየጠፋ ነው ማለቴ ነው፡፡
ዘመን፡- ነገሩ የካሳ ጥያቄ ይሆን?

አቶ ጃዋር፡- አይደለም፡፡ የካሳ ጥያቄ አይደለም፡፡ ከተማ ሲያድግ ነባሩ ሕዝብ አብሮ ማደግ አለበት፡፡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መግባት አለበት፡፡ ከገጠር ነዋሪነት ወደ ከተሜነት መለወጥ አለበት፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ግን እንደዛ አይደለም፡፡ መሬቱን ስትነጥቀው ብትን ይላል፡፡ ካሳ ብትሰጠውም፤ ፕላን አውጥተህ ክፍያው ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገሪያ እንዲሆነው ካልፈቀድክለት ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላ ብሩን ይጨርስና ልጆቹና ያ ሰውዬ ተበትነው ያልቃሉ፡፡ ስለዚህ የከተማው ልማት ገበሬውን የሚያሳድግ እየሆነ እንዲሔድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ዘመን፡- የአዲስ አበባ እድገት የኦሮሞን ገበሬ ጥቅም ሳይነካ ሊከናወን እንደሚችል ሊረጋገጥና በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው? የአዲስ አበባ አስተዳደር በኦሮሞ ባለሥልጣናትና ድርጅቶች እንዲተዳደሩ በማድረግ ነው ወይስ ሌላ አማራጭ አለ?
አቶ ጃዋር፡- አስተዳደሩ የግድ ኦሮሞ መሆን የለበትም፡፡ አንደኛ የአስተዳደር ክፍፍል ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ አስተዳደሮች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መኖር አለበት፡፡

ሁለተኛም የገቢ ክፍፍል መኖር አለበት፡፡ ያንን መደራደር ይቻላል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ በሚመርጣቸው ወኪሎቹና ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚመድባቸው ወኪሎች አማካይነት ፖለቲካዊ የአስተዳደር ክፍፍልና ኢኮኖሚያዊ የገቢ ክፍፍል ሲካሔድ ነው መተማመኛ የሚፈጠረው፡፡
ዘመን፡- የአዲስ አበባ ጥቅሞች፣ መብቶች፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትስ ተከብሯል ብለው ያምናሉ?
አቶ ጃዋር፡- የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የሌላውም ክልል፣ የሁሉም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አልተከበረም፡፡

ዘመን፡- የአዲስ አበባን ልዩ የሚያደረገው ግን እንደ ሌሎች ክልሎች ራሱን እንዲያስተዳድር አልተፈቀደለትም፡፡ ለምሳሌ ‹ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች፤ ትግራይም የትግራዋዮች፣ አዲስ አበባን ግን ከየትኛውም ቦታ የተጠራ ሰው ሊያስተዳድራት ይችላል› የሚሉ ሐሳቦች የሚያነሡ አሉ፡፡
አቶ ጃዋር፡- ኦሮሚያም ቢሆን በሕዝብ የተመረጠ የራሱ አስተዳደር ኖሮት አያውቅም፡፡

አሁን ያሉት መሪዎች ራሳቸውን ከሕዝብ ትግል ጋር ስላያያዙ ሕዝባዊ ድጋፍ አገኙ እንጂ ሕዝብ መርጦ እንዲስተዳድሩት አላደረጋቸውም፡፡ ሕዝባዊ ተቀባይነት (ፖፑላር ሌጂቲሜሲ) እንጂ ‹‹ኢሌክቶራል ሌጂቲሜሲ›› (በምርጫ የተገኘ ቅቡልነት) አላገኙም፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ተለይቶ ተበደለ ሊያስብል የሚችል ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አንጻራዊ ነጻነት ግን አዲስ አበባ ያለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሰው በጎንደር ሲጨፈጨፍ፣ አምቦ ውስጥ ሲጨፈጨፍ አዲስ አበባ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ነበር፡፡
ዘመን፡- በ1997 ደግሞ ተቃራኒው ነበር፡፡
አቶ ጃዋር፡- እሱም ቢሆን በጣም አጭር ጊዜ ነበር፤ ኢሕአዴግ ላይም ብዙ ጫና አምጥቷል፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ስለሆነች ትንሽ ቁጥር ያለው ሰው ቢሞት ተጋኖ ይሰማል፡፡ ሌላ ቦታ ግን የሚሞተው ሰው ቁጥር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አንጻራዊ ነጻነት ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡

ዘመን፡- በመርሕ ደረጃ ብንመለከተው ሕገ መንግሥቱ ለሌሎች የሰጠውን የክልልነት ደረጃ ለአዲስ አበባ አልሰጠም፡፡ ይህ አድልዎ አይደለም?
አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች፡፡ የክልልነት ዕውቅና የላትም፤ ሊኖራት አይችልም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ክልል አይደለችም፤ ወደ ፊትም ልትሆን አትችልም፡፡ በሌላ በኩል ሕብረ ብሐራዊ በሆነ መልኩ ዜጎች ስለሚኖሩባት የነዋሪዎቿ መብት ሊከበር ይገባዋል፡፡
ዘመን፡- የእስካሁኑን እቀበላለሁ፤ “ወደ ፊትም ልትሆን አትችልም” ያሉኝን ግን በምክንያት ሊያስደግፉት ይችላሉ?
አቶ ጃዋር፡- በአንድ ክልል ውስጥ ሁለት ክልል ሊኖር አይችልም፡፡ ፊንፊኔ ዋና የኦሮሚያ አካል ነች፡፡ ስለዚህ በአንድ ክልል ውስጥ ሌላ ክልል ልትፈጥር አትችልም፡፡

ዘመን፡- በአገሪቱ ውስጥ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት፣ ሀብት የማፍራትና የመኖር መብቶች ሲጣሱ ተስተውሏል፡፡ ይህ ችግር ከምን የመነጨ ይመስሎዎታል? መፍትሄውስ ምንድነው ይላሉ
አቶ ጃዋር፡- እዚህ አገር የነበረው መሠረታዊ ችግር ለተነሡ ጥያቄዎች በፌደራሊዝም መዋቅራዊ መልስ ተሰጥቶ የክፍፍል መብት (‹ሪዲስትሪቢውሽን›) ግን መነፈጉ እንደሆነ ደጋግመን አንሥተናል፡፡

ይህም ማለት መዋቅራዊ መፍትሔ ከተሰጠ በኋላ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ አልሆነም ማለት ነው፡፡ የፌደራል ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ ደግሞ የጠቀስካቸው ችግሮች በሙሉ ይፈጠራሉ፡፡ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ቢሆን ኖሮ የድንበር ጥያቄ ሀያ ዓመት ቆይቶ እንደ አዲስ አይገነፍልም ነበር፡፡ ገና ከመጀመሪያው ክልሎች ሰጥቶ በመቀበል መርሕ ተደራድረው ሊፈቱት ይችሉ ነበር፡፡

የክልሎችን መኖር በመዋቅር ደረጃ የፈቀደው የፌደራል ሥርዓት ሥልጣንን ግን ጠቅልሎ ለፌደራል መንግስት ብቻ በመስጠቱ ክልሎች የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ዕድል አልሰጣቸውም፡፡ አገሪቱ ውስጥ የተቋቋሙ ሁሉም ኩባንያዎች ማለት ይቻላል ‹‹ፒ ኤል ሲ›› እየተባሉ ግብር የሚያስገቡት ለፌደራል መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ክልሎች ምንም ነገር በእጃቸው የለም፡፡ የክፍፍል ጉዳይ የሚመጣው እዚያ ላይ ነው፡፡

የክልሎች መዋቅራዊ መብት ተከብሮ የሚያስተዳድሩት ሕዝብ መብት ግን አልተከበረም፡፡ ዜጎች ወደሌሎች ቦታዎች ተዘዋውረው ሲኖሩ መብታቸውን ክልሎቹ ሊያስከብሩላቸው ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ክልሎች እርስ በራስ እየተገናኙ የመደራደርና የመነጋገር ዕድል ቢኖራቸው ኖሮ ችግሩ ይቀረፍ ነበር፡፡ ዜጎችም በሚሔዱበት ክልሎች ውስጥ ያለውን የክልሎቹን ሕግጋት ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡ የብዙዎቹን ክልሎች ሕገ መንግሥቶች አይቼዋለሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሠላሳ አንቀጾች ስለዜጎች መብት ነው የሚያወሩት፡፡ ስለዚህ እሱ ችግር ያለበት አይመስለኝም፡፡ ሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ካደረግነው የዜጎች እንደ ልብ መዘዋወር መብት ሊጠበቅ ይችላል፡፡

ዘመን፡- ‹ይህ ችግር የተፈጠረው በሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት የተነሣ ነው› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህ ሃሳብ ምን ዓይነት አጸፋ ያቀርባሉ?

አቶ ጃዋር፡- በፍጹም አይደለም፡፡ በደርግ ጊዜስ መቼ እንደልብ የመዘዋወር መብት ነበር? የዛኔም ችግሮች ነበሩ፡፡
ዘመን፡- ‹ከኢህአዴግ በፊት አንድም የብሄር ግጭት ተነስቶ አያውቅም፤ ግጭት የመጣው አሁን በፌደራሊዝም ዘመን ነው› የሚሉ እኮ አሉ፡፡

አቶ ጃዋር፡- እንዴ! የት ነበሩ? አሁን ነው እንዴ የተወለዱት? የብሔር ግጭት እኮ እዚህ አገር ነባር ነገር ነው፡፡ አገሪቱ ራሷ የተመሠረተችው በብሔር
ግጭት ነው፡፡ ምኒሊክ ደቡብን ጨፍልቆ የገነባት አገር እኮ ነች፡፡ ምን መሰለህ እዚህ አገር ያለው ችግር? ሰዎች ወቅታዊውን ፖለቲካ ለማሰማመር ሲሉ ኦሮሞና አማራ በፍቅር ተጣብሰው የመሠረቱት አገር እያስመሰሉ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ከአሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ደም አፋሳሽ የሆኑ ግጭቶችና ጦርነቶች ተካሂደው ነው ይህችን አገር የፈጠሯት፡፡

የሙስሊም ክርስቲያን ጦርነት፣ የኦሮሞ ጦርነት፣ የምኒሊክ ጦርነት ተካሒዶ ወደ መጨረሻው ደግሞ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ኃይሎች ሕዝብን አንቀሳቅሰው ባደረጉት ግጭት እኮ ነው ይህች አገር የተመሠረተችው፡፡
አይደለም በደርግ ጊዜ ከዚያ በፊትም ቢሆን አንዱ ብሔር ሕዝብ አንቀሳቅሶ ሌላውን በመውጋት ካሸነፈ በኋላ የራሱን ባህል እየጫነበት ነው የመጣው፡፡ እኔ ጎንደር ሔጄ ነው እንዴ አማርኛ የተማርኩት? እና አልነበረም እንዴት ይባላል? በደንብ ነበረ፡፡ መነሣት ያለብን በመካድ አይደለም፡፡ ዛሬ ተባብሷል ማለት ይቻል ይሆናል ግን ግጭት ትናንትም ነበር፤ ግጭት የሌለበት አገር የለም፡፡ ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች አሉ፡፡ አንዱ ትናንት ጦርነት በጦርነት ብቻ ነበር፤ ስለዚህ የዛሬውንም በጦርነት እንፍታው የሚል ነው፡፡ ሌላው ትናንት ፍቅር በፍቅር ነበርን፤ መለስ ዜናዊ መጥቶ ችግር አመጣ የሚል አለ፤ ልክ እዚህ አገር መለስ ዜናዊ ብሔርን የፈጠረ የሚያስመስሉ አሉ፡፡ እነ መለስ ዜናዊ፣ እነ ኢሳያስ አፈ ወርቂ፣ እነ ሌንጮ ለታ ጫካ የገቡት እኮ ብሔራችን ተጨቆነ ብለው ነው፡፡ ደግሞም የዘር ጭቆና ባይኖር ኖሮ ካንድም ሰው ድጋፍ አያገኙም ነበር፡፡ እውነተኛ የሆነ ችግር እዚህ አገር ውስጥ አለ፤ በመካድ ልታስቆመው አትችልም፡፡

ፌደራላዊ ሥርዓት ሰጥተህ ከዴሞክራሲ ጋር ጎን ለጎን እንዲኖር አለማድረግ ተቀጣጣይ ነዳጅ እንደማስቀመጥ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ እየገነነ እየገነነ ይመጣና የሚተነፍስበት ሥርዓትና የጎንዮሽ ግንኙነት ስለሌለ ይፈነዳል፡፡ ሁሉም የራሱን ብቻ እየገነባ ከሌላው ጋር ሰጥቶ በመቀበል አይደራደርም፤ የጋራ ማንነት እየሠራ አይሔድም፡፡ አማራና ኦሮሞ ረጅም ድንበር እየተጋሩ፣ ውስብስብ ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እያላቸው የእርስ በርስ ፖለቲካዊ ግንኙነትና ውይይት ግን አልበራቸውም፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር ቀስ በቀስ ችግር እየፈጠረ ይመጣና ግጭት ያስነሳል፡፡ በእኔ እመነት ለዚህ ቸግር ሁነና መፍትሄ የሚመስለኝ ፌደራላዊ ሥርዓቱን እንዳለ ይዘነው ዴሞክራታይዝ ማድረግ ነው፡፡

ዘመን፡- በአመጽና በእምቢተኝነት ሥልጣን ለመያዝ የመፈለግ አዝማሚያዎች እንዴት ሊቀረፉ ይችላሉ?
አቶ ጃዋር፡- ሥልጣን ላይ ያለው አካል ለውይይት ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ሥልጣንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ካልያዘ ወይም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ሊለቅ ካልቻለ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ዘግቶት የራሱ ፖለቲካ መከንቸሪያ ብቻ ካደረገው ማመጽ መብትም ነው፤ ግዴታም ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ሊሆን ይችላል፣ በጦርነት ሊሆን ይችላል ግን ማመጽ መብት ነው፡፡

አንድ መንግሥት ግን ለድርድር ዝግጁ ከሆነ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ካሰፋ፣ የሚድያ መብትን ካከበረ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ሕዝብን ማደራጀትና መቀስቀስ እስከቻሉ ድረስ ወደ አመጽ መግባት ግን ተገቢነት የለውም፡፡ ይሄ በርግጥም የኪሳራ ስትራቴጂ ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምህዳሩ ሰፍቷል፡፡ ነጻ ሆነን በሚድያ እየተወያየን፣ እየተከራከርን ነው፡፡

የሐሳብ ፍጭት ማድረግም ይቻላል፡፡ የሃሳብ ገበያውም ክፍት ነው፡፡ መንግሥት ቀጣዩን ምርጫ ነጻና ፍትሓዊ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ተጨባጭ ርምጃዎችንም እየወሰደ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ግን የፖለቲካ ሥልጣን በአቋራጭ ለመያዝ ወደ ብጥብጥ መግባት ሞኝነት ነው፡፡ የተገኙት ዕድሎችንም መልሶ ማስነጠቅ ነው የሚመስለኝ፡፡

ይህን ዓይነት መንገድ የሚመርጡ ወገኖች እኔ እንደሚታየኝ አንደኛ ሥልጣን በመጋራት የዚህ መንግሥት አካል መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ሥልጣን መጋራት አይጠቅማቸውም፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ሥልጣን መጋራት የኢሕአዴግን ሸክም መጋራት ስለሆነ ከጥቅም አንጻር ብትወስደው ራሱ ዕውቀት የጎደለው (ናይቭ) አካሔድ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ይህ መንግሥት ራሱን አሻሽሎ ሽግግር እንዲያካሒድ አደራ ተሰጥቶታል፤ ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከካቢኔው ጋር ሆኖ እንደፈጽም መርዳት ያስፈልጋል እንጂ ባቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር ጠቃሚ አይመስለኝም፤ አይቻልምም፡፡

ሰዎች ሥልጣን ለመጋራት የሚፈልጉት መስተካከል አለባቸው ብለው የሚያስቡትን ሕጎችና ፖሊሲዎች ለመለወጥና ለማሻሻል ነው፡፡ ነገር ግን በዚህች አገር የፖሊሲና የሕጎች ክፍተት የተፈጠረው በሕዝብ ያልተመረጡ ሰዎች እንደልባቸው የሚጠፈጥፉት ስለሆነ ነው፡፡ እዚህ አገር ምናልባት አባ ገዳዎቹና ቄሶች፣ ሼሆች ካልሆኑ በቀር አንድም በሕዝብ የተመረጠ ሰው የለም፡፡ የሚወደዱ፣ የሚከበሩና ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ግን አሉ፡፡ መወደድና መከበር ግን መመረጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥትንም ሆነ ሌላ ፖሊሲ ለመቀየር መጀመሪያ የሕዝባችንን ውክልና መያዝ አለብን፡፡

ዘመን፡- ይህን ዓይነት ትንታኔ የሚሰጡት ግን የተሳካላቸው አይመስሎትም? ለምሳሌ እርስዎ አሜሪካ በነበሩበት ጊዜ አገር ውስጥ በሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች እርስዎን በሕገ ወጥነት ፈርጀው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እርስዎ በተራዎት ሌሎችን የሚፈርጁ ይመስላል፡፡

አቶ ጃዋር፡- የእኔ ዓላማ ዴሞክራሲያዊና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የእኔ ዓላማ – በከፊልም ቢሆን – አዎ ተሳክቷል፡፡ በነጻነት መነጋገር መቻል አለብን፤ እያደረግነው ነው፡፡ አሁን እኔ ከአንተ ጋር የማደርገውን ውይይት የተነፈገ አካል ካለ ይነገረኝ፤ እታገልለታለሁ፡፡ በመንግሥት ሚድያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚውም እየተጠቀመበት ነው፡፡ የታገልነው ለዚህ ነው፡፡ ለዘላለም እገዛለሁ ከሚል አመራር ነጻ፣ ገለልተኛ ተፎካካሪ ምርጫ አካሒዳለሁ ወደሚል አመራር ተሸጋግረናል፡፡

የጠቅላይ ሚንስትሩን ጠቅላላ ፖሊሲ እደግፋለሁ ማለት አይደለም፡፡ ግን ወደ ዲሞክራሲ አሸጋግራለሁ ብሎ እስከመጣ ድረስ ከእሱ የተሻለ አማራጭ ፖሊሲ ካለኝ በሚቀጥለው ምርጫ ተወዳድሬ ማሸነፍና ወደ ሥራ መለወጥ ነው፡፡ ስለዚህ አሸንፈን ስለመጣን ብቻ ሳይሆን እዚህ አገር ላይ የተመረጠ ኃይል ብቻ ነው አገር ማስተዳደር ያለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

የተመረጠ ኃይል ብቻ ነው ፖሊሲ መለወጥ የሚችለው፤ ያንንም ፖሊሲ ወደ ተግባር ሊለውጥ የሚችለው ያው የተመረጠው ኃይል ነው ከሚል አንጻር እንጂ እከሌ አሸነፈ እከሌ ተሸነፈ በሚል አይደለም፡፡
እርግጥ ነው! እኛ ነን የታገልነው፡፡ ግን ተጠቃሚው እኛ ብቻ ነን እንዴ? አገር ውስጥ ገብተን በነጻነት በመንቀሳቀስ ላይ ያለነው እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ የፕሬስ ነጻነትን እየተጠቀምን ያለነው እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ ችግር የሚመጣው እኛ ነን የታገልነው ስለዚህ እናንተ አትናገሩ፤ እኛ ፓርቲ እናደራጃለን፤ እናንተ ግን አትችሉም ብንል ነበር፡፡

ዘመን፡- በሐሳብና በርዕዮት ሳይሆን ባህላዊ የማንነት መገለጫዎችን እየኮረኮሩ ሕዝብ በመቀስቀስ የሚከናወን ፖለቲካ ምን ዓይነት ሚና አለው?
አቶ ጃዋር፡- ያ ችግር የለውም፡፡ ከእውቀት አንጻር ከተመለከትከው ትክክል አይደለም፡፡ ሊበራል በሆነ አመለካከት ከተመለከትከው ላያስኬድ ይችላል፡፡ ግን ዴሞክራሲ ውስጥ ምክንያታዊ (ራሽናል) የሆነ ቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን ኢምክንያታዊ የሆነውም ሊሠራ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ‹ይህኛው ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ያዋጣል› ብሎ በፖሊሲ ብቻ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡

ሌላው ደግሞ የማንነት ፖለቲካን ሊመርጥ ይችላል፡፡ ዴሞክራሲ ሁሉንም ያስተናግዳል፡፡ ባህላዊ በሆኑ የማንነት መገለጫዎች ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሁንና ከዴሞክራሲ መስፈርቶች የወጣ ግን አይደለም፡፡
ዘመን፡- የሕዝብ ውክልና ሳይኖራቸው እንደ ባለሥልጣን እየተናገሩ ሕዝብ ላይ በሚፈጥሩት ተጽእኖ ምክንያት አገርና መንግሥት እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ ሰዎች (አንዱም እርስዎ ኖት) ሚና ምን መሆን አለበት?

አቶ ጃዋር፡- ሕዝብ ይሰማናል፤ እኛም ለሕዝብ ታግለናል፡፡ ነገር ግን ሕግ የመቀየር መብት የለንም፡፡ የታገልንለት ሕዝብ አቅጣጫ እንድናሳየው ይጠብቃል፡፡ ፍላጎቱን እንድንገልጽለት ይፈልጋል፡፡ የታገልንለት ዓለማ ባልሆነ መንገድ ሲወሰድ ዝም ብለን አናይም፡፡ ስለዚህ ተሰሚነት ካላቸው ሰዎች የሚጠበቀው የሐሳብ ክርክር ማድረግ፣ የሚደግፋቸው ሕዝብ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ ሲሆን፤ በሌላም በኩል መንግሥት ላይ ጫና ማድረግና ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በፍጥነት እንዲሔድ ማድረግ ነው፡፡

የሕዝብን ውክልና ሳናገኝ ግን ሕግን መለወጥና ሥርዓትን መቀየር አንችልም፡፡ መለወጥ ከፈለግን ወደ ምርጫ ውድድር መግባት ይኖርብናል፡፡ ያ ካልሆነ ግን የምንችለው ሐሳባችን መግለጽ፣ በሐሳብ መፋጨት፣ የሕዝብን አመለካከት መቀየር ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ አመለካከት መቀየር ወንጀል አይደለም፡፡ የፌደራል ሥርዓቱ አይጠቅምም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የማይቻለው ወደ ጉልበት መግባት ነው፡፡
ዘመን፡- ታዋቂ ፖለቲከኞችንና ድርጅቶችን በሚደግፉ ሰዎች መካከል ግጭት እየተነሣ ብዙ ጥፋት ሲደርስ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ አንጻር ተጽእኖ ፈጣሪ መሪዎች ምን ሊያደረጉ ይገባቸዋል ይላሉ?

አቶ ጃዋር፡- የመሪዎቹ ሚና በማነሣሣት ደረጃ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያም አልፈው በተደራጀ መንገድ ታስቦበበት የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ራስን በራስ እንደመምታት ነው፡፡ በሽግግር ጊዜ ተቃዋሚው ስልጡን (smart) መሆን አለበት፡፡ የሥልጣን ትርፍራፊ አይደለም መጠበቅ ያለበት፡፡ ይልቁኑም ሽግግሩን ወደ ዴሞክራሲ መግፋትና ሊቀለበስ ወደማይችልበት ደረጃ ማድረስ ነው ያለበት፡፡ ሕግ መቀየሩና የመሳሰለው ሁሉ ቀስ ተብሎ ይደረስበታል፤ ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ግን ሊሠሩ የሚገባቸውን ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት አለባቸው፡፡
ዘመን፡- ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን በፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ለመተካት የሚፈልጉ ፖለቲከኞችና ድርጅቶች አሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ለውጥ የሚገኘው ፖለቲካዊ ትርፍና የሚያስከትለው ስጋት ምንድነው?

