ኢትዮጵያ ሱዳን ያለባትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍል ጠየቀች

  • ኢትዮጵያ ሱዳን ያለባትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍል ጠየቀች
  • ሱዳን ከአምስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ አለመክፈሏም ተገልጿል

ኢትዮጵያ፤ ሱዳን ያልከፈለቻትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍላት መጠየቋን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ፡፡

እስካሁን ሱዳን ከአምስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ አለመክፈሏንም ተቋሙ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ2014 ስድስት ወራት አፈጻጸሙን ለገንዘብ ሚኒስቴር ባስገመገመበት ወቅት፤ ሱዳን ውስጥ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት አገሪቱ ለኢትዮጵያ መክፈል የነበረባትን የስድስት ወራት ክፍያ መፈጸም አለመቻሏን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሞገስ መኮንን ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት፤ ሱዳን ያልከፈለችው የኤሌክትሪክ ክፍያ መኖሩን ገልጸው፤ ይህ ግን ከዚህ ቀደምም የሚያጋጥም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊትም ሱዳን የተጠቀመችውን የኤሌክትሪክ ውዝፍ ክፍያ ትከፍል እንደነበር የገለጹት ሞገስ የአሁኑም ከቀደመው ጊዜ የተለየ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተገኘው መረጃ መሰረት፤ ኢትዮጵያ ለሱዳንና ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች ትገኛለች፡፡

ኹለቱም አገራት ውዝፍ ክፍያ ቢኖርባቸውም ቀደም ሲል ባለው አሰራር መሰረት ውዝፍ ክፍያውን እንደሚከፍሉ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያም፤ ሱዳን ለተጠቀመችው ኤሌክትሪክ የሚጠበቅባትን ክፍያ እንድትከፍል መጠየቋን ሞገስ የገለጹ ሲሆን፤ ሱዳኖችም ክፍያውን እንደሚከፍሉ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ሱዳን ክፍያውን እንድትፈጽም ከኢትዮጵያ ለቀረበላት ጥያቄም የ “እንከፍከላለን” ምላሽ ሰጥታለች ተብሏል፡፡

ሱዳን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያውን ባለመፈጸሟ ኃይል እንደማይቋረጥ የገለጹት ሞገስ ይሄ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ ሱዳን የተጠቀመችበትን ክፍያ ከመክፈልም ባለፈ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቧንም ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም ለሱዳን እና ጅቡቲ 100 ሜጋ ዋት ኃይል እየተሸጠ መሆኑ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይ ግን ይህ ቁጥር ከአገር ውስጥ አቅርቦት ሁኔታ ጋር እየታየ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ሱዳን፤ 1200 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቧ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ በኩል እየታየ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የኃይል አቅርቦት ጥያቄ እያቀረቡላት ሲሆን ሶማሊላንድ እና ደቡብ ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