በጋምቤላ ታራሚዎችን ከፍ/ቤት ቀጠሮ ወደ ማረሚያ ቤት ሲመልስ የነበር የፖሊስ ተሽከርካሪ ተገልብጦ ከፍተኛ አደጋ መድረሱ ተገለጸ

  • በጋምቤላ ታራሚዎችን ከፍ/ቤት ቀጠሮ ወደ ማረሚያ ቤት ሲመልስ የነበር የፖሊስ ተሽከርካሪ ተገልብጦ ከፍተኛ አደጋ መድረሱ ተገለጸ
  • በአደጋው የአንድ እስረኛ ህይወት ማለፉም ተነግሯል

በጋምቤላ ክልል መዠንገር ዞን፤ ሜጢ ከተማ ከፍርድ ቤት ቀጠሮ ወደ ማረሚያ ቤት 22 እስረኞችን ጭኖ ሲመልስ የነበረ የፖሊስ ተሽከርካሪ ተገልብጦ ከባድ አደጋ መድረሱ ተገልጿል።

አጠቃላይ በተሽከርካሪው የነበሩ 22 እስረኞችና 4 የፖሊስ አባላት (26 ሰዎች) የአደጋው ሰለባ ሲሆኑ በአደጋው የሞት፣ ከባድ፣ እና ቀላል ጉዳት ተመዝግቧል ተብሏል።

የመዠንገር ዞን ፀጥታ መምሪያ ለሸገር ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው፤ መኪናው ከፊት ለፊት ባጃጅ ገብቶበት እሱን አድናለው ሲል መገልበጡን ገልጾ ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች እና የፖሊስ አባላት ቴፒ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አስታውቋል።

ከእስረኞች መካከል ያመለጠ እንደሌለ ያሳወቀው ፀጥታ መምሪያው አንድ ታራሚ ህይወቱ እንዳለፈ ሌሎቹ ግን በሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

22ቱ ግለሰቦች በተለያየ ጥፋት ተጠርጥረው ማረሚያ የወረዱ መሆናቸውን የገለፀው የፀጥታ መምሪያው ከአዲስ አበባ የሚላክ ” የስንዴ እርዳታ ” ወደ ህዝብ ሳይደርስ መንገድ ላይ ሲሸጡ እና ለግል ጥቅም ሲያውሉ የነበሩ ሰዎች መኖራቸውን መጠቆሙን ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘግቧል።