" /> ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለነጻነት ተጋድሎ ያደረጉበት ቤት ሙዚዬም ሆነ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለነጻነት ተጋድሎ ያደረጉበት ቤት ሙዚዬም ሆነ

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለነጻነት ተጋድሎ ያደረጉበት ቤት ሙዚዬም ሆነ፡፡ በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በመግዛት ነው ቤቱን ሙዚዬም ያደረጉት፡፡

(አብመድ) ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄን በመያዝ ሲንቀሳቀሱ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይል ጋር በተፈጠረ ግጭት የተታኮሱበትና በኪራይ ይኖሩበት የነበረው ቤት ወደ ሙዚዬምነት ተቀየረ፡፡

በጎንደር ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 18 ሕዳሴ ሰፈር (ደሳለኝ ትምህርት ቤት) አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤት ሐምሌ 05 ቀን 2008 ዓ.ም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ በተደረገ ሙከራ በጥይት ተመትቷል፡፡

የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴም የትግሉን ምዕራፍ አቅጣጫ የለወጠና የአማራን ተጋድሎ ከፍ ያደረገ ክስተት አድርጎ በመቁጠር ቤቱ ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

እነ አቶ አታላይ ዛፌ፣ ንግስት ይርጋንና ሌሎችንም የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የትግሉ ደጋዎች በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ከግለሰቡ በመግዛት ነው ቤቱን ሙዚዬም ያደረጉት፡፡
በሙዚዬሙ ለአማራ ሕዝብ ማንነትና መብት መከበር የታገሉ፣ የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉ ሁሉ ማስታወሻ እንደሚቀመጥበት ሰምተናል፡፡

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ባደረጉት ንግግርም ሙዚዬሙ ወጣቱ ትውልድ ለዕውነት ከታገለ የሚፈልገውን ለውጥ የሚያይበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ሙዚዬሙ ዛሬ በይፋ ተመርቆ ሥራ የሚጀምር መሆኑ ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV