በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭት አካባቢ ያሉ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና በድጋሜ እንዲወስዱ ተወሰነ

የግጭት እና የጦርነት ቀጠና በነበሩ አካባቢዎች ውስጥ ሆነው የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በድጋሜ እንዲፈተኑ ተወሰነ።

ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ግጭት እና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ተፈትነው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ከዘንድሮ መደበኛ ተፈታኞች ጋር በድጋሜ ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጿል።

እስካሁን ድረስ በተደረጉ የእርማት ሂደቶችን እንደገና ለማየት ሞክሮ ምንም ዓይነት የእርማት ችግር እንደሌለ የገለጸው መግለጫው ጦርነት እና ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የተፈተኑ ተማሪዎችን በማሰብ ውሳኔው መተላለፉን አስረድቷል።

ከ2013 ዓ.ም ከተሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ጋር ተያይዞ የተለያዩ ክልሎች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ከእነዚህ ክልሎች አንዱ የሆነው የአማራ ክልል በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ያስፈተናቸው ተማሪዎች በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ባለማግኘታቸው በፈተናው አሰጣጥና እርማት ላይ ቅሬታዎችን ማቅረቡ ይታወሳል።

ክልሉ ኮሚቴ በማዋቀር “ያልተለመደ የተማሪዎች ውጤት መቀነስ” ላለው ችግር የፈተና እርማት ችግር፣ የፈተና ስርቆት፣ ተማሪዎች በጦርነት አውድ ውስጥ ሆነው መፈተናቸውን ለውጤት መቀነሱ እንደ መላምት አቅርቦ ለፈተናዎች ኤጄንሲ እና ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄውን አቅርቦ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያላመጡ ተማሪዎች ከዘንድሮ መደበኛ ተፈታኞች ጋር በድጋሚ ፈተናውን ይወስዳሉ ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በተገለጸው የማለፊያ ነጥብ ወደ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መግባት ከቻሉት ተማሪዎች በተጨማሪ 4339 ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቅበላ እንዲያገኙ መወሰኑ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ክልሉ ይህ በሚኒስቴሩ የተሰጠው ውሳኔ አመርቂ አለመሆኑን የገለጸ ሲሆን ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ ለወደፊቱ መሻሻል እንዲደረግ አሳስቧል።

የፈተና መሰረቅን በተመለከ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በተመለከተም ምንም ዓይነት ችግር እንዳላገኘ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ ከዚህ በኋላ ከ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ጋር በተያያዘ መሰል ቅሬታዎችን እንደማያስተናግድም ገልጿል።

በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስደው የመግቢያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ምደባም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንደሚካሄድም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በ2013 ዓ.ም 598 ሺህ 679 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ሲሆን በአገሪቷ ትምህርት እየሰጡ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከእነዚህ ተማሪዎች የመቀበል አቅማቸው 25 በመቶ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።