ባለቤት ያጣው የነዳጅ ሥርጭትና የሚያስከትለው መዘዝ

ሪፖርተር ኣማርኛ ( ዳዊት ታዬ )

ከጥቂት ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለው የነዳጅ እጥረት ኅብረተሰቡን እያማረረ ነው፡፡ ለትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል ምክንያት ሆኗል፡፡ ነዳጅ ለመቅዳት የሚወስደው ጊዜ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ሲሳርፍ ይታያል፡፡ በነዳጅ ማደያዎች የለም የተባለው ቢንዚን ግን ከማደያ ውጪ ለመግዛት ከተፈለገ በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚዎችም እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህ ከሕገወጥ የቤንዚን ንግድ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ይናገራሉ፡፡

ይህ ችግር የበረታው ከጥቅምት 2011 ዓ.ም. ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ነው፡፡ አቶ ታደሰ እንደሚገልጹት፣ ቀደም ባሉት ከሐምሌ 2010 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም. ድረስ ያለምንም ችግር የነዳጅ ሥርጭቱ ይካሄድ እንደነበር ነው፡፡

ሆኖም ከጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ በየማደያው የተፈጠረው መጨናነቅ ከነዳጅ ድርጅቱ ዕውቅና ውጭ እየተፈጸመ ያለ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ያስፈልጋል የተባለውን ነዳጅ ያለምንም ችግር በበቂ ሁኔታ እያቀረበ በመሆኑ እጥረት ሊፈጠር የሚችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

ይህንንም አኃዛዊ በሆነ መረጃ ሲያብራሩም በሐምሌ 2010 ዓ.ም. 1.7 ሚሊዮን ሊትር፣ በነሐሴ 2010 ዓ.ም. 1.8 ሚሊዮን ሊትር በመስከረም 2011 ዓ.ም. 1.8 ሚሊዮን ሊትር ተሠራጭቷል፡፡ በጥቅምት 2011 ደግሞ ለወሩ ከተያዘውና ያስፈልጋል ከተባለው ነዳጅ መጠን በላይ 1.9 ሚሊዮን ሊትር ተሠራጭቷል፡፡

ይህ የተሠራጨው ነዳጅ የአገሪቱን የነዳጅ ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ በተሠራ ጥናት እንዲሠራጭ የተደረገ ስለሆነ፣ በእነዚህ ሦስት ወራት ችግሩ ሳይታይ ነዳጅ እንዲሠራጭ መደረጉና በሥርጭት ረገድ ምንም ችግር የሌለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ችግሩ ነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማመልከት እንደ መረጃ የሚቀርበው ነጥብ ባለፈው ወር ከሚያስፈልገው ነዳጅ በላይ ተጨማሪ ነዳጅ ከመጠባበቂያ ማከማቻ ጭምር ወጥቶ እንዲሠራጭ ቢደረግም፣ በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ የሚታየው መጨናነቅ ያለመለወጡ ኅብረተሰቡን እያጉላላ ይገኛል፡፡ ከሚፈለገው በላይ ነዳጅ ከቀረበ ችግሩ ለምን ተከሰተ? የሚለው ጥያቄ ሲታይ ግን፣ ችግሩ ሰው ሠራሽ ስለመሆኑ አቶ ታደሰ በቁጭት ይናገራሉ፡፡

