ድርቅ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ አፋር እና ደቡብ ኢትዮጵያ 10 ሚሊየን ህዝብ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ማሳረፉ ተገልጧል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ምስራቅ አፍሪቃን የመታው ድርቅ ከ10 ሚሊየን በላይ ህጻናት ለአስከፊ የምግብ እጥረት መዳረጉን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ተራድኦ ድርጅት (UNICEF) ዐስታወቀ። ድርቁ በአራት ክልሎች በሰፊው የተከሰተባት ኢትዮጵያ ከችግሩ ለመላቀቅ ቢያንስ 5 ዓመታት ያስፈልጓታልም ተብሏል።  በኢትዮጵያ አራት ክልሎች (ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ አፋር እና ደቡብ ኢትዮጵያ) ድርቁ 10 ሚሊየን ህዝብ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ማሳረፉ ተገልጧል።

በኢትዮጵያ ባጋጠመው ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች የዝናብ እጥረት በዓመታት አስከፊ የድርቅ ሁኔታ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑ ነው የሚነገረው። በተለይም በዚህ ዓመት ተፅእኖው ጎልቶ የወጣው ድርቅ፤ ለበርካታ እንስሳት ሞት ምክንያት ሲሆን የውኃ ምንጮችም ተሟጠው እንዲደርቁ መንስኤ ሆኗል። እንደ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ተራድኦ ድርጅት (UNICEF) መረጃ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች (ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ አፋር እና ደቡብ ኢትዮጵያ) ድርቁ 10 ሚሊየን ህዝብ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ሲያሳርፍ ከዚህ ውስጥ 1.5 ያህሉ ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት የተዳረጉ ህጻናት ናቸው፡፡ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ምክትል ኃላፊ ሚካኤል ሴርቫዴይ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩትም 1.75 ሚሊየን ህዝብን ከመኖሪያ ቀዬያቸው ያፈናቀለው ድርቁ እጅጉን አስከፊም ነው፡፡

“አሁን ወቅቱ የዝናብ ወቅት እንደመሆኑ ተፈላጊው ዝናብ ብጥል እንኳ ኢትዮጵያ ድርቁ ካሳረፈው ጉዳት ለማገገም አምስት ዓመታት ያህል ይፈጃል፡፡ ይሄ ደግሞ የችግሩን አሳሳብነት ይገልጻል፡፡”
ድርቁ ባስከተለው የምግብ እጥረት ችግር በሶማሊ ክልል ብቻ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 220 ሺህ ህጻናት ገደማ የተመጣጠነ ምግብ እጦት አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ ክልል ከ150 ሺህ በላይ አጥቢና እርጉዝ እናቶች በቂ ምግብ የማያገኙ ናቸው፡፡ እንደ ዩኒሴፍ መረጃ በክልሉ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር ላልተመጣጣነ ምግብ ችግር የተዳረጉ ህጻናት ቁጥር ከ30-40 በመቶ ጨምረዋል፡፡

“የተመጣጠነ ምግብ እጦት አንዱ የምንሰራበት የትኩረት አቅጣጫችን ሲሆን ሌላው ድርቁ ያስከተለው ችግር በምግብ እጦት አሊያም አለመመጣጠን የሚመጡ የበሽታዎች ወረርሽኝ ነው፡፡ በንፁህ ውሃ እጥረት ህጻናት እንደኮሌራ ላሉ ውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ ለአብነት ያህል በኦሮሚያ ባሌ ዞን 600 ህጻናት ኮሌራ በሚመስል በሽታ ተጠርጥረው ነው ያሉት፡፡ ተጠርጥረው ነው ያልኩት፡፡ በትክክልም ደግሞ ድርቁ ከቀጠለ ይህ ኮሌራ መሰል በሽታም ስለሚቀጥል የችግሩን ደረጃ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡”

Das Logo und der Schriftzug der Hilfsorganisation UNICEF sind am 5. Februar 2008 an der Zentrale in Koeln zu sehen.

በሌላ በኩል ድርቁ ያሳረፈው ማህበራዊ ችግርም በቀላሉ የሚታይ አልሆነም፡፡ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በችግሩ ሳቢያ ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተቆራርጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ምስቅልቅሎችን አሳርፏል፡፡ እንደ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ምክትል ኃላፊ ሚካኤል ሴርቫዴይ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ የናሬው የስንዴ እና ሌሎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ የድርቅ ተፅእኖውን ምላሽ የመስጠት ጥረቶችን አዳጋች አድርጎታል፡፡

“ድርቁ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ በዚህ አነሳን እንጂ እንደ አፍሪካ ቀንድ ካነሳን ደግሞ ችግሩ ይጎላል፡፡ በቃጣናው ድርቁ 10 ሚሊየን ህጻናትን ለምግብ እጦት ዳርጎ አስርቧቸዋል፡፡ በርግጥ እስካሁን በርሃም አደጋው የሞተ ሰው አላጋጠመንም፡፡ ነገር ግን በውሃ እጥረትና ምግብ እጦት በተለይም ህጻናት ለአስከፊ ህመም እየተዳረጉ ነው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አጥቢና እርጉዝ እናቶች ለምግብ እጦት እየተዳረጉ ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ መስጠትም አይችሉም፡፡ ቀውሱ መልከ ብዙ ነው፡፡”

ባለፈው ወር በኦሮሚያ ቦረና ዞን አከባቢ የጣለው ዝናብ በድርቁ የተፈተኑትን አፋርና ሶማሊን እንዳልጎበኛቸው የተራድኦ ድርጅቱ መረጃ ያስረዳል፡፡ የእርዳታ ድርጅቶቹ በምግብ እጦት ለህመም የተዳረጉትን ከ200 ሺህ በላይ ህጻናት ህክምና እንዲያገኙ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ከህጻናቱ በተጨማሪ እርግዝና ላይ ያሉና የሚያጠቡ እናቶችን ትኩረት ያደረገ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ላይም ረጂ ተቋማቱ በትኩረት እየሰሩ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ይሁንና የእርዳታ ቁሳቁሶች እጥረት ሌላው ፈተና ነው፡፡

“በዚህ ዓመት ብቻ በድርቅ ለተጎዱ ለርዳታ ምላሽ የጠየቅነው ድጋፍ 65 ሚሊየን ዶላር አካባቢ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ያለብን የበጀት ክፍተት 90 በመቶ ያህል ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ማህበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ መስራት ቀዳሚው ትኩረታችን አድርገን እየሰራንበት ነው፡፡ ድርቁ በፈጠረው ቀውስ ለምግብ እጥረት የተዳረጉ ሕጻናትን ተደራሽ ማድረግ ሌላው ትኩረታችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የረጂም ጊዜ ኢንቨስትመንት ያሻዋል፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አከባቢ ከድርቅ በተጨማሪ ግጭቶች ተንሰራፍተው በመገኘታቸው ተጨማሪ የድጋፍ በጀት ይፈልጋሉ፡፡ ግን ድርቁ ከፍተኛ ትኩረት ነው ማግኘት ያለበት፡፡ በተለይም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያም አልፎ አልፎ ስጋት ያጫረው የኮሌራ ወረርሽኝ ክስተት ቶሎ ካልተቆጣጠርነው ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ እንዲፈጠር አንፈልግም”