” ጋዜጠኛን ከሕግ ውጭ ሰውሮ ማቆየት ይቁም ” – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከቀናት በፊት ማንነታቸውን ባልገለጹ የመንግስት ሰዎች ተከራይቶ ከሚኖርበት ቤት ውስጥ ተይዞ መወሰዱንና የት እንዳለ አለመታወቁን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ መልስ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል።

ማህበሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፤ ጋዜጠኛው በምን ጥፋት ተጠርጥሮ እንደተያዘና ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ካለመነገሩ በላይ የት እንደሚገኝ አለመታወቁ ከዚህ ቀደምም ማሕበሩ ሲቃወመው የቆየው በሌሎች ጋዜጠኞችም ላይ የደረሰው መሰል ድርጊት አካል ሆኖ እንዳገኘው አሳውቋል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የማህበሩ መስራች አባል መሆኑን በማሳት ታፍኖ ተወስዶ እንዲሰወር የተደረገው የዓለማችን የፕሬስ ነጻነት ሳምንት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ መንግስት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ጥቃት እንደከፈተ ያስቆጥረዋል ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ያጠፋው ጥፋት ቢኖር እንኳን የፍትህ አካላት እንደማንኛውም ተጠርጣሪ በህግ ቁጥጥር ስር ሊውልና ዳኝነት ሊሰጠው ሲገባ ከተያዘበት ቀን አንስቶ የት እንደሚገኝ ሳይገለፅ መቆየቱ የመብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን መንግስት ይህን ያልተገባ አደገኛ አዝማሚያ በጋዜጠኞች ላይ ማድረስ እንደመብት የቆጠረው አስመስሎታል ሲል ኮንኗል።

ማህበሩ ፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ለምን እንደታሰረ፣ የት እንደሚገኝ እና የተያዘበት ምክንያት በግልጽ እንዲነገር በጽኑ ጠይቋል።