የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ምክትላቸው ፓይተን ኖፍ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ምክትላቸው ፓይተን ኖፍ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው እና ምክትላቸው በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከፌደራሉ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከሰብአዊ ድርጅቶች ተወካዮች እና ከዲፕሎማቲክ አጋሮች ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው፤ የአምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እና የምክትላቸው ፓይተን ኖፍ የኢትዮጵያ ጉብኝት ግጭት ለማቆም፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶች ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ እና ለግጭት በድርድር መፍትሄ ለመስጠት አሜሪካ የምታደርገው ጥረት አካል ነው ብሏል።

የቀድሞውን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በቅርቡ የተኩት ሳተርፊልድ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

አምባሳደሩ መጋቢት 12 እና 13/2014 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተው ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ቆይታ አድርገው ነበር።

የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲደርስ ለማስቻል ግጭት ለማቆም ወስኛለሁ ያለው የአምባሳደሩን ጉብኘት ተከትሎ ነበር።

አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ መጋቢት አጋማሽ ላይ በነበራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ነበር።

ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ሳተርፊልድ በአሁኑ ጉብኝታቸው በሚኖራቸው ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች እና ከሰብአዊ ድርጅት አስተባባሪዎች ጋር ይገናኛሉ ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።