የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡


ስርዓተ ቀብራቸው በጋምቤላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የስራ ጓዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ ተፈፅሟል፡፡

ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ ከአባታቸው ከአቶ ኡቦንግ ኡሉምና ከእናታቸው ከወይዘሮ አሪያት ኡሞድ ህዳር 03/ 1965 ዓ.ም በጋምቤላ ወረዳ ፒንኪየው ቀበሌ ነበር የተወለዱት፡፡

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፒንኪየው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጋምቤላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
በ1995 ዓ.ም በጂማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው በመምህርነት ሙያ ተመርቀው ከሀምሌ 01 1985 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 1987 ዓ.ም ድረስ በአቦቦ ወረዳ በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርታቸውን በ1990 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡
ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ ትምህትታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በክልሉ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ቦታ ላይ ያገለገሉ ሲሆን ከመስከረም 07/1998 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ ወር 2005 ዓ.ም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ለክለሉ ልማትና እድገት መፋጠን በቅንነትና በታማኝነት እንዳገለገሉ ተመልክቷል፡፡
ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ የተቀበሉት ህዝባዊና ድርጅታዊ ኃላፊነት ሳያግዳቸው የሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን በኦፔን ዩኒቨርሲቲ በ Management of Business Administration በመቀጠልም በኤዥያ ፕሊፕንስ በሚገኘው ቡሉካን እስቴት ዩኒቨርሲቲ ዶክትሬት ድግሪያቸውን በ Management of Business Administration ተቀብለዋል፡፡
ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ በክልሉ የሰላም ግንባታ ዙሪያ ባከናወኑት ስኬታማ ስራ በአውሮፓ ህብረት በሚደገፈውና Vision Ethiopia Congress for Democracy ከተባለ ሀገር በቀል ድርጅት የዓለም የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ ያገኙ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ ሚያዚያ 2005 ዓ.ም ላይ ኃላፊነታቸውን ለተተኪ አመራር ካስረከቡ በኋላ ከግንቦት ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ፌዴራል መዋቅር ተዛውረው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ በፌዴራል ደረጃ እያገለገሉ በነበሩበት ወቅት ሲከሰት የነበረውን የፍትህ መጓደልና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር በመቃወም የዶክትሬት ትምህርታቸውን ወደተማሩበት ፕሊፒንስ በመሄድ እስከ ዕለተ ሞታቸው በተማሩት ሙያ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ባደረባቸው ህመም እዚያው ፕሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ በሚገኘው ፕሊፒንስ-ቻይና ጄኔራል ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ46 ዓመታቸው ህዳር 07 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ስርዓተ ቀብራቸው ዘመዶቻቸው፣ ወዳጆቻቸውና የስራ ጓዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተፈፅሟል፡፡
ዶክተር ኡሞድ ኡቦንግ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅና የሰባት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE