በወቅታዊ የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ – የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

በወቅታዊ የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ሰላም ሁላችንም ዘብ የምንቆምለት እና የምንታገልለት ዋና ጉዳያችን ነው፡፡ በምንም አይነት መንገድ የከተማችንን ሰላም እና ፀጥታ የሚያውኩ እና ለህግ የማይገዙ ኃይሎችን አጥብቀን የምናወግዝ ቢሆንም በሰላም ማስከበር ስም ዜጎች ላይ የሚካሄድ መንግሥታዊ አፈናን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡

በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከአድዋ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የከተማዋ ነዋሪ ወጣቶች እየተለቀሙ እየታሰሩ መሆኑን በትልቅ ትኩረት ሲከታተል ቆይቷል፡፡ የከተማውም ወጣት አንገቱን እንዲደፋ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ጥያቄዎቹን እንደመሰረታዊ ጥያቄ ወስዶ መነጋገር ሲገባ የመጠየቅ መብቱን እንዳይጠቀም እና በጅምላ በመፈረጅ ምንም አይነት ፖለቲካዊ እና ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ እንዳይኖረው እየተሰራ ይገናል፡፡

አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖሪያ፣ የሀገራችን የፖለቲካ ማዕከል እንዲሁም የዲፕሎማቶች መቀመጫ ከተማ ናት፡፡ የመዲናዋ ነዋሪ በተለያዩ አገዛዞች ወቅት በእጅጉን የተነቃቃ፣ የሀገሪቷ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የነበረው እና ተሳትፎው ለመላው ኢትዮጵያውያን አለኝታ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫ 97 በእርግጠኝት እንደሚያሸንፍ ሲተማመን ንቁ የነበረው ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ገዢውን መንግሥት በካርዱ በመቅጣቱ፤ በጊዜው የነበሩ አምባገነኖች በወሰዱት እርምጃ የከተማው ነዋሪ በተለይም ወጣቱ ከፖለቲካው እንዲገለል በር ከፍቷል፡፡ ይህም ሆኖ ወጣቱ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ ከማድረግ ሳይቦዝን የተቻለውን እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

‹‹የለውጡ ሀይል›› ሀገርን ማስተዳደር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የአዲስ አበባ ህዝብ በተለያዩ ክልሎች እንዲሁም በመዲናቸን ሕገ ወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ፣ በታጣቂዎች ግለሰቦች ሲገደሉ፣ ቤተ እምነቶች የእሳት ራት ሲሆኑ፣ በአራቱም ማዕዘን ሀገሪቱ የጦር አውድማ ስትመስል በለውጥ ጊዜ የሚከሰት ኩነት ነው በማለት በከፍተኛ ትዕግስት ሀገርን ለሚመራው አካል ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣና ሰላም እንዲያስጠብቅ እድል ሲሰጠው እንደቆየ ይታወቃል፡፡

በዘመናት የትውልድ ቅብብሎሽ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር በጽናትና በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ የመጣው የአድዋ ድል ዝክረ በዓል የታሪካችን ትልቁ አሻራ እና የከተማችን ህዝብም ኩራት ነው፡፡ የ2014ቱ የዚህ የመላው ጥቁረች ድል በዓል አከባበር ቦታና ሁኔታን በተመለከተ መንግሥት የተለያዩ መግለጫዎችን እየሰጠ ህዝብን ግራ ሲያጋባና ሲያስቆጣም ነበር፡፡ በአድዋ ክብረ በዓል ላይ የተቃውሞ ድምፆች የነበሩ ሲሆን ያንን ያደረገው የመንግስት ፀብ-አጫሪነት ነው፡፡ ወንጀል የሰሩ ዜጎች ካሉ በወንጀላቸው ልክ መጠየቅ እንጂ በጅምላ እያሰሩ እና ፍርድ ቤት እያመላለሱ በጅምላ ለማሸማቀቅ እና የከተማውን ወጣት የፖለቲካ ተሳትፎ ለማፈን መሞከርን በከፍተኛ ሁኔታ እንቃወማለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የነዋሪ ቁጥርና የፖሊስ ኃይል ምጥጥን ለማስተካከል የአዲስ አበባ ከተማ የፖሊስ አባላት ቁጥርን 50ሺ ለማድረስ በሁሉም ክልሎች መልማዮች መላካቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

