የኦሮሚያ ክልል፤ የአማራ ክልል የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች የመገናኛ አውታሮችን “ጥላቻ በመስበክ” እና “የግጭት ነጋሪት በመጎሰም” ከሰሰ። የክልሉ መንግስት ዛሬ ሰኞ መጋቢት 26 ባወጣው መግለጫ፤ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለደረሰው ጥቃት “በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ” ያላቸውን “ጽንፈኛ ኃይሎች” ተጠያቂ አድርጓል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በዛሬው መግለጫው፤ “ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና የወንድማማችነት ጸር ነው” ያለውን “ጽንፈኝነት” አስመልክቶ ያለውን አቋም አሳውቋል። ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ “ለዜጎች መፈናቀል፤ ሞት እና ሰቆቃ መንስኤ” መሆኑን የጠቀሰው የክልሉ መንግስት፤ “ለሀገራዊ መግባባት እና ምክክር ጋሬጣ ሆኖ ይገኛል” ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል።
በክልሉ መንግስት መግለጫ “እዚህም እዚያም የሚታይ” ለተባለው “ጽንፈኝነት” መባባስ ምክንያቱ፤ “በባህሪው ላይ ተመሳሳይ አቋም አለመያዙ” መሆኑ ተጠቅሷል። “የህዝባችንን እሴት የማይመጥኑ ጽንፈኞች በሚፈጥሩት መሳሳብ ቀላል የማይባል ሀገራዊ ጉዳትን በማስከትልና እሴቶቻችንን በመሸርሸር ላይ ይገኛሉ” ያለው የኦሮሚያ ክልል መንግስት፤ “የእነኚህን ጽንፈኛ ኃይሎች እኩይ ተግባርን አንድ ቦታ ማስቆም ካልተቻለ በሀገራችን ሌላ አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
———————————-
ተጨማሪ ኢሰመጉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ወረዳ መጋቢት 20 ላይ ታጣቂ ቡድኖች አንድ ሰው እንደገደሉ እና 7 ሰዎችን እንዳቆሰሉ መረጃ እንዳገኘ ገልጧል። ታጣቂ ቡድኖቹ በወረዳው አሞራ ቤት ቀበሌ ጥቃት የፈጸሙት በመንግሥት ተሽከርካሪዎች ጦር መሳሪያ በመጫን እንደሆነ ኢሰመጉ ጠቁሟል። በዕለቱ በቦታው በተፈጠረ ግጭት ደሞ 26 ሰዎች እንደተገደሉ፣ ብዙዎች እንደቆሰሉ እና እንደተፈናቀሉ አጣርቻለሁ ያለው ኢሰመጉ፣ የታጣቂ ቡድኖቹንም ሆነ ሞቱ የተባሉትን ሰዎች ማንነት ግን አልገለጸም። የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ስለ ክስተቱ የሚጣረሱ መረጃዎች ማውጣታቸው ይታወሳል።