ለኢኮኖሚያዊ ቀውሱና ለዋጋ ንረት መባባስ ዋና ምክንያት መሬትና የመብት ማሽቆልቆል መሆኑ ተገለጸ

ለኢኮኖሚያዊ ቀውሱና ለዋጋ ንረት መባባስ ዋና ምክንያት መሬትና  የመብት ማሽቆልቆል መሆኑ ተገለጸባንኮች የወለድ ምጣኔያቸውን እንዲያስተካክሉ ተጠየቀ

የመሬት አቅርቦትና የአጠቃቀም መብት በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ መምጣት፣ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ ለዋጋ ንረትም ዋነኛ መንስዔ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ባለሙያዎች ማኅበር ገለጸ፡፡

ማኅበሩ በወቅታዊ አገራዊ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠናውን ጥናት ሰሞኑን ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ የመሬት አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ለዋጋ ንረት መባባስ በዋናነት ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

ለኢኮኖሚያዊ ቀውሱም ሆነ ለዋጋ ንረቱ መባባስ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ቁልፍ ሚና ያለው የመሬት አቅርቦትና በመሬት መጠቀም መብት በከፍተኛ ሁኔታ መሸርሸሩ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ መሆኑንም ማኅበሩ ገልጿል፡፡ በሕጋዊ መንገድ መሬት አግኝቶ ማልማት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን ባደረገው ጥናት ማረጋገጥ መቻሉን የገለጸው ማኅበሩ፣ ይህ ጉዳይ መፍትሔ ካላገኘም የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማኅበር የምርምርና የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፣ ከመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአግባቡ መሬት የማቅረብና የመጠቀም መብት እ.ኤ.አ. በ2013 ወደ 96 በመቶ አካባቢ የነበረ ቢሆንም፣ በ2021 ግን ወደ 21 በመቶ መውረዱን ማኅበሩ ያደረግኩት ባለው ጥናት ያመላክታል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ለግብርናም ሆነ ለማንኛውም ዓይነት ኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም ለቤት ግንባታና በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ መሬትን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ቢሆንም፣ ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ችግር እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡

ባለፉት 25 እና 30 ዓመታት የመሬት አቅርቦትና የመጠቀም መብት በከፍተኛ ሁኔታ እየወረደ መምጣት ደግሞ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና ከመፍጠር አልፎ፣ አሁን ለተከሰተው የኑሮ ውድነት ከፍተኛውን ድርሻ እንዲይዝ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡ ማኅበሩ የችግሩን ግዝፈት ለማሳየት ሌላው የጠቀሰው አኃዛዊ መረጃ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ከ129 የዓለም አገሮች የመሬት አቅርቦትና የአጠቃቀም መብትን በተመለከተ የነበረው አፈጻጸም፣ ኢትዮጵያ 67ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረ ቢሆንም፣ በ2021 ግን ወደ 115ኛ ደረጃ መውረዷ ተጠቁሟል፡፡

መሬትን በሕጋዊ መንገድ አግኝቶ ማልማት ከማይቻልበት ደረጃ መድረሱን የጠቆሙት ጎሽዬ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት መሬት ማግኘት የሚቻለው በሁለት መንገድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አንዱ መሬት ማግኛ ዘዴ ሙስና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መሬትን በመውረር መውሰድ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ይህም በሕጋዊ መንገድ መሬት ማግኘት ከባድ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡ አይደለም ለውጭ ኢንቨስተር ለአገር ውስጥም መሬት ማግኘት ከባድ እየሆነ መምጣቱን፣ በመሆኑም የመሬት አጠቃቀምና በመሬት የመጠቀም መብት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ መሬት የግል ይሁን ወይም የመንግሥት የሚለው ሳይሆን ባለው የመሬት ሥሪት እንኳን በአግባቡ ቢሠራ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤›› በማለት ትንታኔ የሰጡት ዳይሬክተሩ፣ እዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት በትኩረት ቢሠራ ኢኮኖሚውን በማሻሻል ብዙ ለውጦች ሊመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መሬትን በማቅረብና በመጠቀም ረገድ ያለው አፈጻጸም ከ96 በመቶ ወደ 21 በመቶ የወረደው፣ የመሬት ሥሪቱ ተቀይሮ ባለመሆኑ፣ መፍትሔ የሚሆነውም ባለው የመሬት ሥሪት በአግባቡ መሥራት መሆኑንም አክለዋል፡፡

መሬትን በአግባቡ መጠቀም ቢቻል የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል የማኅበሩ ጥናት እንደሚያሳይ የገለጹት ጎሽዬ (ዶ/ር)፣ ችግሩ መዋቅራዊ መሆኑን ተቀብሎ በዚሁ አግባብ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለኢንቨስትመንት፣ ለግብርና፣ ለቤት ግንባታም ሆነ ለመሳሰሉት መሬትን በሕጋዊ መንገድ መጠቀም የማይቻልበት ደረጃ ይደርሳል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ግብርና መር ኢኮኖሚ ትከተላለች ሲባል ትልቁ መነሻ ሀብት ‹‹መሬትና ጉልበት ነው፤›› በማለት ያስታወሱት ጎሽዬ (ዶ/ር)፣ አሁን ግን ትልቁ የመሬት ሀብት ታንቆ እየመከነ መገኘቱ ጉዳት እያስከተለ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ይህም በመሆኑ ግብርናው ኢኮኖሚውን መርቶ ሊነሳ ይቅርና አሁን ባለው ሁኔታ የዕለት እንጀራችንን ሊሰጠን ያልቻለበት ምክንያት፣ በመሬት ዙሪያ ያለውን ችግር መፍታት ባለመቻሉ ነው፤›› ሲሉ ጥናት አቅራቢው ገልጸዋል፡፡ በጥቅል ሲታይ ደግሞ፣ የመሬት አቅርቦትና መሬት ላይ እየታየ ያለው ችግር እየጨመረ የመጣውና ለችግሩ መባባስ መንግሥት በአብዛኛው መቆጣጠር ባለመቻሉ እንደሆነም ጥናቱ አሳይቷል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች፣ ለተቀማጭ ገንዘብ በሚከፍሉት ወለድና በማበደሪያ ወለድ ምጣኔያቸው መካከል ያለው ልዩነት መጥበብ እንዳለበትም ማኅበሩ አሳስቧል፡፡

ባንኮች ለቁጠባ ገንዘብ የሚሰጡት ወለድ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ የዋጋ ንረቱን እንዳባባሰው፣ የማበደሪያ ወለዳቸውም የተመጣጠነ ባለመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም ጠቁሟል፡፡

አሁን እንደሚታየው የኢትዮጵያ ባንኮች ጥሩ ትርፍ ከማግኘታቸውም በላይ ዕድገት እያሳዩ ቢሆንም፣ እያገኙ ያሉት ከፍተኛ ትርፍ በማበደሪያና በብድር ወለድ ምጣኔ መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት እየተጠቀሙ በመሆኑ፣ ለዋጋ ንረት ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡ ለተቀማጭ ገንዘብ የሚታሰበው ወለድና የማበደሪያ ወለድ መካከል ያለው ልዩነት በጣም እየሰፋ መሄዱ፣ ባንኮችን ከመጠበቅ ሌላ ምንም ፋይዳ እንደሌለው የሚጠቁመው የማኅበሩ መረጃ፣ ኢንቨስትመንትን የማያበረታታ ነው ብሎታል፡፡ ስለዚህ በቁጠባና በማበደሪያ ወለድ መካከል ያለው ልዩነት በጣም እንዲጠብ በማድረግ፣ አሁን የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ዓይነተኛ መፍትሔው ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጿል፡፡

‹‹እንዲህ ባለው ልዩነት ላይ ተመሥርቶ የፋይናንስ ተቋማት የሚያገኙት ትርፍ ለኢኮኖሚው ጥቅም የለውም፤›› ያሉት ዳግም (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ተቋማቱ እንዲያድጉና እንዲያተርፉ የሚፈለገው ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብና በመወዳደር ነው ይላሉ፡፡ አሁን እየሠሩበት ባለው ሁኔታ ግን ለእነሱም የማያዛልቅና በተለይ የውጭ ባንኮች ቢገቡ ሊጎዱበት ይችላሉ የሚለውን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በመሆኑም የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ መጠንን ከፍ ማድረግ የማበደሪያ ወለድን መቀነስ፣ በተለይ በዚህ ወቅት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል፡፡ እንደ ማኅበሩ መረጃ ኢትዮጵያ ለቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ ዝቅተኛ ወለድ ከሚሰጡ አሥር የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