“ክርስቶስ ሞቶ የተነሳው ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር ለይቶ ሳይሆን የሰው ልጆችን ሁሉ ነፃ ለማውጣት ነው” ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ

የሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የላልይበላ ገዳማት የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው ለምዕመኑ የመልካም ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በቅድሚያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ወገኖቻችን አንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ብለዋል። ይህ በዓል እግዚአብሔር ወልድ የሰው ልጆችን መከራ አስወግዶ በሞቱ ሞትን ድል ነስቶ የተነሳበት፣ ብዙ ሙታነ ህሊናን፣ ሙታነ ነፍስን፣ ሙታነ ስጋን ያስነሳበት ለሰው ልጆች ትርጉም ያለው በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉን ስናስብና ስናከብር ክርስቶስ ተነሳ ብቻ እያልን አይደለም ‘ክርስቶስ ተነሳ ሙታንንም አስነሳ’ ነው የምንለው ነው ያሉት። ይህ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለው ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ስለዚህ ሁላችንም ክርስቲያኖች ‘ክርስቶስ ተነሳ ሙታንንም አስነሳ’ እንዳልን ሁሉ ብቻችንን የምንበላበት፣ የምጠጣበት፣ በልተን ጠግበን የምንረካበት ጊዜ አይደልም ብለዋል።
በልተን የምናበላ፣ ጠጥተን የምናጠጣ፣ አጊጠን የምናስጌጥ መሆን እንዳለብን ነው የበዓሉ ትርጉም የሚያሳየው ነው ያሉት። እያንዳንዳችን የሰው ልጆች ይህንን ፈለግ መከተል እንዳለብን መክረዋል። የሰው ልጆች ከወደቁበት የ5 ሺህ 5 መቶ ዘመን መከራ ክርስቶስ ሰዎችን ነፃ አወጣን ብለዋል። ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው “ትንሣኤ” ብለን የምናምን ሁሉ ይህንን በዓል ስናከብር፣ ብዙ የወደቁ ወገኖቻችን አሉና እነሱን በማንሳት፣ በመደገፍ፣ በማብላት፣ በማጠጣትና በማልበስ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ክርስቶስ ለሁሉ እንደመጣ ሁሉ እኛም የእሱ ልጆች ለሰው ልጆች ሁሉ መፍትሔ ፈላጊ መሆን አለብን ብለዋል። በዚህ ሰዓት የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ከተለያየ ጎሳና ከተለያየ ማኅበረሰብ የተገኙ፣ የተለያየ እምነት ያላቸው፣ የተለያየ ባህል ያላቸው ወገኖቻችን በመከራ የወደቁበት ሰዓት ነው። እናም እንደ ክርስቶስ እናንሳ፣ እናብላ፣ እናጠጣ ስንል ያለምንም ልዩነት የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ከእኛ የሚፈልገውን እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግ ነው ብለዋል።
የእኛን እርዳታ፣ የእኛን ድጋፍ እየፈለገ የእኛ ቋንቋ ተናጋሪ የእኛ እምነት ተከታይ፣ የእኛ ባህል አራማጅ ባለመሆኑ ሊቀርበት አይገባም ነው ያሉት። ሰው መሆንን መሰረት አድርጎ ነው ክርስቶስ ሰው የሆነው። እኛም ሰው መሆንን መሰረት አድርገን እንደ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በጎ ነገር እናድርግ ሲሉ መክረዋል።
ትንሣኤ የሚከበረው ይህን ሥራ ለመሥራት ነው ብለዋል ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ።
ክርስቶስ ሞቶ የተነሳው ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር ለይቶ ሳይሆን የሰው ልጆችን ሁሉ ነፃ ለማውጣት ነውና ክርስቶስ ተነሳ ብለን ብናከብር እግዚአብሔር በዚህ አይከብርም፤ እግዚአብሔር በዚህ አይደሰትም። በትክክል እሱ የሠራውን ዓላማ እያስታወስን መሥራት፣ እንደ ክርስቶስ ለሌሎቹ መዳን፣ ለሌሎች መነሳት ምክንያት ስንሆን ነው እግዚአብሔር የሚከብረውና የሚደሰተው፤ በዓላችንንም የሚባርከው በዚህ መንገድ ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የመከፋፈልንና የመጠላለፍን መንፈስ አስወግደን አንድ ሆነን የምንነሳበት፣ አንድ ሆነን ኢትዮጵያን የምናስነሳበት ጊዜ፣ ወቅት እንዲሆን አሳስባለሁ። በክርስቶስ መስቀል፣ ሞትና ትንሣኤ የተገኘው ሰላም ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ይሁን ሲሉ ለምዕመኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።