በሸዋሮቢት ለተከሰተው ግጭት ኦሮሚያ ክልል ፋኖን ሲወነጅል አማራ ክልል ኦነግ ሸኔን ወንጅሏል

በሸዋሮቢት ለተከሰተው ግጭት ኦሮሚያ ክልል ፋኖን ሲወነጅል አማራ ክልል ኦነግ ሸኔን ወንጅሏል። ፋኖ በግልጽ ሽብርንና ወረራን የሚመክት ሲሆን ኦነግ ሸኔ ደግሞ ህዝብን በመግደልና በማፈናቀል ላይ የተሰማራ መሆኑ ልዩነቱ በግልጽ ይታወቃል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ በሚገኙ አካባቢዎች ባለፈው ሳምንት እሁድ በተከሰተውና 20 ለሚሆኑ ግለሰቦች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ለሆነው ግጭት ተጠያቂዎቹ የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል።በአካባቢዎቹ ለደረሰው ግድያ፣ ንብረት መውደምና መፈናቀል የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ የሸኔ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን የጅሌ ድሙጋ ወረዳ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ በበኩላቸው ተጠያቂዎቹ የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ።

በኤፍራታና ግድም ወረዳ ዘምቦ ቀበሌ ስር ባለችው ሞላሌ መንደር እሁድ አመሻሹ ላይ በተከሰተው ግጭት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን፣ ስምንት ሰዎች መቁሰላቸውንና 125 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ችሮታው ባሳዝን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ችሮታው የሸኔ ታጣቂ ኃይል እሁድ አመሻሹን መጥቶ በአንድ አርሶ አደር ላይ ጥቃት እንደሰነዘረና በነገታው ሰኞም ቀጥሎ በተደራጀና በከባድ መሳሪያ በታገዘ መልኩ በአካባቢው አርሶ አደርና ሚሊሻ ላይ ጉዳት መድረሱንና በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን ያስረዳሉ።

የጅሌ ድሙጋ ወረዳ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዑመር አልዮ በኩላቸው ለቢቢሲ ግጭቱ እንዴት እንደተጀመረ ሲያስረዱ “የአማራ ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በመሆን ከኤፍራታ ግድም ወረዳ በሞላሌ ቀበሌ በኩል ወደዚህ በመሻገር ከብት የሚያግዱ ልጆች ላይ ተኩስ ከፈቱባቸው” ይላሉ።

በተኩሱ ወቅት አንድ ልጅ የቆሰለ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዑመር፤ ታጣቂዎች ከብቶች ዘርፈው ሄደዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

“ከዚህ በፊትም ነጌሶ ወንዝ በሚባለው ላይ ከብቶቻቸውን ውሃ እያጠጡ በነበሩ ታዳጊዎች ላይ እና በአካባቢው በነበሩ አርሶ አደሮች ላይ ማስፈራራት እና ጥቃት እየተፈፀመ ነበር” ይላሉ።

አቶ ችሮታው በበኩላቸው በጅሌ ጥሙጋ ላይ ፋኖ ነው ጥቃት ያደረሰው በሚለው ሃሳብ የማይስማሙ ሲሆን በአካባቢው ፋኖ አይንቀሳቀስም ብለዋል።

እሳቸው እንደሚሉት በአካባቢው ጥቃት ሲፈጸም አርሶ አደር ሚሊሻዎች ለመከላከል እንደገቡና ግጭቱም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ያስረዳሉ።

“ራሳቸውን ለመከላከል በአካባቢው ያሉ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ሚሊሻዎቻችን እና ነዋሪዎቹ ናቸው እንጂ የተደራጀ ቡድን ወይም የፋኖ ኃይል ከኛ በኩል የገባበትና ረብሻ ያነሳበት ጉዳይ የለም።” የሚሉት አቶ ችሮታው፤ በዚያ በኩል ያለውን ኃይል ሽፋን ለመስጠት ሙከራ ነው በማለት ክሱ ውሃ እንደማይቋጥር ያስረዳሉ።

እንደ አቶ ዑመር ገለጻ በዚህ ግጭት ሙጤ ፈጫ፣ ጥቁሬ ወዳዎ እና ወሰን ኩርኩር ቀበሌዎች ውስጥ በጥቂቱ ወደ ሶስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸው እና ቢያንስ አስር ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም ከአርባ በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ያስረዳሉ።

አቶ ዑመር ይህንን ይበሉ አንጂ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ የሟቾቹን ቁጥር 12 ያደርሱታል።

አቶ ችሮታው በበኩላቸው ከሞላሌ መንደር 1 ሺህ 560 ሰዎች ተፋናቅለው ወደ ጫካና አጎራባች መንደሮች መሰደዳቸውንና በነጌሶና በሌሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል ይላሉ።

ጅሌ ድሙጋ በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ የሚገኝ ወረዳ ነው።

በጅሌ ድሙጋ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለያየ ጊዜ ግጭት የሚከሰት ሲሆን ይህም ግጭት የዚያ አካል መስሏቸው ሁኔታውን ለማረጋጋት ወደ አካባቢው እንዳመሩ የሚናገሩት አቶ ችሮታው የታጠቀና የተደራጀ ኃይል በስፍራው ነበር ብለዋል።

በአካባቢው የሸኔ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ነው የሚሉት አስተዳዳሪው “የብሄር ግጭት ለማስመሰልና ወደ ማህበረሰቡም ከፍ እንዲል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው” ይላሉ።

በአካባቢው በተነሳው ጥቃት ሶስት የአማራ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸው የተነገረ ሲሆን በዚህ ግጭት የልዩ ኃይሉ አባላት ተሳታፊ ነበሩ ወይ? በሚል ቢቢሲ ለአቶ ችሮታቸው ያቀረበላቸው ሲሆን እሳቸውም በምላሹ አካባቢውን ለማረጋጋት ሲገቡ የተገደሉ አሉ ብለዋል።

አስተዳዳሪው ቁጥሩን ባይጠቅሱም “የተሰው አሉ፣ የቆሰሉ አሉ። ልዩ ኃይሉ አካባቢውን ለማረጋጋት ሲገባ ነው የሸኔ ታጣቂዎች እርምጃ የወሰዱባቸው።” ብለዋል

በዚህ ወረዳው ውስጥ የሚኖሩ እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ግለሰብ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት እሁድ፣ የአማራ ታጣቂዎች በማሳ ላይ ያለ አንድ ሰው ላይ ጥቃት በመክፈት ሁለት ልጆችን ከዛፍ ጋር ካሰሩ በኋላ ነው ግጭቱ የተቀሰቀሰው ይላሉ።

እኚህ ግለሰብ እንደሚሉት የአማራ ፋኖ በሸዋ ሮቢት ከብቶቹን ውሃ ሲያጠጣ የነበረ አርሶ አደር አግኝተው ለምን እዚህ ውሃ ታጠጣለህ በሚል 39 ከብቶችን ወስደውበታል ይላል።

መንግሥትም የከብቶቹን ባለቤት ከሚሴ ወስዶ አሰረ፣ የዘረፉትን ደግሞ ለቀቃቸው። በዚህም ግጭት ተቀስቅሶ ነበር።

እኚህ ነዋሪ ኤፍራታ ግድም ወረዳ በኩል ጉዳት ደርሷል በማለት ሞላሌ የተባለችው ቀበሌ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ተናግረዋል።

እኚህ ነዋሪ አክለውም በአሁኑ ጥቃት 12 ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ይናገራሉ።

አቶ ችሮታው በበኩላቸው በአካባቢው ይነሱ በነበሩ ግጭቶች ከቀናት በኋላ በሽምግልና ይፈቱ እንደነበር አስታውሰው እነዚህን ጥቃቶች እየፈፀመ ያለው የአካባቢው አርሶ አደር ሳይሆን ማህበረሰቡን መጠቀሚያ ያደረገው ሸኔ ነው ይላሉ።

“በዚህ አካባቢ የተጠናከረ የሸኔ እንቅስቃሴ አለ። በሎጂስቲክ፣ በከባድ መሳሪያ ታግዞ፣ በተጠናከረ ትጥቅ ነው ጥቃት እየፈጸመ ያለው። የሸኔ ኃይል ሰው በአሰቃቂ ይገድላል፣ ቤት ያቃጥላል፣ ወረራ በመፈጸም ይህንን እየፈጸመ ያለው ከህዝቡ ጋር የኖረው የኦሮሞ ማህበረሰብ አይደለም።” ይላሉ።

በአካባቢው በተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚፈጸሙ ሲሆን በተደጋጋሚ ውይይቶች፣ የህዝብ ለህዝብ መድረክ በሽምግልናና እርቅ ለመፍታት ቢሞከርም ውጤት አላመጣም።

ለአቶ ችሮታው መፍትሄ ብለው የሚያነሱት ጉዳይ የሸኔን ኃይል ሙሉ በሙሉ ማጥፋትና መንግሥት የማያዳግም እርምጃ መውሰድን ነው።

“ሸኔ በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት ነው። ለአሮሞውም፣ ለአማራውም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ስጋት ነው። የማያሳልስ እርምጃ ካልተወሰደ የአካባቢው ማህበረሰብ አሮሞውም፣ አማራውም ሰላም አይኖረውም” ይላሉ።