አቶ ጃዋር፡- በመጀመሪያ ደረጃ አይችሉም፡፡ አሸንፈው የመለወጥ ሥልጣን እስኪያገኙ ድረስ ያንን ማድረግ አይችሉም፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እናውራ ከተባለ ግን ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚፈልጉ ሰዎች በተለይ የተከፋፈለ ማኅበረሰብ ባለበት ውስጥ ወጣ ያለ ድጋፍ ያለው አሸንፌ ፕሬዚዳንት መሆን እችላለሁ ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በአንጻራዊነት የተረጋጋ ነው፡፡ የሚያረጋጋው አገሩን ሳይሆን ሥርዓቱን ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተመረጠበት የጊዜ ወሰን የፈለገውን ፖሊሲ ያለ ምንም ችግር እንደልቡ ማስፈጸም ስለሚችል ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጠቀሜታ አለው የሚል መከራከሪያም ይነሣል፡፡

ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ደግሞ በተለይ ለታዳጊ አገር ኤሊት ባርጌኒንግ (የልኂቃን ድርድር) ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አንድም ሰው በቂ ድምጽ አግኝቶ ወደ ሥልጣን ሊመጣ ስለማይችል ቋሚ ለሆነ ድርድር በር ይከፍታል፡፡ ተመራጩ በሚመረጥባቸው ወረዳዎች ተቀባይነት አግኝቶ በፓርቲው መመረጥ አለበት፡፡ ቀጥሎም አንድ ፓርቲ ለብቻው አሸንፎ ሥልጣን የመያዝ አቅም ስለማይኖረው ከሌላው ጋር ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለመደራደር ይገደዳል፡፡ ሥልጣን ከያዘ በኋላም ጠቅላይ ሚንስትሩ የሁሉንም ቡድኖች ፍላጎት የሚያስጠብቅ የተማከለ ውሳኔ ነው ይዞ የሚሔደው፡፡ አለበለዚያ ከፓርቲዎቹ አንዱ ራሱን በማግለል ከሥልጣን ሊያወርደው ይችላል፡፡

ስለዚህ በሕግ አስፈጻሚው ላይ ያለው የሕግ አውጪው ቁጥጥር ከፍተኛ ነው፡፡
ሕዝብን ለማቀራረብ፣ በተለይም ሕዝቡን የሚወክለውን ኤሊት ለማቀራረብ ይረዳል፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ዋልታዊ (ፖላራይዚንግ) ነው፡፡ የተወሰኑ ክልሎችን ብቻ ነው ይዞ የሚነሣው፡፡ በተለይ ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የሁሉንም ሐሳብ ለመስማት ስለማይገደድ የፈለገውን ውሳኔ ብቻ እየወሰነ ይቀጥላል፡፡ በዚህም ያልረኩት እየተከፋፈሉ ወደ ጦርነትም ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት አምባገነኖችን የመፍጠር ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ መለስ እኮ ጦር ባይኖረው ኖሮ አምባ ገነን ሊሆን አይችልም ነበር፡፡

ጦሩ በትጥቅ ትግል ወቅት የተፈጠረና ከዚያው ይዞት የመጣ ባይሆን ኖሮ በፍጹም አይችልም ነበር፡፡ አሁን አቢይ ጦር የለውም፡፡ ስለዚህ አምባገነን የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ በፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ግን ፕሬዚዳንቱ ሙሉ ቁጥጥር ስላለው አምባገነን ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ስንመለከተው ኢትዮጵያን ለመሰለ አገር ፓርላሜንታዊ ሥርዓት የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ዘመን፡- ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓትን የሚፈልጉ በሕዝብ ብዛት ገዘፍ ካለ ብሔረሰብ ድጋፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ ናቸው ብለው ያስባሉን?
አቶ ጃዋር፡- አዎ! ያሰሉታል፡፡ ለምሳሌ እኔ የፖለቲካ ፍላጎት ቢኖረኝና ፍላጎቴም ግላዊ ከሆነ ፕሬዚዳንታዊውን ሥርዓት በጣም ነው የምወደው፡፡ ምክንያቱም ከኦሮሞ ሰላሳ ከመቶ ድጋፍ ባገኝ፣ ከአማራ የተወሰነ፣ ከደቡብና ከሶማሌም ጨምሬበት አብላጫ ድምጽ ሊኖረኝ ይችላል ማለት ነው፡፡ በሕዝብ ታዋቂ እስከሆንክ ድረስ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ይህ ግን ለሕዝብ ማሰብ አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የተከፋፈለ አገር ይዘህ ሁሉም ሳይበታተን ወደ መሀል እንዲመጣ ከፈለክ ሁሉም የድፎ ዳቦው ተቋዳሽ መሆን አለበት፡፡ ድፎ ዳቦውን ሲቋደስ ግን አንዱ ለሌላው እንደለማኝ እየጣለለት መሆን የለበትም፡፡ አስገድዶ እንዲቆርስልህ ማድረግ መቻል አለብህ፡፡

ሥልጣኑን የያዝኩት እኔ ብሆን ላንተ ስቆርስልህ የግዴታ አንተ ስለምታስፈልገኝ መሆን አለበት፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ላይ አንዴ ከተመረጥኩ በኋላ አታስፈልገኝም፡፡ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ግን ሥልጣን ለመያዝም ሆነ ለመቀጠል ታስፈልገኛለህ፤ ፖሊሲ ለማስፈጸምም ታስፈልገኛለህ፤ ለበጀትም ታስፈልገኛለህ፡፡ እኔና አንተ በመደበኛነት ያቺን ድፎ ዳቦ እየቆራረስን ስንካፈል ከመኖር ውጪ አማራጭ አይኖረንም፡፡ ያ ማለት እየተቀራረብን በጋራ ጥገኝነት ሥርዓት (ኢንተርዲፔንደንስ) ውስጥ ነው የምኖረው ማለት ነው፡፡ የመገንጠል አደጋ በሚያንዣብብበት አገር ውስጥ ፓርላሜንታዊ ሥርአት ይበልጥ ያስፈልጋል፡፡

እዚህ አገር ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች ‹ኤሊት ባርጌኒንግ (የልኂቃን ድርድር) አስፈላጊ ነው› ብለው ደጋግመው እየተናገሩ በሌላ በኩል ደግሞ ‹ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ይሻላል› እያሉ ሲሰብኩ ሳይ ሐሳባቸው ይጋጭብኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ታዋቂ ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ናቸው ይህን የሚፈልጉት፡፡
በበኩሌ የምመክረው ግን የምንታገለው ለራሳችን ከሆነ የትም አንደርስም፡፡ የታገልነው ዓለማ ከግብ ሲደርስ ተጠቃሚ የሚሆነው በጣም ጥቂት ሰው ነው፡፡ ዛሬ የምንታገለው የእኛ ልጆች እኛ ያደግንበትን ጭቆናና እኛ የኖርንበትን ግፍና ድህነት እንዳይወርሱ ነው፡፡ ጥቅሙ ለቀጣዩ ትውልድ መትረፍ አለበት፡፡ ሰሞኑን ከአንድ አንጋፋ ፖለቲከኛ ጋር ስወያይ አንድ የሚገርም ሐሳብ አካፈሉኝ፡፡ ‹እዚህ አገር ሕግ ሲወጣ አንድን ሰው ታሳቢ አድርጎ የሚወጣበት ጊዜ አለ፤ ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ ያ ሰው ሺህ ዓመት እንደሚኖር ሆኖ ነው ሕጉ የሚወጣው› ስለዚህ ቁንጮ ላይ ያለውን ሰው ሳይሆን አጠቃላይ ሥርዓቱ ሁሉን ተጠቃሚ ሊያደረግና ሰላም ሊያሰፍን በሚችልበት መልኩ ነው መቀረጽ ያለበት፡፡ አሁን እዚህ አገር የብሔር ግጭት እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ ‹ይህን ግጭት የሚያስቀረው የትኛውን ብንከተል ነው?› ተብሎ መታሰብ አለበት፡፡ በእኔ ግምት ፓርላሜንታዊው ሥርዓት የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ይበልጥ እያጠናን ልንወያይበትና ልንከራከርበት ይገባል፡፡

ዘመን፡- አሁን ያለውን አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምን ያሰጋዋል ብለው ያስባሉ?
አቶ ጃዋር፡- ዋናው አደጋ የኢኮኖሚው መዳከም ነው፡፡ አሁን ከተማዋን ብትቃኝ የተጀመሩ ፎቆች ሁሉ ሥራቸው ቆሟል፡፡ ይህ ኢኮኖሚው ያለበትን ችግር ጠቋሚ ነው፡፡ ሦስት መቶ ፎቆች ሥራ ካቆሙ፣ ምናልባት እያንዳንዱ ውስጥ የሚሠሩ ሦስት መቶ ሰዎች አሉ ብንል ወደ ዘጠና ሺ ሰው ሥራ ፈቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ጫና አለው፡፡