ዋና ችግሩ ደግሞ ከየማደያዎቹ በሕገወጥ መንገድ በበርሜሎች ተጭኖ ወጥቶ በየመንደሮቹ በችርቻሮ እንዲሸጥ እየተደረገ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በእጅጉ ከበረታበት ጥቅምት 2011 ዓ.ም. ወዲህ በተደረገ የዳሰሳ ምልከታ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የከተማው ክፍል በየመንደሩ ቤንዚን በችርቻሮ የሚሸጡ ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ያመለከተ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የችግሩን መጠን ለማወቅ በአዲስ አበባ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ያገኘው ውጤት ይህንኑ ያመለክታል፡፡ በአንድ ቀን ብቻ በሦስት ቡድን ተከፋፍሎ በናሙናነት የተገኙትን ሕገወጥ የቤንዚን መሸጫ ቦታዎች እስከመለየት ደርሷል፡፡ ሥር ነቀል ዳሰሳ ቢደረግ ብዙ እንዳሉ ለማወቅ ይቻላል ይላል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ የቤንዚን መሸጫ ዋጋ በሊትር 18.77 ብር ሲሆን፣ ከተመን በላይ እስከ 44 በመቶ ተጨምሮ በየስርቻው እየተሸጠ መሆኑንም ከድርጅቱ ጥናት ላይ  ተመልክቷል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ በሕገወጥ መንገድ ቤንዚን ሲቸረችሩ የደረሰባቸው አካባቢዎችም የካ አባዶ መታጠፊያ፣ አያት 49 ማዞሪያ፣ ኃይሌ  ጋርመንት፣ ወደ ሃና ማሪያም መታጠፊያ፣ ላፍቶ መብራት ኃይል፣ ዓለም ባንክ ስልጤ ሠፈር አካባቢ፣ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ከሾላ ወደ ቀጨኔ በሚወስደው መንገድና ቀጨኔ ይገኙበታል፡፡ ሌላው የጥናት ቡድን ደግሞ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ማስተም ሆቴል፣ ብርጭቆ ፋብሪካ አስኮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ዊንጌት እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ጀርባ፣ ሕገወጥ የቤንዚን ሽያጭ ሲካሄድ እንደነበር ማረጋገጡን ሪፖርት አድርጓል፡፡ ሌላው ቡድን ደግሞ ሽሮ ሜዳ ላዳ መኪና ማቆሚያ አካባቢ፣ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ኬላ አካባቢ ጎሚስታ፣ ፈረንሣይ ለጋሲዮን ማዞሪያ ጎሚስታ ውስጥ በጀሪካን ቤንዚን ሲቸበችብ እንደነበር ማረጋገጥ ሲችሉ፣ ይህም ሕገወጥ ሽያጭ አንዱን ሊትር በአማካይ 25 ብር እየተሸጠ መሆኑን ያሳያል፡፡

በችርቻሮ በየመንደሩ የሚሸጠው ቤንዚን ከሱቆችና መጠለያ ካላቸው ቤቶች ባሻገር ሁለት ሊትር መያዝ በሚችሉ የውኃ ፕላስቲኮች ተሞልተው በታክሲዎች ላይ ጭምር እየተሸጡ ነው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ የሚሸጠው ቤንዚን ሁለቱን ሊትር ከ50 እስከ 54 ብር ዋጋ ያወጣል፡፡ አንዳንዴም እጥረቱ ባሰ ሲባል 60 ብር የሚሸጡበት አጋጣሚ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን ማግኘት ያልቻሉ አሽከርካሪዎች ከእነዚህ በሕገወጥ መንገድ ቤንዚን ከሚቸበችቡ ግለሰቦች መግዛት ደግሞ ችግሩን ሊያብሰው ችሏል፡፡

አንድ አሽከርካሪ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የገጠማቸው የቤንዚን ችግር ለመቅረፍ በሰዎች ጥቆማ ከመንደር ቤንዚን ቸርቻሪዎች ቤንዚን ለመግዛት መገደዳቸውን ይናገራል፡፡

ቤንዚኑን ያገኙት በደላላ ሲሆን፣ አንድ ሊትር ቤንዚን በ30 ብር ገዝተው ተጠቅመዋል፡፡ ይኼንን ያደረጉት ስለቸገራቸው መሆኑን የሚጠቅሱት እኚሁ አሽከርካሪ፣ በመንደር ስለሚሸጠው ቤንዚን ለማጣራት አድርጌያለሁ ባሉት ማጣራት የነዳጅ ማደያ ሠራተኞች ከቤንዚን ቸርቻሪዎች ጋር በመመሳጠር የሚሠሩ ሲሆን፣ ቤንዚኑን ለማሻሻጥም ሊስትሮዎች ጭምር በመሳተፍ ሕገወጥ ሥራውን እየደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እኚሁ አስተያየት ሰጪ አስሽከርካሪ ቤንዚኑን ሲገዙ መጀመርያ ወደ መንደር ቤንዚን መሸጫ የወሰዳቸውም ሊስትሮ መሆኑን በማስታወስ ጉዳዩ ሰንሰለት ያለው መሆኑን ይጠቁማል፡፡

አቶ ታደሰ ከማደያዎች ውጭ ዛሬ በአዲስ አበባ ተስፋፍቶ ከመታየቱ ቀደም ብሎ እንዲህ ያለው ችግር ይታይ የነበረው በአንዳንድ የክልል ከተሞች ነበር ይላሉ፡፡ ከእነዚህ ከተሞች ውስጥ አንዱ ድሬዳዋ ከተማ ነበር፡፡ ከከተማው የንግድ ቢሮ የተገኘው መረጃ ይህንን ያመለክታል፡፡

ይህንኑ በመገንዘብ በእነዚህ ከተሞች ጥናት በማድረግ ችግሩን የሚያሳይ መረጃ ለሚመለከተው ክፍል አቅርበን ነበር፡፡ ዕርምጃ ባለመወሰዱ አሁን አዲስ አበባ ላይ ሊስፋፋ ችሏል፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከማደያዎች ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አመላካች ሆኗል፡፡

ለዚህም በቅርቡ እንኳን በከተማዋ በሚገኙ በተለያዩ ማደያዎች በሕገወጥ መንገድ በበርሜል ተጭኖ ሊወጣ የነበረ ቤንዚን ስለመያዙ ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ተያዙ እንጂ ያልተያዙት አሁንም በየመንደሩ ቤንዚን እየቸረቸሩ የአገሪቱን የቤንዚን ግብይት እያሰነካከሉ ናቸው፡፡

ለችግሩ መባባስ ሌላው ምክንያት የሆነው ደግሞ እነዚህ በሕገወጥ መንገድ የተጫኑ የቤንዚን በርሜሎችን ይዘው ሊወጡ ሲሉ የተያዙት ግለሰቦች ላይም ሆነ ነዳጁን በበርሜል የሸጠው የነዳጅ ማደያ ላይ ዕርምጃ አለመወሰዱ ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ አካባቢ የተጫኑ በርሜሎች ሲያዙ የተወሰደው ዕርምጃ የተቀዳው ነዳጅ ወደ ማደያው እንዲመለስ ማድረግ ብቻ በመሆኑ፣ የነዳጅ ሥርጭት ጉዳይ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ የገባ መሆኑንና ሕገወጦችን ለመከላከል ያልተቻለ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ይህም ዘርፉ ባለቤት ያጣ እየሆነ መምጣቱን አቶ ታደሰ ገልጸው፣ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉት መንግሥታዊ አካላት ምንም ዕርምጃ አለመውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችለው አሠራር አለመኖሩን እንደ ችግር ያነሳል፡፡ ነዳጅን የተመለከተ የቁጥጥርና የሥርጭት መመርያ አለመኖር ከሰሞኑ በተለያየ ቦታ በተያዙ በርሜሎች ተቀድተው ሊወጡ የነበረውን ነዳጅ መያዝ ቢችልም፣ በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ያልተቻለው ለዚህ የሚሆን መመርያ አለመኖር ነው፡፡ ነገር ግን የተያዘው ነዳጅ ወደ ማደያው እንዲገባ በማድረግና በበርሜል ሽያጭ አድርገዋል የተባሉ የነዳጅ ማደያዎችን ማስጠንቀቂያ እየሰጠ በመቆጣጠር ብቻ መገደቡን የሚያመለክት ነው፡፡

የነዳጅ ሥርጭት በአግባቡ ስለመከናወኑና ከሰሞኑ እንደታየው በሕገወጥ መንገድ ከማደያዎች በበርሜል ተሞልተው በሕገወጥ መንገድ ገበያ ላይ የመዋላቸው ነገር የሚቆጣጠርበት ሥልት የለም ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ የሌለው መስሏል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በአዋጅ የተሰጠኝ ሥልጣን ነዳጅ ወደብ ድረስ አምጥቶ ለነዳጅ ኩባንያዎች ማከፋፈል ነው ይላል፡፡ በእርግጥም ኃላፊነቱ ይህ ነው፡፡ አቶ ታደሰ እንደገለጹት ደግሞ፣ ኃላፊነታቸው በዚህ ደረጃ የተገደበና የነዳጅ ሥርጭትና የቁጥጥር ሥራን የሚሠራው እንደ ንግድ ሚኒስቴር፣ በክልል ደግሞ የንግድ ቢሮዎች እንዲሁም የነዳጅና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ነው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ቁጥጥሩን እያደረጉ አለመሆኑ ሕገወጥ የወጪ ንግድ ፈታኝ እየሆነ ስለመምጣቱ ይጠቅሳሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማስፈጸሚያ መመርያ ስላልወጣ ነው በሚል በዚህ መሀል ግን የአገር ሀብት እየባከነና ሕገወጥ ተግባራት እየተስፋፉ መሆኑ ችግሩን ለማቃለል አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ሥራው ባለቤት አልባ ሆኗል ወደ ሚል መደምደሚያ እየወሰደ ነው፡፡ አቶ ታደሰም የነዳጅ ሥርጭትና ቁጥጥር ሥራ ባለቤት የሌለው ሆኗል በሚለው በብርቱ ይስማማሉ፡፡

በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ የንግድ ቢሮዎች ሕገወጥ የነዳጅ ሽያጭን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም፣ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸው መመርያ ባለመኖሩ የተያዘውን ነዳጅ ተመልሶ ለነዳጅ ማደያው እንዲመለስ ከማድረግ ውጪ አስተማሪ ዕርምጃ ሊወስዱ አለመቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው የቁጥጥር ሥራውን መሥራት አለበት የተባለው የነዳጅ ማደያዎችና የተፈትሮ ሀብት ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶችን ሥርጭት መቆጣጠር ቢሆንም፣ ይኼንን እያደረገ አይደለም፡፡ ንግድ ሚኒስቴርም እኔ ተመን አውጪ ነኝ በሚለው አቋሙ ላይ እንደፀና ነው፡፡

ነገር ግን የንግድ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባርን የተመለከተው መረጃ እንደሚጠቅሰው፣ ‹‹የአገር ውስጥ ንግድ እንዲስፋፋና ሕጋዊ አሠራር እንዲሠራና ተገቢነት ያላቸው ዕርምጃ ይወስዳል፤›› ይላል፡፡ ሌላው ሥልጣኑና ተግባሩ ደግሞ አግባብ ባላቸው ሕጎች መሠረት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን ይሰጣል እንዲሁም የተሰጡ የንግድ ሥራ ፈቃዶች ለተሰጠባቸው ዓላማዎች መዋላቸውን ይቆጣጠራል፡፡ እርሱ ግን ኃላፊነቱን የነዳጅ ዋጋ ተመን ላይ ብቻ የሚሠራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም ሕገወጥ ተግባሩን በመቆጣጠር ላይ ነኝ ቢልም ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያመች መመርያ የለኝም ይላል፡፡

የድሬዳዋ ንግድ ቢሮ ግን ከዚህ የተለየ ነገር ይታያል፡፡ በከተማ ውስጥ የታየውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ መመርያ የለም በሚል ብቻ ዝም አለማለቱና ዕርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀሱ ውጤት እንዳስገኘለት ያመለክታል፡፡

ሕገወጥ የነዳጅ ሽያጭን ለመቆጣጠር እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ የለም ቢባልም፣ የድሬዳዋ ንግድ ቢሮ ግን ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ እየተስተዋለ ያለው ዓይነት እጥረት ሲገጥመው የወሰደው ዕርምጃ የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር ማስቻሉን ይገልጻል፡፡

የድሬዳዋ ንግድ ቢሮ የኢንስፔክሽንና ሬጉራላቶሪ ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብደላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከስድስት ወራት በፊት በድሬዳዋ ከተማ ይታይ የነበረው የነዳጅ እጥረት አስተዳደሩን በከፍተኛ ሁኔታ ፈትኖ ነበር፡፡

ወደ ከተማው የሚላከው ነዳጅ ማደያ ከገባ በኋላ አለቀ ተብሎ ሽያጭ ይቆማል፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር አባብሶ በትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ህልውና እስከመፈታተን ደርሶም እንደነበር ይናገራሉ፡፡

እጥረቱ የተፈጠረው ግን ማደያዎች የመጣላቸውን ነዳጅ በበርሜልና በጀሪካን በጎን መሸጣቸው ስለነበር፣ ይህንን ለማቃለል አስተዳደሩ የወሰደው ዕርምጃ ከነዳጅ ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ቁጥጥር ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በጋራ የተደረሰበት ስምምነት ወደ ድሬዳዋ የሚመጣው ነዳጅ መጠን እንደታወቀና እያንዳንዱ ማደያ በትክክል መሸጡን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ ተደረገ፡፡

ይህም የንግድ ቢሮው ማታ ማደያዎቹ ሲዘጉ ምን ያህል መጠን እንደነበራቸው መመዝገብ፣ ጠዋት ላይ ማታ የተመዘገበውን መጠን መኖሩን በማረጋገጥ በትክክል ለተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲሸጥ በማድረግ ቀድሞ የነበረው ችግር ሊቀረፍ ችሏል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ በከተማ ውስጥ የሚፈጠረው ችግር የከፋ ነበር በማለት ገልጸዋል፡፡

ይህ የድሬዳዋ ተሞክሮ ከልብ ከተሠራ ሕገወጥነትን መከላከል እንደሚቻል ያሳየ ነው ተብሏል፡፡ አቶ ታደሰም የድሬዳዋ ንግድ ቢሮ የሄደበትን መንገድ ያደንቃሉ፡፡ ተቆጣጥረው በመሥራታቸው ይኸው ላለፉት ስድስት ወራት በድሬዳዋ ስለነዳጅ እጥረት አይሰማም፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ የነዳጅ ሥርጭት መረጋጋት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትም እጅ አለበት፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ የተላከው ነዳጅ ምን ያህል እንደሆነና በማን የነዳጅ ኩባንያ በኩል እንደተጫነ ሁሉ ለንግድ ቢሮው በየዕለቱ መረጃውን ስለሚሰጥ፣ ንግድ ቢሮው በዚሁ መሠረት እየተከታተለ አስቸጋሪ የነበረውን የነዳጅ እጥረት በሕጋዊ መንገድ እንዲሠራጭ ማድረግ ችሏል፡፡

ይህንን መጤ ችግር ለመቅረፍ ግን አቶ ታደሰ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡ ሕገወጦች ላይ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበትና ኅብረተሰቡን ከመንደር የቤንዚን ግዥ እንዲቆጠብና በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን መጠቆም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ማስፈጸሚያ ሕግ የለም እየተባለ የሚቆይበት ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

አቶ አህመድ በበኩላቸው መንግሥት ለዚህ የሚሆን መመርያ እስኪያወርድ ድረስ መጠበቅ የለበትም ይላሉ፡፡ ችግሩ የሁሉም ኅብረተሰብ ነው፡፡ ነዳጅ እጥረት የሚገጥመው ከሆነ በመልካም አስተዳደር ዕጦት በመሆኑ፣ መመርያ እስኪወርድ መጠበቅ አደጋ አለው፡፡ በድሬዳዋ ከተማ እንኳን ስድስት ሺሕ ባጃጆች አሉ፡፡ እነዚህ ባጃጆች ነዳጅ አጥተው ቢቀመጡ ስንት ሰው ሥራ ሊፈታ ነው? ስለዚህ ሁሉም የመቆጣሪያ ሥልት ነድፎ ሊሠራ ይገባል ይላሉ፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ችግሩ የነዳጅ ማደያዎች ከሆነ የማደያዎቹ ባለቤቶች ሠራተኞቻቸውን መቆጣጠር ግድ ይላቸዋል፡፡ ነዳጅ እንደ ሸቀጥ ሜዳ ላይ መሸጥ የሕግ ክፍተት መኖሩን የሚያሳይ ነውና እኔን አይመለከተኝም የሚሉ አካላት ሁሉ ሊጠየቁበት ይገባልም ብለዋል፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከል መመርያ የሚጠይቅ አለመሆኑን ማወቅ ይገባልም በማለት የመንግሥት አካላትን ቸልተኝነት ነቅፈዋል፡፡

FacebookTwitterLinkedIn


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE