ራሱን በሕግ መግራት ያልቻለ ገዥ ፓርቲ አገር መምራት አይቻለውም፡፡

ከግጭት አዙሪት ውስጥ አለመውጣት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል!
May be an illustrationእውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳንስ በጭካኔ ደም የሚያፋስሱ ቅራኔዎች ሊኖሩ ቀርቶ፣ ከዕለት ኩርፊያ የሚዘሉ ጠቦች እንዲፈጠሩ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን አገርና ሕዝብ ንቀው ለሥልጣናቸውና ለጥቅማቸው ብቻ የሚራኮቱ ከንቱዎች ናቸው የበዙት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና የመሳሰሉ ልዩነቶቹን እንደ ጌጥ ተጠቅሞ ሲጋባና ሲዋለድ ነው የሚታወቀው፡፡ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው እንጂ፣ የዘመኑ ነፍሰ በላ ፖለቲከኞች እንደሚያስቡት እርስ በርስ ለመገዳደል የሚፈላለጉ ሆነው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የሚታወቁት በከፍተኛ ፍቅር ለአገራቸው በአንድነት ተሠልፈው መስዋዕት ሲሆኑ እንጂ፣ አገራቸውን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፈው ሲሰጡ አይደለም፡፡ እነ ዶጋሊ፣ ጉንደት፣ ሰሃጢ፣ መተማ፣ ዓድዋ፣ ማይጨው፣ ካራማራና የመሳሰሉት ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ዓውደ ግንባሮች ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ ዘመን ግን አገርና ሕዝብን ከሥልጣን ምኞታቸው በታች ያደረጉ መሰሪዎች፣ በታሪክ የሚያስወቅስና የሚያስወግዝ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብተው መከራ ያሳጭዳሉ፡፡ ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትም አገርን ያመቻቻሉ፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ በሕግና በሥርዓት መመራት ነው፡፡ መንግሥትን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የሚታየው ውስጣዊ ሽኩቻ መላ ካልተፈለገለት፣ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገርን ይዞ የመጥፋት ዕምቅ ኃይል አለው፡፡ በተለይ የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ቅርንጫፎች እያሳዩት ያለው አደገኛ አዝማሚያ፣ ፓርቲውን ከመበተን አልፈው ለአገሪቱም ጦስ እንደሚያስከትል መታወቅ አለበት፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው አደገኛ ጦርነት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሳይወጣ፣ የብልፅግና ፓርቲ ውስጣዊ ዲሲፕሊን መበላሸት የከፋ መዘዝ እንደሚያስከትል መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ራሱን በሕግ መግራት ያልቻለ ገዥ ፓርቲ አገር መምራት አይቻለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ ኃጢያቱ ከሚቀጣባቸው በደሎች መካከል ለከት ያጣው የኑሮ ውድነት፣ ግጭትና ውድመት፣ እንዲሁም በሕግና በሥርዓት አለመመራት ይጠቀሳሉ፡፡ ሕዝቡ ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ መንግሥትን በችግሮቹ ላይ ለማሳሰብ ጥረት ቢያደርግም አዳማጭ እያገኘ አይደለም፡፡ በግጭት ውስጥ መኖር ታክቶታል፡፡ ከግጭት አዙሪት ውስጥ አለመውጣት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል!
ተጨማሪ ያንብቡ: http://bit.ly/38LdCwf