አዲስ አበባ ላይ ወጣቶች እየታፈሱ ነው የሚባለው ውሸት ነው ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስተባበለ

‹‹በከተማ ፖሊስ ወጣቶች እየተለቀሙና እየታሰሩ ነው››

ኢዜማና ባልደራስ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ከተከበረው የዓድዋ ድል በዓል ላይ ተቃውሞ ያሰሙ የከተማዋ ወጣቶችን “በጅምላ እያሰረ ነው” ተብሎ የቀረበውን ወቀሳ አስተባበለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባወጧቸው መግለጫዎች ወጣቶች በከተማው ፖሊስ “ተለቅመው” እየታሰሩ መሆኑን ቢናገሩም፣ ኮሚሽኑ “በየትኛውም መመዘኛ ወንጀል ሳይሠራ የሚያዝ ሰው የለም፤” ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፣ “ወጣቶች እየታፈሱ ነው የሚባለው ውሸት ነው፤” ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ግለሰቦች እየተጠየቁ ያሉት ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት ሳይሆን በሕጉ አግባብ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ “ወጣቶች ታፍሰዋል” ተብሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚዘዋወረው መረጃ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለኮማንደር ፋሲካ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ “ወጣቶችን” አስመልክቶ ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ “ወጣቶች አይደሉም የሚታሰሩት፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች አሉ፣ የሠሩት ወንጀል ነፃ የሚያደርጋቸው ከሆነ ይወጣሉ፤” ብለዋል፡፡

አክለውም ይህንን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ግለሰቦችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችንና ተቋማትን የሚዘልፉ፣ የሚሳደቡና የሚያዋርዱ ሐሳቦች ይዘዋወራሉ በማለት ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

ፖሊስ ኮሚሽን ይህንን ቢልም የአዲስ አበባ ወጣቶችን እስር አስመልክቶ መግለጫ ያወጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) በከተማው ፖሊስ ወጣቶች “እየተለቀሙ እየታሰሩ” ነው ብለዋል፡፡

ኢዜማ ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከዓድዋ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የከተማዋ ነዋሪ ወጣቶች “እየተለቀሙ እየታሰሩ” መሆኑን ሲከታተል መቆየቱን አስታውቆ፣ “የከተማው ወጣት አንገቱን እንዲደፋ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራ ይገኛል፤” ብሏል፡፡

ወንጀል የሠሩ ዜጎች በወንጀላቸው ልክ መጠየቅ እንዳለባቸው የገለጸው ኢዜማ፣ በጅምላ እያሰሩና ፍርድ ቤት እያመላለሱ ለማሸማቀቅና የከተማውን ወጣት የፖለቲካ ተሳትፎ ለማፈን መሞከርን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡ ፓርቲው አክሎም ከዓድዋ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ “ያለ አግባብ የታሰሩ” የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከበረው የካራማራ ድል በዓል ላይ አባላቱ ለእስር እንደተዳረጉ ያስታወቀው ባልደራስ በበኩሉ፣ የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ 34 የፓርቲው አባላትና በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች መታሰራቸውን ከገለጸ በኋላ እስሩ መግለጫው በወጣበት ዕለትም መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡

ባልደራስ በከተማዋ ወጣቶች ላይ ተፈጽሟል ያለውን እስር “ጉልበትን እንጂ ሕግን መሠረት ያላደረገ” በሚል የገለጸው ሲሆን፣ “አንድን የፖለቲካ ፓርቲና የአዲስ አበባን ልጆች የማሳደድ መንግሥታዊ ዕርምጃ በአገራችን ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ብሔራዊ ንግግርም ሆነ ለከተማዋ መረጋጋት ፈጽሞ የሚበጅ አይደለም፤” ብሏል፡፡

ሁለቱም ፓርቲዎች በመግለጫቸው በዓድዋ ድል በዓል ላይ የተገኙ ወጣቶች መንግሥት ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ባልደራስ ተቃውሞው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተገለጸ መሆኑን ሲያስታውቅ፣ ኢዜማ ደግሞ ክብረ በዓሉ ላይ የተቃውሞ ድምፆች እንዲኖር ያደረገው “የመንግሥት ፀብ አጫሪነት ነው” በማለት በመንግሥት ላይ ወቀሳውን ሰንዝሯል፡፡

የዓድዋና የካራማራ የድል በዓል ላይ የተስተዋሉ ሁነቶችን አስመልክቶ የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የኢፌዴሪ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፣ “አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች” በሁለቱ የድል በዓላት ላይ በመገኘት፣ “በአገራችን ብሔር ብሔረሰቦችና በሕዝብ መካከል ግጭት ለመቀስቀስ ሞክረዋል፤” ብሏል፡፡ “የፀጥታ አካላትን ክብር አፀያፊ ስድቦችን በመሳደብ ደፍረዋል፤” በሚል ከሷል፡፡

በተጨማሪም ግብረ ኃይሉ፣ እነዚህ ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ከዚህ ድርጊት የማይቆጠቡ ከሆነ፣ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድና በሕግም ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው አስጠንቅቋል፡፡

“የሚታፈስ ወጣት የለም” ተብሎ የተነሳውን ወቀሳ ያስተባበሉት የአዲስ አበባ ፖሊስን ኮሚሽ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ፣ ዓቃብያነ ሕጎች ከፖሊስ ጋር አብረው እየሠሩ መሆኑን በመጥቀስ፣ በሚደረገው ማጣራት በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸው ወይም ቢወጡ መረጃ የማያጠፉ በዋስትና እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በከተማዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን 15 በመቶ ለመቀነስ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ መቀነስ የቻለው አምስት በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በአንፃሩ በግማሽ በጀት ዓመቱ ባደረጋቸው ብርበራና ፍተሻዎች እንደ ቦምብ፣ ፈንጂ፣ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች፣ ልዩ ልዩ ሽጉጦችና ሌሎች መሣሪያዎችን፣ እንዲሁም የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን መያዙን አስታውቋል፡፡