ሁለተኛ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል፤ ግን ቦይ አልተበጀለትም፡፡ ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ ብቻዋን ሜዳ ውስጥ ኳስ ትጫወት ነበር፡፡ መስመሩም የራሷ ነው፡፡ ደስ ሲላት ገፋ፣ ደስ ሲላት ቀረብ ታደርገዋለች፡፡ ጎሉን ሲመቻት ታሰፋዋለች፤ ሲመቻት ታጠበዋለች፡፡ ዳኛው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ቲፎዞዎቹ በሙሉ ኢሕአዴጎች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ከዲቪዥን ኤፍ የመጡ ተጫዋቾች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ብቻዋን ነበር ስትጫወት የኖረችው፡፡ አሁን ሁሉም እንዲገቡ ተፈቀደላቸው፡፡ ግን የግብ ቋሚው አይታወቅም፤ ዳኛው ላይ አመኔታ የለም፤ የጨዋታው ሕግ አልታወቀም፤ ቲፎዞው ድብልቅልቁ ወጥቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ጨዋታው እየተጀመረ ያለው፡፡ እኔ ይህን ችግር እየጠቆምኩ ስለፈልፍ ስድስት ወር ሞላኝ፡፡ ሁለት ቡድኖች ለመጫወት ገና ሰውነት ሲያሟሙቁ የአንዱን እግር አንዱ ይጠልዘውና የተደበላለቀው ቲፎዞ የባሰ ድብልቅልቅ ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ ገዢውን ፓርቲና ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ቁጭ ብለው የጨዋታውን ሕግ ማውጣት አለባቸው፡፡ የሚያስተማምን የምርጫ ሕግ፣ የሚስተማምን የምርጫ አሠራር፣ የሚያስተማምን የፓርቲዎች ሕገ ደምብም ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡
ዘመን፡- ሥርዓት አልበኝነት ሥርዓቱን አያሰጋውም?

አቶ ጃዋር፡- ሕዝቡ እኮ ሥርዓት አልበኛ አይደለም፡፡ ካለው ጫና፣ ከነበረው አፈና አሁን ትንሽ ፈታ ሲል የታዩ ነገሮች የሚጋነኑ አይደሉም፡፡ የሚነሡት ግጭቶች አሳዛኝ ናቸው፡፡ ግን ሊደርስ ከሚችለውና በሌሎች አገሮች ከደረሰው አንጻር ብዙ ትልቅ አይደለም፡፡ እዚህ አገር እኮ አገር እያስተዳደረ ያለው እግዚአብሔር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከታች ያለው የመንግሥት መዋቅር ወላልቋል፡፡ ወላልቆም ግን ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እየገባ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ እኮ ሊከበር ይገባዋል፡፡

ሌሎች አገሮችን ተመልከት፡፡ እኔ ሰባ ምናምን አገር ሔጃለሁ፡፡ አይደለም እንደኛ ብዙ ችግር ያለበትን ተወውና የተረጋጋውና ጠንካራ መንግሥት ባለበትም ትንሽ የኢኮኖሚ ችግር ሲከሰት የሚመጣው ቀውስ ቀላል አይምሰልህ፡፡ እዚህ አገር ሕዝቡ በጣም ታጋሽ ነው፡፡ ሲብስበት እኮ ነው ኢሕአዴግንም ራሱ ነክሶ ያባረረው፡፡ አሁን ሥርዓት እንገንባ እያልን ነው፡፡
የጠመንጃ አገዛዝ ነበር፤ ተሸነፈ፡፡ ድሮ ሰው ጠመንጃ ፈርቶ ይገዛል፡፡ በዴሞክራሲ ውስጥ ደግሞ ሕግ አክብሮ ይገዛል፡፡ ያ እንዲሆን ከፈለክ የልኂቃኑ ሥራ መሆን ያለበት ሕዝብ ሊያከብረው የሚችል ሕግን ማስፈን ነው፡፡ ያን ሕግ ሕዝብ ሊያከብረው የሚችለው ደግሞ በሕዝብ ተሳትፎ ሲሠራ ነው፡፡ ሕዝብ ሊሳተፍ የሚችለው ደግሞ ወኪሎችን በመምረጥ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት ያለባት አገር እንድትኖረን ከፈለግን ሊከበር የሚችል ሕግ አምጥተን ጨቋኙን ሕግ ልንተካ ይገባናል፡፡ ሥርዓት አልበኝነቱ ሊስፋፋ የሚችለው ልኂቃኑ ከተንከረፈፉና በራቸውን ዘግተው ሊሠሩት የሚገባቸውን የድርድርና የውይይት ሥራ ትተው ወይ ባቋራጭ ሥልጣን ላይ ለመውጣት ወይ ደግሞ ጊዜ እየገዙ ራሳቸው አምባገነን ለመሆን የሚያደላድሉ ከሆነ ያን ጊዜ ሥርዓት አልበኝነቱ እየሰፋ ይሔዳል፡፡ የሥርዓት አልበኝነቱ መንሥዔም ሕዝብ አይመስለኝም፤ የልኂቃኑ መንከርፈፍ እንጂ፡፡
ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊና ዝርዝር ምላሽ እናመሰግናለን።
አቶ ጃዋር፡- እኔም አመሰግናለሁ!


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE