በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ ኩላሊቴን ሁኪሞች ሰረቁኝ ስላለው ታማሚ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዶክተር የስጠው መልስ

በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ ኩላሊቴን ሁኪሞች ሰረቁኝ ስላለው ታማሚ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዶክተር የስጠው መልስ

ህዳር 21/2011 ዓ.ም

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን በተመለከተ ህዳር 19/2011 ዓ.ም በኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ የማታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንነጋርበት በተሰኘ ፕሮግራም ለተለቀቀ መረጃ የተሰጠ የባለሙያ ማብራሪያና አስተያየት

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አንቱ የተባሉ ሆስፒታሎች አንዱ እና ቀደምት ነው፡፡ ሆስፒታሉ በየቀኑ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ታካሚዎች የህክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በሆስታሉ ውስጥም ተምረውና አስተምረው፤ እንዲሁም ሰርተው ያለፉ አሁንም ቢሆን እያገለገሉ ያሉ በሀገራችን ታዋቂ ሀኪሞች ያሉበት ተቋም ነው፡፡

የቀዶ ህክምና ክፍሉም የዚህ ታሪክ ተጋሪ ሲሆን ከበፊት እነ ዶ/ር በርናንድ አንደርሰን (ነፍሳቸውን ይማር)፣ ዶ/ር ዘኪ አብዱረህማን፣ ዶ/ር አመዘነ ታደሰ አሁን ላይ ደግሞ እነ ዶ/ር መሃመድ ከድር፣ ዶ/ር መንሱር ዑስማን እና ዶ/ር ጋሻው መሰለ የመሳሰሉ ታዋቂ ሀኪሞች የሚሰሩበት ትምህርት ክፍል ነው፡፡

የቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍሉም በየቀኑ ከሃያ ያላነሱ ድንገተኛ ቀዶ ታካሚዎችን ባለው ውስን ቦታ ላይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በሰሞኑ በኢሳት ቴሌቪዥን እንዲሁም በተለያዩ ሶሻል ሚዲያ ተጠቃዎች እየተናፈሰ ስላለው የአንድ ታካሚ ሁኔታና የተከሰተውን ብዥታ ለህብረተሰቡ ግልፅ እንዲሆንለት ለማድረግ ነው፡፡

አቶ ጎሼ አበጋዝ የተባለው የ32 ዓመት ታካሚ በ23/10/2008 ዓ.ም በጥይት ሆዴ ላይ ተመታሁ ካለ 6 ሰዓታት በኋላ ሆስፒታላችን መጥቶ ህክምና ተደርጎለታል፡፡ በጊዜውንም 2X3 ሴ.ሜ የሚሆን ጥይት የገባበት ቁስል በግራ ሆዱ ታችኛው ክፍል ላይ ሲደማ ይታይ ነበር፤ ነገር ግን ጥይቱ የወጣበት ቦታ አልነበረውም፡፡ እንዲሁም ሆዱ ውስጥ ደም የመጠራቀም ምልክቶች ነበሩ፡፡ በጊዜውም ሙሉ በሙሉ የደም መጠኑን (BP) መለካት አይቻልም ነበር (Profound Shock) :: ለዚህም የምግብ ዉሃ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ከተደረጉለት በኋላ አራት ሰዓታት የፈጀ ቀዶ ህክምና በዕለቱ ተረኛ በነበሩ የቀዶ ህክምና ሀኪሞች ተሰርቶለታል፡፡

በቀዶ ህክምናው ወቅትም፡-
ትንሹ አንጀት (Small Intestine) ተበጥሶ ነበር፡፡
ትልቁ አንጀት (Large intestine) ተበጥሶ ነበር፡፡
ትልቁ የደም ስር (Left common iliac artery) ተበጥሶ በከፍተኛ ሁኔታ ደም ወደ ሆዱ ይፈስ ነበር፡፡
ሁለት ሊትር ደም ከሰገራው ጋር ተቀላቅሎ ሆዱ ውስጥ ተጠራቅሞ ነበር፡፡
ከግራ ኩላሊቱ እስከ ፊኛው በጥይት አረር የመቃጠል ምልክት ነበር፡፡
ከሆድ ዕቃው ጀርባ (retro peritoneum ) ብዙ የረጋ ደም ነበር፡፡

ለዚህም በሆዱ ተጠራቅሞ የነበረው ደም ተወግዶለታል፣ ትንሹ አንጀት ተሰፍቶለታል፣ የሚደማው የደም ስር ተጠግኖለታል፣ ትልቁ አንጀት ግን ወደ ሆዱ ውጭ ወጥቶ ለጊዜው በዚያ እንዲፀዳዳ ተደርጓል (End Colostomy)፡፡ ታካሚው ባጠቃላይ አምስት ከረጢት ደም ተሰጥቶታል፡፡

በ01/11/2008 ዓ.ም ሆዱ ውስጥ መግል ስለቋጠረ ሁለተኛ ቀዶ ህክምና አድርጓል፡፡

በዚህ ጊዜም፡-
አንድ ሊትር መግል ሆዱ ውስጥ ተጠራቅሞ ነበር
የግራ ኩላሊቱ ታችኛው ክፍል የመቃጠል (መጥቆር) ምልክት ነበረው፤ ለዚህም መግሉ ተወግዶ፣ ሆዱ ታጥቦ ተዘግቶለታል፡፡

በ14/11/2008 ዓ.ም በተደረገለት የአልትራሳውንድ ምርመራ ሁለቱ ኩላሊቶቹ ይታዩ ነበር፡፡

በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት እና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የፕሮቲን እጥረት ስለሚኖር ከሌላ ታካሚ በተለየ መልኩ ለጽኑ ታካሚዎች በተጨማሪነት የሚታዘዝ ምግብ (ተጨማሪ ሁለት እንቁላልና ግማሽ ሊትር ወተት በየቀኑ) ታዞለት ባጠቃላይ 42 ቀናት ሆስፒታል ቆይቶ ደህና ሲሆን፤ በቀጠሮ ወደ ቤቱ በ 04/12/2008 ዓ.ም ተሸኝቷል፡፡

በ09/03/2009 ዓ.ም ኮሎስቶሚ (በሆዱ ያለውን መፀዳጃ) ለማዛወር ሆስፒታል አልጋ ተሰጥቶት፤ ለኦፕራሲዮን (ቀዶ ህክምና) ዝግጅት የሚያስፈልጉ ምርመራዎችን ሲያደርግ ቆይቶ፤ በ17/03/2009 ዓ.ም በተደረገ አልትራሳውንድ ምርመራ የግራ ኩላሊቱ በቦታው አልነበረም፡፡ ይሄም በኋላ ላይ በCT Scan ተረጋግጧል፡፡

በ19/03/2009 ዓ.ም ኮሎስቶሚው ተዛውሮለት፣ በ26/03/2009 ዓ.ም በሰላም ወደ ቤቱ ተሸኝቷል፡፡

ከአልትራ ሳውንድ ምርመራው የምንረዳው፤ የታካሚው የግራ ኩላሊት በአምስት ወር ገደማ ጊዜ ውስጥ በቦታው አልነበረም፣ ነገር ግን ከቀዶ ህክምናው ሪፖርት እንዳየነው ኩላሊቱ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡

በተለያዩ አለማት የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዪት የአንድ ግለሰብ ኩላሊት በሚደርስበት በማንኛውም አይነት ምት ምክንያት መጥፋት ወይም መሟሸሽ (Atrophy) ወይም ወደ ጠጣር ነገር መቀየር ሊያመጣ ይችላል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ታካሚ ኩላሊት ላይም ከሁለቱ አንዱ ተከስቷል ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡

የአንድን ግለሰብ ኩላሊት ለንቅለ ተከላ ለመውሰድ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ፡-
ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ መሆን፤
በዚህ ሙያ ለብቻው የሰለጠነ ባለሙያ (Transplant Surgeon)፤
ከሰላሳ የሚበልጡ ምርመራዎችን ማሟላት፤
ኩላሊቱን ለማቆየት የሚረዳ የተለየ ኬሚካል (ሶሉሽን) እና ማጓጓዣ ዘዴ፤
የሚነቀለዉ ኩላሊት ሙሉ ጤነኛ መሆን ይገባዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከላይ የተጠቀሰው ግለሰብ በሞት እና በህይወት መካከል ውስጥ ሆኖ በነበረበትና ኩላሊቱ ተጎድቶ እያለ ኩላሊቴ ተወሰደብኝ ማለቱ ተዓማኒነቱን ያሳጣዋል፡፡

ከላይ የተገለጸው ግለሰብ የተከሰተው ነገር ቢነገረውም፤ ነገሩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ በተደረገው የሰነድና የባለሙያ ማስረጃ ዩኒቨርሲቲው ነፃ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

በተለይም በአሁኑ ሰዓት ፍርድ ቤቶች ነፃነታቸውን አግኝተው በነፃ ህሊና መፍረድ በሚችሉበት ወቅት የፍርድ ቤት ውሳኔን ባለመቀበል፤ የመገናኛ ብዙሃንንና ማህበራዊ ድረ- ገፆችን በመጠቀም በፈጣሪና በህዝብ ፊት ቃላቸውን ሰጥተው ደፋ ቀና የሚሉ ሀኪሞችንና የጤና ባለሙያዎችን ስም ለማጉደፍ መሞከር፤ባለሙያዎችን ከማሸማቀቅ ባለፈ፤አንጋፋ ሆስፒታሉንና የጤና ተቋሙን በህብረተሰቡ ዘንድ እምነት እንዲታጣባቸው በማድረግ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተጠቀሰውን ግለሰብ ሁኔታ የኢሳት ቴሌቪዥን እንዲሁም አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከአንድ ጎን ባገኙት መረጃ ብቻ ነባራዊውን ሁኔታ በተቃራኒው መልኩ ህብረተሰቡ እንዲረዳውና እንዲሁም በህብረተሰቡና በሀኪሞች፤በጤና ባለሙያዎችና ባጠቃላይ በሆስፒታሉ መካከል አለመተማመን እንዲከሰት ስለሚያደርግ፤ በተቻለ መጠን ሁላችንም አንድን ድርጅት ወይም ግለሰብ ከመፈረጃችን በፊት የተለያዩ መረጃዎችን ብናሰባስብ ለሀገራችን እድገት ጥሩ ነው እላለሁ፡፡

በመጨረሻም ከላይ የተጠቀሰውን ግለሰብ በደረሰበት ከባድ አደጋ እንዲሁም በጊዜው ከነበረበት ህይወቱን ሊያሳጣ ከሚችል ሁኔታ፤በሁለትና ሦስት የተለያዩ የቀዶ ህክምና ሰፔሻሊቲዎች ሊሰራ የሚገባው ቀዶ ህክምና በማድረግና ሌት ተቀን በመስራት ከአንድም ሁለት፣ ሶስት ጊዜ ቀዶ ህክምና በማድረግ፤ ህይወቱን የታደጋችሁ የሆስፒታሉ የህክምና አባላት ክብርና ምስጋና ሊደርሳችሁ ይገባል እላለሁ፡፡

ዶ/ር ደስይበለው ጫኔ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የኩላሊት፤የሽንት ቧንቧዎቸና የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE