ብሊንከን እየተሻሻለ ነው ያሉትን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ አደነቁ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እየተሻሻለ ነው ያሉትን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረግ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት አደነቁ።

ብሊንከን ትናንት ባወጡት መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እየተጓጓዘ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መደበኛና ቀጣይነት ያለው እየሆነ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው ማለታቸውን ጠቅሷል።

ባለፉት ሰባት ቀናት የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ 1 ሺህ 100 የሚሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸው በዚህ መግለጫ ተጠቅሷል።

ተሽከርካሪዎቹ አስፈላጊ ሕይወት አድን ምግቦች፣ የጤና ቁሳቁሶች፣ አልሚ ምግቦች እና ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዙ ናቸው ሲሉ በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥራ ቤቱ ኃላፊው የሰብዓዊ እርዳታው ሰዎች ጋር እንዲደርስ የፌደራሉ መንግሥት፣ የአፋር ክልላዊ አስተዳደር እና የትግራይ ክልላዊ አስተዳደር ላደረጉት የተቀናጀ ትብብር አድናቆታቸውን ችረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሚገኙ መሥሪያ ቤቶችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶችም ከብሊነክን ምስጋና ተችሯቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ከትናንት በስቲያ ሰኞ ግንቦት 29/2014 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ወደ ትግራይ ክልል ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ 2.1 ቢሊየን ብርና 87 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ እንዲሁም ከ783 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተልኳል ብለው ነበር።

ለአማራ ክልል ተፈናቃዮችም 244 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጭቱን ቢልለኔ ስዩም ጨምረው ተናግረዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አስክትሏል። ጦርነቱ በተለይ በትግራይ ከፍተኛ የሰዓዊ ቀውስን አስከትሏል።

በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚሻ የእርዳታ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

ይህንም ተከትሎም ባለፈው መጋቢት ወር የፌደራሉ መንግሥቱ ወደ ክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ለማስቻል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ የህወሓት መሪዎችም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ቢስማሙም በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በቂ እርዳታ ሳይደርስ ቆይቷል። ለዚህም ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት አንዱ ሌላኛውን ተጠያቂ ሲያደርጉ ነበር።

ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ያሻል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ግንቦት 30/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ አሁን እየታየ ያለውን በጎ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ወደ ንግግር በመግባት ለግጭቱ የማያዳግምና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ያሻል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ብሊንከንመሠረታዊ መሠረተ ልማቶችና የግንኙነት መስመሮችም ግጭቱ ባለባቸው አካባቢዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ጥረት እንዲደረግ፣ ሁሉን አካታች ንግግር እንዲጀመር፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሁሉም አካላት ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑም በዚሁ መግለጫቸው ጠይቀዋል።