የመዲናዋን ጸጥታ የሚያስጠብቁ፣ በዋናነት በፖሊስነት የሚጠብቋት ዘቦች የከተማዋ ነዋሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የከተማዋን ሁሉን አካታችነት ተገን በማድረግ ከተለያየ ቦታ፣ ከሌሎች አካባቢዎች ፖሊሶቿን መመልመል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የከተማዋ ባለቤቶች እና ባለመብቶች ሲሆኑ ከተማዋን የማስተዳደር እና በፀጥታ ዘርፍ ተሰማርቶ መጠበቅ የከተማዋ ነዋሪ ሀላፊነት ነው ብለን በጥብቅ እናምናለን፡፡

ስለዚህም፡-
1. ከአድዋ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ያለ አግባብ የታሰሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲፈቱ፣
2. ወንጀል ሰርተዋል ተብሎ ለታመነባቸው፡-የፍትሕ ሥርዓቱ በነፃና ገለልተኛ መንገድ እንዲታይ፣ ችሎቱም ለሕዝብና ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት እንዲሆን፣
3. በሕግ ከለላ ሥር የሚገኙ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻቸው፣ በጓደኞቻቸውና በጠበቆቻቸው እንዲጎበኙና ሌሎችም መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣
4. የከተማዋ ፖሊስ ከከተማዋ በተውጣጡ ዜገች እንዲጠናከር፡፡
5. የከተማዋ ወጣት በተደጋጋሚ ከተማውን ለመጠበቅ ፍቃደኛ አይደለም ተብሎ ቢነገርም ሀገር ጭንቅ ውስጥ በገባችበት ወቅት ከመቶ ሀያ ሺ (120,000.00) በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማቸውን ሲጠብቁ እንደከረሙ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ ነዋሪዎች መካከል ብቃትና ፍላጎት ያላቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የከተማውን ፖሊስ እንዲቀላቀሉ
6. የተከበረው የአዲስ አበባ ነዋሪ የከተማ አስተዳደሩን እንቅቃሴዎች በትኩረት እንዲከታተል እና በምርጫው ወቅት የነበረው አይነት መዘናጋት እንዳያሳይ እናሳስባለን፡፡

ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ፣ የውስጥ ለውስጥ ብክነትና ዝርፊያ እንዳይጋለጥ፣ ወጣቱ እንዳይቃወማቸው በጥቅማጥቅም መደለያ ድምጹን ለማፈን የሞከሩ አካላት በተቃራኒው ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ‹‹ሕዝቡ በዚህ ልክ ለምን ተቃወመን?›› ብሎ ራስን ከመመርመር ይልቅ ‹‹ከእኛ ጎን ለምን አልቆመም?›› በሚል ወጣቶችን በጅምላ ማሰር የሥርዓቱን ፍጹም ደካማነት እና ለትችት ክፍት አለመሆን የሚያሳይ ነው፡፡

በመሆኑም በሕዝብ ድምጽ ተመርጬ አገር እየመራሁ ነው የሚል መንግሥት ዜጎች የተቃውሞ ድምጽ ባሰሙ ቁጥር ማሰር እና ማንገላታቱ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የከተማው ነዋሪን በዚህ እሰብራለሁ ብሎ ማሰብ መሪዎቻችን ምን ያህል የሚያስተዳድሩትን ህዝብ እንደማያውቁ ከመጠቆም ያለፈ ሚና የለውም፡፡ ለማረም እና ማስተካከል መስራት እንጂ ለመሸፈን መሞከር ችግሮችን አያጠፋም፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አዲስ አበባ ከተማ በተጋረጡባት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመጪው ሳምንት ለሁሉም ሚድያዎች ክፍት የሚሆን ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
መጋቢት 8፣ 2014 ዓ.ም