ውጥረት አንግሷል ! …. ፊንላንድ እና ሩስያ … ሌላኛው የዓለም ስጋት !

ፊንላንድ እና ሩስያ … ሌላኛው የዓለም ስጋት !

” ፊንላድ NATOን ከተቀላቀለች የአፀፋ እርምጃ እንወስዳለን ” – ሩስያ

የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ምንም ሰላማዊ መፍትሄ ሳያገኝ ወራትን ያሳለፈ ሲሆን ጦርነቱ ለሺዎች ሞት ፣ ለሚሊዮኖች መፈናቀል፣ ለመላው ዓለም የከፋ የኢኮኖሚ መናጋት ምክንያት ሆኗል።

ሩስያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ከገጠመችበት አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት NATOን እቀላቀላለሁ ማለቷ እንደነበር አይዘነጋም።

ከዩክሬን ጦርነት በኃላ ሩስያ ፥ ፊንላንድ እና ስውዲን NATOን ለመቀላቀን ብታስቡ እጅግ ” ጎጂ ” የሆኑ ውጤቶች [ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ] ይኖራል ስትል አስጠንቅቃቸው ነበር።

በኃላም ሀገራቱ NATOን ለመቀላቀል ለማመልከት መወሰናቸውን ተከትሎ ሌላ ውጥረት አንግሷል።

በዛሬው ዕለት ይፋ በሆነ መረጃ ፊንላንድ ያለምንም መዘግየት NATOን ለመቀላቀል ለማመልከት እንደምትፈልግ ገልፃለች። ስውዲንም ፊንላንድን ትከተላለች እየተባለ ነው።

ይህ ደግሞ ሩስያን ክፉኛ አስቆጥቷል።

ሞስኮ ፊንላንድ NATOን ለመቀለቀል ያሳየችውን ፅኑ ፍላጎት እና ዝግጁነት ” ቀጥተኛ ስጋት ” ስትል የጠራችው ሲሆን ” ወታደራዊ-ቴክኒካል ” እርምጃዎችን ጨምሮ አፀፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ አስፈራርታለች።

የዩክሬንና ሩስያ ጦርነት አንዳች መፍትሄ ባላገኘበት ሁኔታ ሌላ ዓለም አቀፋዊ ውጥረት እየተፈጠረ ይገኛል ፤ ይህ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና ለታዳጊ ሀገራትና ለመላው ዓለም የሚተርፍ ነው።