የ 7.2 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ኢትዮጵያ ካላት የቤት ግንባታ ልምድ እና ተጨባጭ አቅም አንፃር አሳማኝ አይደለም ።

የከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት ዐሥርት ዓመታት በመንግሥት፣ በግለሰቦች እና በባለሃብቶች 7.2 ሚሊዮን ቤቶች በከተማ እና በገጠር እንደሚሠሩ ይፋ አድርጓል። ሚኒስቴሩ የቤት ችግር ዜጎችን በእጅጉ እየፈተነ ለከፍተኛ ማኅበራዊ ምስልቅል እያጋለጠ መሆኑን ገልፆ ይገነባሉ ከተባሉት ቤቶች መካከል የመንግሥት የመገንባት ድርሻ ሃያ በመቶ መሆኑን ተናግሯል። አንድ የኪነ ሕንፃ እና የከተማ ፕላን ባለሞያ በኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ አንድም በውልደት በሌላ በኩል ከተለያየ የአገሪቱ አካባቢ ወደ ከተማዋ በሚደረግ ፍልሰት የነዋሪውና የመኖሪያ ቤት ምጣኔ አልጣጣም ብሎ ትልቅ ማኅበራዊ ችግር ሆኗል ብለዋል።

ሌሎች ከተሞችን በማሳደግ አዲስ አበባ ብቸኛ የዜጎች የስበት ማእከል እንዳትሆን ማድረግ ፣ የመሬት የይዞታ ባለቤትነት መብትን መቀየር ብሎም የግል የቤት አልሚዎች ዘርፉን በስፋት እንዲቀላቀሉ በማድረግ ችግሩን ማቃለል ይገባል የሚሉት ባለሙያው የከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በአሥር ዐመታት ውስጥ ይገነባሉ በሚል የያዘው የ 7.2 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ኢትዮጵያ ካላት የቤት ግንባታ ልምድ እና ተጨባጭ አቅም አንፃር ሊታመን የማይችል ነው ብለዋል።