ገንዘብ ሚንስቴር መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ ሳያስፈልግ ወደ አገር ውስጥ ገበያ እንዲገቡ መፍቀዱን አስታውቋል። መንግሥት ያለ ውጭ ምንዛሬ ፍቃድ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል እንዲገቡ የፈቀደላቸው የምግብ ሸቀጦች፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ሩዝ፣ ስኳር፣ የሕጻናት ወተት ሲሆኑ፣ የውጭ ምንዛሬው ምንጭ በብሄራዊ ባንክ እየተረጋገጠ ሸቀጦቹ ለ6 ወራት እንዲገቡ ነው የተፈቀደው። መንግሥት ይህንኑ የወሰነው፣ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአገር ውስጡን ገበያ ለማረጋጋት ለምግብ ሸቀጦች ማስገቢያ የፍራንኮ ቫሉታ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ በመቆየታቸው እንደሆነ ተገልጧል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴ፣ የህጻናት ወተት እና ሩዝ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ ( ፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ በኩል በቀጥታ እንዲገቡ መወሰኑን አስታወቀ።
ውሳኔው የተላለፈው በአገሪቷ ውስጥ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የውጭ አገር የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ በአፋጣኝ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ እያቀረቡ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።
በመሆኑም መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ሸቀጦች የሆኑት ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የህጻናት ወተት እና ሩዝ ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ለስድስት ወራት በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በቀጥታ እየተፈቀደ እንዲገባ መወሰኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የምንዛሬ ምንጩም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይረጋገጣል ተብሏል።
ሚኒስቴሩ የምግብ ዋጋን ለማረጋጋት ምርትን ያለውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲገባ ሲፈቅድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት እንዳልቻለ የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች እና የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋቶች ለምግብ ዋጋ ንረት እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ።
ይህንን ችግር ለማቃለል የአገር ውስጥ ምርትን መጨመር ወሳኝ መፍትሔ እንደሆነ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
ፍራንኮ ቫሉታ ምንድን ነው?
ፍራንኮ ቫሉታ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ሲሆን የባንክ ቤት ፈቃድ ሳያስፈልገው ከውጪ አገር ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል ፈቃድ ነው።
የፍራንኮ ቫሉታ መብት ያላቸው አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቧቸው ምርቶች የውጪ ምንዛሬን በተመለከተ በብሔራዊ ባንክ የወጡ እና በንግድ ባንኮች የሚተገበሩ ጥብቅ መመሪያዎችን የማለፍ ግዴታ የለባቸውም።
ይህም ማለት የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት የባንክ ቤቶች ፍቃድ ሳያስፈልገው በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የማስገባት መብት ያገኛል ማለት ነው።