በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን የመልካ ጉባ ወረዳን ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ነፃ መውጣቱ ተገለፀ

  • በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን የመልካ ጉባ ወረዳን ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ነፃ መውጣቱ ተገለፀ
  • ከ200 በላይ ታጣቂዎች መገደላቸው፣ ከ100 በላይ መቁሰላቸውና 22 መማረካቸውም ተገልጿል

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን መልካ ጉባ ወረዳ ባደረገው ዘመቻ አካባቢውን ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ነፃ ማድረጉን የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

በዚህ ዘመቻ በአካባቢው ለ4 ዓመታት ያህል በህዝቡ ላይ ስቃይ ሲያደርሱ ከነበሩ የቡድኑ ታጣቂዎች መካከል በርካታዎቹ መደምሰሳቸው ተገልጿል።

የዕዙ የኋላ ደጀን አስተባባሪና የኦፕሬሽኑ መሪ ኮሎኔል ግርማ አየለ፤ በዚህ ውጊያ ከ200 በላይ የሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ ከ100 በላይ መቁሰላቸውንና 22 መማረካቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ከተደመሠሡት ውስጥም የህወሃት ታጣቂዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

መልካ ጉባ በተፈጥሮው በአስቸጋሪ የመሬት ገፅና ከፍተኛ የውሃ ሙላት ባለው ዳዋ ወንዝ መከበቡ፣ ሸኔን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች በአካባቢው መገኘታቸው፣ ታጣቂ ቡድኑ ለአመታት በአካባቢው በመንቀሳቀስ ይዞታውን ማስፋቱ በዘመቻው የነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ ያሉት ኮሎኔል ግርማ፤ ሰራዊቱ ኹሉንም ችግሮች እንደአመጣጣቸው በመመከት ድል ማስመዝገብ ችሏልም ብለዋል።

የዳዋ ወንዝ ከፍተኛ የውሃ ሙላትን እንደምሽግ በመጠቀም ለማጥቃት ሙከራ ያደረገውን የሸኔ ቡድንን ለመደምሰስ የሰራዊቱ ተነሳሽነት ከፍተኛ ነበር ያሉት ኮሎኔል ግርማ፤ ዘመቻው የህይወት መስዋዕትነት ያልተከፈለበትና በጥንቃቄ የተመራ ተልዕኮ እንደነበርም ገልፀዋል።

ዘመቻው የጠላትን አንገት ያስደፋ፣ በርካታ የተዘረፉ ንብረቶችን ይዞ እንዳይወጣ ያደረገና ለዓመታት ሰላም የጠማቸውን ህዝቦች የሰላም አየር የመለሰ ዘመቻ እንደነበርም ተናግረዋል።

ሸኔ በቦታው በርካታ ዜጎችን በመግደል በጅምላ ቀብሯል ያሉት ኮሎኔል ግርማ መላው ህዝባችን የዚህን አረምኔ ቡድን መጥፎ ተግባር በመረዳት ልጆቹን ከዚህ ሽብርተኛ ቡድን ጥሪ እንዲጠብቅና መከላከያ ኃይሉን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

ሦስት ቀናትን በፈጀው ውጊያ ተማርከው እጃቸውን ከሰጡ የሸኔ አባላት መካከል ወጣት ጉዮ አዲ፣ ወጣት መሃመድ ረሽድ እና ወጣት ሰለሞን አምቢሳ እንዳሉት፤ የሸኔ ታጣቂ ቡድን በተለያዩ የማደናገሪያ ስልቶች በመጠቀም ወጣቱን እየመለመለ የቡድኑ መጠቀሚያ ማድረጉን ይናገራሉ።

ቡድኑ የኦሮሞን ህዝብ ከመጨቆንና የኦሮሞን ህዝብ ከመግደል ያለፈ ምንም ፋይዳ የሌለው ስብስብ መሆኑን የተናገሩት ምርኮኞቹ የኦሮሞ ወጣት የዚህ ሽብርተኛ ቡድን መሰረተቢስ ዓላማ ተጋሪና ፈፃሚ መሆን የለበትም ሲሉ መናገራቸውን ከአገር መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።